የእለት ዜና

ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶች ለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መመለሳቸው ተገለጸ

በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከአንድ መቶ ሃምሳ ሦስት ዓመት በፊት ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶችን ማሰመለሱን አስታውቋል።
በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን ጦርነት ላይ ያገለግሉ የነበሩ ጋሻ፣ ከቆዳ የተሠራና በእጅ የተጻፈ የብራና መጽሐፍ ቅዱስ እስከነመያዣው፣ መስቀሎች ፣ ጽዋ የሚወሰድበት ዋንጫ ከነማንኪያዎቹ፣ የጳጳስ አክሊል፣ ከቀንድ የተሠሩና በብር የተለበጡ የቀንድ ዋንጫዎች ከነመስቀሉ ለኤምባሲው ተመልሰዋል።
የዩናትድ ኪንግደም የበጎ አድራጎት ድርጅት ቬሄራዜድ ከለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርሶቹ ዙሪያ ወራትን የወሰዱ ድርድሮችን አድርጓል። ለሽያጭ ቀርበው የነበሩትን ከገበያ እንዲነሱ በማድረግ ቅርሶቹ ለባለቤታቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲመለሱ መደረጉ በርክክቡ ወቅት ላይ ተገልጿል።
ለንደን በሚገኘው አቴናም በተባለና የዩናይትድ ኪንግደም ልሒቃን ክለብ በተካሄደ የርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ ፣ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከኤምባሲው ጋር በመተባበር ላደረገው ሠፊ ጥረት ምስጋና ተችሮታል። እነዚህ የአገር ሀብቶች ከቅርስነት በላይ የኢትዮጵያን የጀግንነትና የኃይማኖት ታሪኮች ለትውልድ የሚያስተላልፉ ጽኑ የሆኑ ማስታወሻዎች በመሆናቸው ራሳችንን መልሰን እንድናገኝ የሚረዱን መለያዎቻችን ናቸው ሲሉ በለንደን የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ተናግረዋል።
የተመለሱት ቅርሶቹ ለኢትዮጵያ መንፈሳዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ዕሴቶች ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ወደፊትም በእንግሊዝ ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶች እንዲመለሱ እየተሠራ መሆኑን አምባሳደር ተፈሪ ጨምረው ገልጸዋል።
የቬሄራዜድ በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ጣሂር ሻህ፣ ከቅርሶቹ መካከል የተወሰኑት በኤምባሲውና በሚመሩት በጎ አድራጎት ድርጅት አማካይነት ለሽያጭ ከቀረቡበት የታገዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህ ቅርሶች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸው ፋይዳ ትልቅ በመሆኑ ለባለቤቱ እንዲመለሱ መደረጋቸው የኹለቱን አገሮች የቆየ ግንኙነት ወደተሻለ ጥልቅ ትሥሥር የሚያሻግር ነው ብለዋል።
በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ዶክተር አሉላ ፓንክረስት በበኩላቸው፣ ይህ ቀን ለኢትዮጵያ የአንድነት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል። ጥንታዊ ታሪክ ያላትን አገር ቅርሶቿን በአግባቡ እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉ የአገራቱን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ገጣሚና የማንቸስተር ዩኒቨርስቲ ቻንስለር ለምን ሲሳይም፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን እንኳን ደስ አለን፤ ታሪክ የአገር መሠረት በመሆኑ የቅርሶቹ ርክክብ ለኢትዮጵያ ሌላ ምዕራፍ ነው ብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!