የእለት ዜና

ከ13 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት 426 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ሲል የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ

Views: 46

አስቸኳይ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያን 426 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲደረግለት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጠየቀ። ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፉን የጠየቀው በመጪዎቹ 6 ወራት ከ13 ሚሊዮን በላይ የአስቸኳይ ድጋፍ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት ነው።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሚካኤል ዱንፎርድ ድርጅቱ በኢትዮጵያ እያደረገ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ እና በቀጣይ ሥራዎቹ ዙሪያ መግለጫ መስጠታቸውን ድርጅቱ በድረ-ገጹ ገልጾ፣ አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ዕርዳታ በማከፋፈል ላይ እንደሆነ አስታውቋል።
ደርጅቱ አክሎም፣ በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች 7 ሚሊዮን ዜጎች የረሀብ አደጋ እንዳያጋጥማቸው የአስቸኳይ ዕርዳታ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
በትግራይ ክልል ያሉ ተረጂዎችን ለመድረስ ከአፋር ክልል መንግሥት ጋር በመነጋገር የተለያዩ የሰብዓዊ ድጋፎችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች እየተጓጓዙ መሆኑንም የድርጅቱ ሪፖርት ያስረዳል። በኢትዮጵያ ከጦርነቱ በተጨማሪ ድርቅ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ጎርፍ እና የኮሮና ቫይረስ የአስቸኳይ ድጋፍ የሚጠይቁ ዜጎችን ቁጥር እንዳሻቀበው ድርጅቱ በመግለጫው አክሏል።
በዚህም አሁን ላይ በኢትዮጵያ 13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች የአስቸኳይ ምግብ ድጋፍን እንደሚፈልጉ ገልጾ፣ በጦርነቱና በሌሎች ምክንያቶች የተፈናቀሉ እና ለዕርዳታ የተዳረጉ ዜጎችን ለመርዳት 426 ሚሊዮን ዶላር ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግለት ጠይቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com