የእለት ዜና

የኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ ማሻሻያ በሚመለከተ ፔ ኤች ኢ ከኮርሃ ጋር ያዘጋጀው መድረክ

ዓለም ዐቀፍ የሥነ-ሕዝብ ቀን በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ በተግባር ማዋል ከጀመረች ከፈረንጆቹ 1993 በኋላ ማክበር ጀምራለች። በዓለም ደረጃ ሲከበር የቆየው ከዛ ቀደም ብሎ በነበሩት አራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሲሆን፣ ይህ ቀን በአብዛኛው የሚከበርበት ምክንያት ኹለት የተለያዩ ባህሪያትን መሠረት አድርጎ ነው። አንደኛ ሰዎች በተፈጥሮ ውልደት በየጊዜው ብዛት ስለሚኖረን እና የምናመርት ሰዎች በመሆናችን ነው ሲሉ በ ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም የፖፑሌሽን ላይቭሊሁድ ፕሮግራም አስተtባባሪ አቶ አሕመድ መሐመድ ገልጸዋል። ስለዚህ የዓለም ሕዝቦች የሥነ ሕዝብ ቀን ላይ አይናቸውን ገልጠው እንዲያዩ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መንገዶች መፈጠር አለባቸው።
የሥነ-ሕዝብ ጉዳይ ችላ የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነ ለማሳየት በፖሊሲ ተደግፎ ቀኑን በስራቴጂ መመራት እንዳለበት የሚሳይ መድረክ ከፒ ኤች ኢ እና ኮርሃ ጋር በመተባበር ተከብሯል።

ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም 71 የአገር ውስጥና ዓለም ዐቀፍ ሲቪክ ማኅበራት በአባልነት አቅፎ የያዘ የሲቪክ ማኅበር ነው። ጥምረቱ በሥነ-ሕዝብ ፣ጤና፣ የአካባቢ እና አየር ንብረት ለውጥ፣ ዲሞክራሲ ግንባታ፣ እንዲሁም ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠራ ሲሆን፣ ኹሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና ከተወጡ የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ በመገንዘብ በአጋርነትና በቅንጅት የመሥራትን ፋይዳ በብዙ መልኩ ያረጋገጠ ተቋም ነው። በተለያዩ የውይይት መድረኮች እንዲሁም ሥልጠናዎች የተለያዩ አጀንዳዎች በመቅረጽም ያወያያል።
የሥነ-ሕዝብ ጤና እና አካባቢ ላይ ትኩረቱን በማድረግ እየሠራ የሚገኘው ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም፣ የዘንድሮውን የዓለም ዐቀፍ የሥነ-ሕዝብ ቀን የፌደራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍል የተወከሉ ማኅበረሰቦችን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዓሉን በፓናል ውይይት አክብሯል።

ይህ በዓል እስከ ዛሬ ድረስ በመንግሥት ደረጃ ሲከበር የቆየ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓመት ደግሞ በአጠቃላይ በተፈጠረው አለመረጋጋትና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሌሎች ጉዳዮች በመወጠራቸው በዕለቱ ለማክበር አልተቻለም ነበር። ነገር ግን ሲቪክ ማኅበርሰቡ የሥነ-ሕዝብ ቀን ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም በማለት በቅንጅት መሥራት የሚያስችል ዓላማን ለማሳካት በማሰብ የተከበረ ነው።
ፒ ኤች ኢ ና ኮርሃ በጋራ በመሆን ባሳለፍነው ሳምንት ነሐሴ 27 ቀኑን አክብረዋል።

በየዓመቱ ይህ ቀን ሲከበር የራሱ የሆኑ መሪ ቃላት ያሉት ሲሆን፣ ዘንድሮ ‹‹ማንኛውም ሰው ስለ ሥነ-ሕዝብ አገልግሎትና መረጃ ማግኘት አለበት›› በሚል መሪ ቃል የተከበረ ነው።
በአገር ደረጃ ሲታይ ኢትዮጵያ በቤተሰብ ዕቅድ አጠቃቀም 36 በመቶ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የቤተሰብ ዕቅድ መጠቀም እየፈለጉ መጠቀም ያልቻሉ የአገራችን ሴቶች ቁጥር 22 በመቶ ስለሆነ ያልተሟላ ፍላጎት አለ። ስለዚህ ይህን ያልተሟላ ፍላጎት ለማዳረስ ለመንግሥትና ለሚመለከታቸው አካላት የቤት ሥራ በመስጠት ነው የሥነ-ሕዝብ ቀን የተከበረው ሲሉ አሕመድ ጠቁመዋል። እንደ ፒ ኤች ኢ ያሉ ተቋማት የሚፈጠሩት አጋጣሚዎችን በመጠቀም ሕብረተሰቡ መረጃዎችን ማግኘት መብት እንዳለው ለማስገንዘብ ይሠራሉ።

ፒ ኤች ኢ የምርታማነት እና የሥነ-ሕዝብ ጉዳይ በተመለከተ መረጃና አገልግሎት ማግኘት መብት ነው ብሎ እንደሚያምን የገለጹት አሕመድ፣ ሌሎች የሰብዓዊ መብትን ለመሟገት እንደሚያከብሩት ሁሉ የሥነ-ሕዝብ ቀንን አክብሯል ብለዋል። የሥነ-ሕዝብ ሐሳብን ዕውቅና በመስጠት፣ ቅድሚያ እንዲሆን በማድረግ ለሚመለከታቸውን አካላትና ለመንግሥትን ሐሳብ የመስጠት ተግባራት ማከናወን የፒ ኤች ኢ ዓላማዎች ናቸው። በሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ ሕብረተሰቡን፣ መንግስትን የሚያግዙ የሲቪል ማኅበራት ተቋማት ይህንን ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል በማለት ቀኑ ታስቧል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት እየተጠቀመች ያለው የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ ላለፉት ስድስት አመታት ያልተሻሻለውንና ለ28 ዓመታት ሲተገበር የቆየውን ነው። በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1993 የወጣው የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ እስከ 2015 ድረስ እንዲያገለግል ታቅዶ ቢሆንም፣ ከታቀደለት ዓመት ባለፈ ለረጅም ዓመት ሳይሻሻል ቆይቷል።

የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ መዋቅሮች፣ ቅንጅቶችና አተገባበር በተመለከተ የሚዳስስ መመሪያ ነው። ምን አይነት የሥነ-ሕዝብ መዋቅር ያስፈልጋል? እንዴት ነው መቀናጀት የሚገባው? የሚል እንዲሁም አተገባበር ላይ ጥልቅ አካሄድ ስልት ይዞ የተነሳ ፖሊሲ ነው።
ይህ ፖሊሲ በተፈለገው ደረጃ አልተተገበረም የሚሉት አቶ አሕመድ፣ ካለመተግበሩም በተጨማሪ የአገልግሎት ዘመኑ አልፎበታል ብለዋል። ስለዚህ አሁን ዓለም ያለችበትንና የኢትዮጵያ አዳዲስ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ ፖሊሲ እንዲኖረን ክለሳ መደረግ እንደሚገባው ተነስቷል።

በሥነ-ሕዝብ ላይ ጥናት ያጠኑ ሰዎች፣ ሲቪል ማኅበራት እና የሚመለከታቸው አካላት ይህ ፖሊሲ ክለሳ ተደርጎበት እንደ አዲስ እንዲሠራ ጥያቄ አቅርበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በአገር አቀፍ ደረጃ በታሰበው የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ውስጥ ተካቶ መውጣት አለበት ሲሉ አሕመድ አብራርተዋል። በመቀጠልም ይህን ፖለሲ ወደ ተግባር የሚቀይሩ አካላት በተሻሻለው ፖለሲ ላይ ተመስርተው ሥራዎቻቸውንና ተግባራቸውን እንዲያስፈጽሙ የሚጠይቅ መሆን ይገባዋል ተብሏል።

እስከአሁን አንዳንድ ጅምሮች ቢኖሩም፣ መቼና የት የሚለው በደንብ ባለመገለጹ በትክክል የሚሻሻልበትን ወቅት ማወቅ አይቻልም። መንግሥት ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱ የሚበረታታ ቢሆንም፣ ወደ ተግባራዊነት ለመግባት ምን መደረግ እንደሚገባው ማወቅ ያስፈልጋል። ማሻሻያ ሲደረግ የተወሰኑ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው የሚወስኑት ሳይሆን ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንደ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማኅበራት እና ሌሎች አካላት ውይይት አድርገውበት መውጣት አለበት የሚል ሐሳብ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ እየተመራች ያለችበት ያረጀ ፖሊሲ በመሆኑ ጠንካራ የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ ያስፈልጋታል። ፖሊሲውን ማሻሻል ብቻ ሳይሆን ፖሊሲውን ወደ ተግባር አውርዶ የሚሠራ አካል የለም።

አገሪቷ ላይ ፖሊሲ የማውጣት ምንም ችግር የለም ብለዋል አቶ አሕመድ። አስፈጻሚ አካላት ግን በተለያዩ ሥራዎች የተወጠሩ በመሆናቸው አሠራራቸው ግልጽ አይደለም። ስለዚህ የሚጠበቅባቸውን የአፈጻጸም ሥራ እየሠሩ አይደለም ሲሉ ጠቅሰዋል።
የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ መውጣት ተከትሎ አገሪቷ ላይ ናሽናል ኦፊስ ኦፍ ፖፑሌሽን አስፈጻሚ በመሆን ሲሠራ ቆይቶ ነበር። ተቋሙም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሆኖ እየሠራ ነበር። ፖሊሲው ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች ጋር እንዴት ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባው ሲሠራ ቆይቷል።

በቢሮ ተደራጅቶ የቆየው ይህ ተቋም የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሥር በዳይሬክቶሬት ይመራ ነበር። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳለ ስለማይታወቅ ፖሊሲውን የሚተረጉም ተቋም ያስፈልጋል ሲሉ አንስተዋል።
ይህ ፖሊሲ በሥነ-ሕዝብ ላይ የሚያተኩር በመሆኑ እያንዳንዱ የሌሎች ተቋማት ፖሊሲዎች የሚመሩት በዚህ በኩል መሆን አለበት። እያንዳንዱ ፖሊሲ የሚቀረጹት ለሰዎች ነው የሚሉት አሕመድ፣ ፖሊሲው ደግሞ ሕዝብን በመመሪያ የሚያገለግል መሆን ይገባዋል።
የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ ሁሉንም የአገሪቷን ፖሊሲ የዳሰሰና በተግባር እንዲታዩ የሚያደርግ ነው። ፖሊሲዎች በሙሉ መቀረጽ የሚገባቸው በስነ-ሕዝብ ፖሊሲ ነው።

ፖሊሲዎች ከመውጣታቸው በፊት ለሕዝቡ አሳይቶ ውይይት ለማድረግ የኮሚዩኒቲ ባለሙያዎችና ሲቪል ማኀበራት ትኩረት የሚሰጡ አካላት አሉ። ፒ ኤች ኢ ደግሞ መንግሥት እንደዚህ አይነት ፖሊሲዎችን የሚያወጣ ከሆነ የተለያዩ ውይይቶችን በማድረግ ለፖሊሲው ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦችን በመሰብሰብ ትልቅ ሥራ መሥራት የሚችል እና ከሌሎች የሙያ ማኅበራት ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው።
ለዚህም ደግሞ ግብዓቶችን ማግኘት የሚቻልባቸው መድረኮችና ፎረሞች በማዘጋጀት መንግሥትን የሚያግዝ ድርጅት እንደሆነም አሕመድ ጠቅሰዋል።

ፒ ኤች ኢ በዋናነት እንደዚህ አይነት መድረኮችን በማዘጋጀት የሚታወቅ ሲሆን፣ ሥነ-ሕዝብን በተመለከተ ደግሞ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ፒ ኤች ኢ ስለ ሥነ-ሕዝብ የሚሟገት ተቋም እንደመሆኑ መጠን የሚያመጣውን ተጽዕኖ እንዴት መመልከት እንደሚገባና በጥናቶች እንዴት መካተት እንዳለበት የሚያሳዩ ሥራዎችን ሠርቷል።

የተለያዩ በፒ ኤች ኢ ስር የሚገኙ የልማት ድርጅቶች ፕሮጀክቶቻቸውን በሚተገብሩበት አካባቢ የሥነ-ሕዝብ ሐሳቦችን እንዴት ሕብረተሰቡን ያስተምራሉ በሚሉ ጉዳዮች ላይ በመሥራት ይታወቃል።
ፒ ኤች ኢ ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ክፍላተ አገራት የስነ-ሕዝብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ይሠራል። የተለያዩ መድረኮችንም በማዘጋጀት ማኅበረሰቡ እንዲወያይ ያደርጋል። ድርጅቱ በጋራ ከሚሰራባቸው የመንግሥት ተቋማት አንዱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሆኑን የጠቆሙት አሕመድ፣ በገጠር አካባቢ የጤና ኤክስቴንሽን ሥራዎችን ይሠራል። ፒ ኤች ኢ በሥነ-ሕዝብ ዙሪያ ከሠራቸው ሥራዎች መካከል ሞዴል ቤተሰብ እና ሜን ሻምፒዮን የሚባሉ ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ።

ሞዴል ቤተሠብ መፍጠር ማለት ጤናውን የሚጠብቅ፣ አካባቢውን የሚያጸዳ፣ የቤተሠብ ዕቅድ የሚጠቀም፣ እንዲሁም በግብርና ዘርፍ በመሠማራትና የጓሮ አትክልት በመጠቀም አካባቢን ለሚያለማ ቤተሠብን ማበረታቻ በመስጠት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑበት ተግባር ነው። በዚህም አመርቂ ውጤት ማግኘት የቻለ ግብረ-ሠናይ ድርጅት ነው ሲሉ አሕመድ ገልጸዋል።

ሌላኛው ሜን ሻምፒዮን የተሰኘው ፕሮጀክት ደግሞ ወንዶች ሚስቶቻቸውን በቤት ውስጥ ሥራ እንዲያግዙ እና የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያበረታታ ሲሆን፣ ይህን ዓይነት ሥራ ባህላችንን ከመቀየር የሚጀምር ሲሆን፣ ፕሮጀክቱም ወንዶች ይህን እንዲሠሩ የሚያበረታታ መሆኑን አሕመድ ጠቅሰዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!