የእለት ዜና

የነሐሴ ወር አጠቃላይ የምግብ ዋጋ ግሽበት 37.6 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል

ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባወጣው መረጃ መሠረት የነሐሴ ወር 2013 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር 2012 ጋር ሲነጻጸር በ30.4 ከመቶ ከፍ ያለ እንደሆነ ታውቋል።
በዚህም የዋጋ ግሽበቱን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጋር በማነጻጸር የሚገኘው ውጤት ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን ያሳያል።
በዚህ መሠረት የነሐሴ ወር 2013 ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር 2012 ጋር ሲነጻጸር የምግብ ዋጋ ግሽበቱ የ 37.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በነሐሴ ወር የነበረው አጠቃላይ የምግብ ዋጋ ግሽበት 37.6 በመቶ ሲሆን፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሸበት ደግሞ 20.8 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።
በዳቦና እህሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በያዝነው ወርም የቀጠለ ሲሆን፣ በተለይ የሩዝ፣ የእንጀራ፣ የዳቦ፣ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የማሽላ፣ የበቆሎ፣ የገብስ፣ የስንዴ ዱቄት፣ የፓስታና ማካሮኒ ዋጋ በፍጥነት ጨምሯል ተብሏል።
በተጨማሪም ሥጋ፣ የምግብ ዘይት፣ ወተት፣ አይብና ዕንቁላል፣ ቅቤ፣ ቅመማቅመም (ጨውና በርበሬ) እና የቡና ዋጋ ጭማሪ በዚህም ወር መቀጠሉ ለዋጋ ግሽበቱ ምጣኔ በፍጥነት መጨመር አስተዋጽኦ አድርጓል።
ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት እንዲሁ የነሐሴ ወር 2013 ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር 2012 ጋር ሲነጻጸርም የ20.8 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በአልኮልና ትምባሆ፣ ልብስና ጫማ፣ አነቃቂዎች (ጫት)፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጅ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች (የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮ)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማስጌጫዎች፣ ሕክምና እና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ፤ ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት በዚህ ዓመት ከፍ እንዲል ካደረጉት ውስጥ ዋና ምክንያቶች ናቸው።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!