የእለት ዜና

የ”እንደራደር” አንድምታ

ሠሞኑን መነጋገሪያ ከሆኑ አንኳር ጉዳዮች መካከል በተወሰኑ ግለሰቦች የቀረበ የድርድር መልዕክት ብዙዎችን አነጋግሯል። በአሸባሪነት የተፈረጀ ቡድንን እንዴት ከመንግሥት ጋር ይደራደር ትላላችሁ እያሉ ብዙዎች የተቹት ሲሆን፣ ሠላም እንዲወርድ በሚል ድርድር አይታሰብም ያሉም በርካቶች ናቸው።

በተለያዩ አካላት በተለይም በውጭ ኃይሎች ተመሳሳይ ጥያቄ መቅረብ ከጀመረ የቆየ ቢሆንም፣ ከሠሞኑ እንደአዲስ መሰማቱ መቼቱን ያልጠበቀ አስብሎታል። ይህ ሁሉ ግፍ ሳይፈጸምና እንዲያ ሽማግሌዎች ሲመላለሱ ሳይናገር የከረመ አሁን ደርሶ አስታራቂ ልሁን ማለት በቁስል ላይ እንጨት መስደድ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አዲስ ማቁሰልም ነው ሲሉ ሐሳቡን በኹለቱም ወገን ያሉ ተፋላሚ ወገኖች ሲተቹት ተሰምተዋል።

እያሸነፈ ያለ አካል ድርድርን ሲፈልግ የትም ቢሆን ተሰምቶ አይወቅም ያሉ አስተያየታቸውን በጉዳዩ ላይ የሰጡ ኢትዮጵያውያን፣ ድርድሩ የተጠየቀበት ጊዜ የተናጋሪውን ውግንና የሚያሳይ ተግባር ስለሆነ ማን የማን ደጋፊ እንደሆነ ይለይበታል ሲሉ ተናግረዋል። በሌላ በኩል፣ ብቸኛው ሠላም ማምጫ መንገድ ድርድር ነው በማለታችን ከኹለቱም ወገን ወቀሳ እየደረሰብን ነው ብለው ስሞታቸውን ሕዝብ እንዲያውቅላቸው ያደረጉም ነበሩ።

የኃይማኖት ተቋማት ራሳቸው እየተጎዱም ቢሆን ሠላም እንዲወርድ ፍላጎት እንዳላቸው ይነገራል። በተለይ ድርድርን በተመለከተ መንግሥት ነኝ ያለ አካልን ሥልጣን የሚቀንስና በጠላትነት ከተፈረጀ ጋር ለመታረቅ መሞከር ተቀባይነታቸውን ስለሚያሳንስባቸው ይጠነቀቃሉ ይባላል። ያም ሆነ ይህ፣ ዓመት ሊሆነው ጥቂት ጊዜ የቀረውን የሰሜኑን ጦርነት ለማስቆም ኹሉም ባመነበት መንገድ እየተጓዘ እንደመሆኑ መቋጫው በቅርብ ያለ አይመስልም የሚሉ ተበራክተዋል።

በሌላ በኩል፣ ጦርነቱ ያስከተለውን ጥፋት እየጠቀሱ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ እንዴት ድርድር ተብሎ በሠላም መኖር ይቻላል እያሉ ሐሳቡን ያመጡትን ጠብእርግፍ አድርገው ያጣጣሉ ብዙ ናቸው። ሠላም መምጣቱን ኹሉም ቢፈልገውም፣ በዚህ ሁኔታ ግን መሆን እንደሌለበት ያስረዳሉ። ሲያሸንፉ በለው፣ ሲሸነፉ እንደራደር የልጅነት ጨዋታ ይመስላል እያሉ በነገሩ በመሳለቅ፣ በጦርነቱ ያለቁት አጥንት ይወጋናል፤ ሳናሸንፍ ከጠላት መነጋገር ፈፅሞ የሚታሰብ አይደለም ያሉ ይበረክታሉ።
ዝነኛዋ አቀንቃኝ ማሪቱ ለገሠ “ዘራፌዋ” በሚለው ዜማዋ እንዳለችው፣

“ዘራፍ እወዳለሁ ሠላምም አልጠላ፣
የዕርቀ ሠላም ፍሬ የፍቅር መሃላ፤
ዘራፍ ዘራፍ በሉ ለሠላም ለፍቅር፣
ለዚህች አንዲት እናት ለዚህች አንዲት ሀገር።
ሠላም ሠላም ቢሉ፣ ሠላም ለአፍ ይሞቃል፣
በትግል ያልተገኘ ተጦርም ይልቃል፣
የሽንፈት ሠላም ግን ከሽብር ይከፋል።”


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!