የእለት ዜና

የኢትዮጵያ ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እና የሚታዩ ምቹ ሁኔታዎች

በአገሮችም ሆነ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በጣም ውስን እና ዕክሎች የበዙበት እንደሆነ ቢታወቅም፣ ባለፍት 10 አመታት ውስጥ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ሆነ በኢትዮጵያ በርካታ ሴቶች ወደ ፖለቲካ ዘርፉ የመጡበት፣ ሴቶች ከተለያዩ የአመራር ደረጃዎች እስከ አገር መምራት የደረሱበት፣ እንዲሁም በተለያዩ አደረጃጀቶች እና በሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች የሴቶችን እኩል ተሳታፊነትን እና ተጠቃሚነትን የሚያንጸባርቁበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው። ይህ የሚያስደስት እና የሥርዓተ-ጾታን እኩልነት ለማሳካት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል።

ዓለም ዐቀፍ እና አገር ዐቀፍ መንግሥታዊ የሆኑ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማጎልበት ትኩረት መስጠታቸው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል። በመሆኑም Action For Social Development And Environmental Protection Organization (ASDEPO) ከ international Republican Institute(IRI) ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የተለያዩ የማሕበረሰብ ውይይቶች በማድረግ /public dialogue/፣ የተለያዩ የሚዲያ/የራዲዮ እና የቴሊቭዥን፣ በማኀበራዊ ድረ-ገጾ ውይይቶችን በማዘጋጀት ማኅበረሰቡ ስለ ፖለቲካ ተሳትፎ አስፈላጊነት ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል።

ASDEPO፣ 2006 ዓ.ም. የተቋቋመ አገር በቀል ግብረ-ሠናይ ድርጅት ሲሆን፣ የተለያዩ የልማት(development) እና የሰብዓዊ ሥራዎችን በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ እና ትግራይ ክልሎች ውስጥ እየሠራ ይገኛል። ASDEPO በተለይ የሴቶች እና ሕፃናት ዕድገት ላይ የበለጠ ትኩረት ስለሚሰጥ የሴቶች ወደ አመራርነት መምጣት እና በፖለቲካው መሳተፍ አጠቃላይ የሥርዓተ-ጾታን እኩልነት ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደሚያሳልጥ፣ እንዲሁም በሕግ አውጭው እና ሕግ አስፈጻሚው መካከል ያለውን የአፈጻጸም ተግዳሮትን እንደሚያቃልል ስለሚያምን የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ይሰራል።

ሴቶች ከወንዶች እኩል በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካ ተሳታፊ እንዳይሆኑ እንቅፋት የሆኑትን ባህላዊ እና አመለካከታዊ ማኀበረሰብ ሠራሽ ተግዳሮቶች ከዚህ በፊት የተገለጹ ቢሆንም፣ በዚህ ዕትም ደግሞ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚስተዋሉ መልካም አጋጣሚዎች፣ እድሎችን እንዲሁም የሴቶችን ተሳትፎ ለማበረታታት አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን እንመለከታለን። እየተስተዋሉ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን፣ ከፖሊሲ፣ ከአስተዳደር አካታችነት እና ድጋፍ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ግንዛቤ አንጻር ሊታዩ ይችላሉ። ከዚህ በታች እንደሚከተለው ተገልፀዋል።

1. አገራዊ ፖሊሲ እና አቅጣጫ፡ አገራዊ እና ዓለም ዐቀፋዊ ሕጎች፣ ስምምነቶች እና ፖሊሲዎችን ስንመለከት በኢትዮጲያ ከ 10 በላይ የሴቶችን ዕኩልነት እና ተጠቃሚነት የሚገልጹ ሥምምነቶች እና ፖሊሲዎች መኖራቸው እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት ምቹ ሁኔታ ይፈጥርልናል።

2. የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እየጨመረ መምጣት፡ ካለፍት 10-20 ዓመታት ጋር ሲወዳደር የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ዕየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ ሴቶች በየደረጃው በሚካሄዱ የፖለቲካ ምርጫዎች ላይ በተወዳዳሪነት፣ በመራጭነት እና በምርጫ ሒደት በታዛቢነት ጉልህ ተሳትፎ ማድረጋቸው፣ በሴቶች ላይ ለመሳተፍ የመነሳሳት ፍላጎት ይቀሰቅሳል።

ዶ/ር አዲስ አለም አባቴነህ፣ የአ.አ. ዮንቨርስቲ መምህር እና በ2013 ምርጫ የብልጽግና የፓርላማ ተወካይ
“የሴቶችን ተሳትፎ በፖለቲካው ዘርፍ ለመጨመር የእርስዎ አስተዋጽኦ ምን ሊሆን ይችላል” ተብለው ቃለ-መጠየቅ በሚደረግላቸው ወቅት
“ እኔ በፖለቲካው ዘርፍ ውስጥ ልምድ የለኝም ነበር፤ ፖለቲካም እጠላ ነበር፤ ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ፖለቲካ ማለት ለግልም፣ ለማኅበረሰብም እንዲሁም ለአገርም ያለውን ጉልህ አስተዋጽኦ ተረድቸ ከመምህርነት ወደ ፖለቲካው ዘርፍ መምጣቴ ሴቶችን የመሳተፍ ፍላጎታቸውን እንዲጨምር ያደርጋል። ምሳሌ ሆኜ በመገኘት እና የማደርገው ጉልህ አስተዋጽኦ በሴቶች የመሳተፍ ውሳኔ ላይ የጎላ ሚና እንዲኖር አደርጋለሁ::”

እውነት ነው ዶ/ር አዲስ አለም አባቴነህ እንደተናገሩት፣ ብዙዎቻችን የሚታይ ነገር እንፈልጋለን። ምሳሌ የሆኑ ጠንካራ ሴቶችን ማየት እንሻለን። ከሥርዓተ-ጾታ ጋር የነበረውን የተዛባ አስተሳሰብ በመቀየር ይቻላል የሚሉ ሰዎችን ማየት ውስጣዊ የመለወጥ ፍላጎታችንን እውን ሊሆን እንደሚችል ያረጋግጥልናል። ስለዚህ በ2013 ዓ.ም. በርከት ያሉ ሴቶች በኹሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ መሳተፋቸው የሴቶችን በፖለቲካው ዘርፍ የተሻለ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚፈጥረው ተነሳሽነትን የጎላ ስለሚያደርገው ይህ ትልቅ መልካም አጋጣሚ ነው እንላለን።

3. በማኅበረሰቡ አመለካከት፡- በአሁኑ ጊዜ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ ያለው የማኅበረሰብ ግንዛቤ እየጨመረ መምጣቱ እና ስለ ሴቶች ፖለቲካዊ እና የአመራርነት ሚና ላይ አዎንታዊ አመለካከቶች መጎልበቱ ከአሁን በፊት እንቅፋት ሆነው በየደረጃው የሚታዩት እና ሴቶችን ወደ አመራርነት እንዳይመጡ የሚያደርጉ ተግዳሮቶች እንዲቀረፉ ያደርጋል።
ASDEPO ከማኅበረሰብ ተቋማት ማለትም ከዕድር አመራሮች፣ ከኃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከተለያዩ ማኅበራት ተወክለው ከመጡ የማኅበረሰብ አመራሮች ጋር “ሴቶች በአመራርነት እና የማኅበረሰብ ተቋማት ሚና” በሚል ባደረገው ውይይት ላይ ከማኅበረሰብ ተቋማት እና በማኅበረሰቡ ላይ የነበሩ የተዛባ ሴቶችን ወደ አመራርነት እንዳይመጡ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም ሴቶች አሁን ያሉበት ደረጃ ከወንዶች ባልተናነሰ መልኩ የአመራር ሚናን ለመወጣት ብቁ እንደሆኑ ገልጸዋል። ለዚህም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የማኅበረሰብ ተቋማት ጉልህ ሚና ስላላቸው በየመጡበት ተቋም ሴቶች ወደ አመራር እንዲመጡ እንደሚደግፍ እና ሕገ-ደንባቸውን እንደሚያሻሽሉ ቃል ገብተዋል።

ከዚህ በፊት በሴቶች ላይ የነበሩ የተዛቡ አመለካከቶች እና ጾታን መሠረት ያደረጉ የሥራ ክፍፍሎች ላይ ማኅበረሰቡ ላይ ለውጥ መታየቱ የሚስተዋሉ ዕንቅፋቶችን ከመቅረፍ አልፎ ሴቶች የአመራርነትን ሚና በማኅበረሰብ ተቋማት ደረጃ፣ ለምሳሌ በወረዳ ፣ በአደረጃጀት፣ በዕድር እና በኃይማኖት ተቋማት እንዲለማመዱ እና ወደ ከፍ ያለ አገራዊ የአመራር ቦታዎች ለመምራት ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጥርላቸው ያደርጋል።፡

4. የመገናኛ ብዙኃን ለሴቶች ፖለቲካዊ እና ሕዝባዊ አስተዳደር ተሳትፎ ለማጉላት አዎንታዊ ሚና መጫወት መጀመራቸው እና በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ላይ መዘገባቸው ማኅበረሰቡ የፖለቲካ ግንዛቤው እንዲጨምር ያደርጋል።
5. የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት መስጠታቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ ሴቶች በፖለቲካው መሳተፋቸው የሚኖረውን አገራዊ ፋይዳ እንዲገነዘቡ ያደርጋል፤ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ይጨምራል።

ASDEPO በአገራችን ላይ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለመጨመር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች በማጠናከር እና በመደገፍ ሴቶች ወደ ከፍተኛ የሥልጣን ዕርከን እንዲደርሱና ውሳኔ መስጠት ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ ሥራ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርቧል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!