የእለት ዜና

የተፈናቃዮች የበዓል ውሎ

በአገራችን ከሚከበሩ በዓላት መካከል ዓመቱን ጠብቆ፣ በዕጸዋት ልምላሜና በአደይ አበባ ውብ ፍካት ታጅቦ፣ አሮጌውን ዓመት አሰናብቶ፣ አዲስ ዘመን እና አዲስ ብሩህ ተስፋ ሰንቆ ብቅ የሚለው የዕንቁጣጣሽ ወይም የዘመን መለወጫ በዓል አንዱ ነው።
የዘመን መለወጫ በዓል አሮጌው ዓመት ተሸኝቶ ለአዲስ ዓመት አቀባባል የሚደረግበት፣ አዲስ ሕይወት የሚጀመርበት፣ አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት፣ ድክመቶች ተቀርፈው ዕድገት የሚታቀድበት፣ ፍቅር፣ መከባበር፣ አንድነት የሚሰበክበት፣ አዲስ የዘመን ምዕራፍ ጅማሮ መሆኑን ኢትዮጵያውያን ይስማሙበታል።

ኢትዮጵያ ከማንም አገር ያልወሰደችው፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ወቅቱን ጠብቆ የሚከወን እና በትውልድ ቅብብል ሕልውናው ሥር የሰደደ የራሷ የሆነ የበዓል አከባባር ባህልና ትውፊት እንዳላት ትውልድ በተግባር ሲመሰክር ይታያል።
የዕንቁጣጣሽ በዓል በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የተለያዩ ሰዎች የሚገናኙበት፣ ዜጎች ተሰባስበው የጳጉሜንን ውኃ በፍቅር የሚጸበሉበት ከመሆኑም ባሻገር፣ ሁሉም አቅሙ እንደፈቀደለት መጠን በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣ ወይም ዶሮ አርዶ ወይም ደግሞ ኪሎ ሥጋ ቀቅሎና ጠላ ጠምቆ ’’ብሉልኝ፣ ጠጡልኝ” የሚልበትና ማዕዱን በፍቅር የሚቋደስበት ዓመታዊ በዓል ነው።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በዓሉን የአካባቢው ማኅበረሰብ በተለመደው መልኩ እንዳያከብረው ተገዷል። በ2014 የሚከበረውን የዕንቁጣጣሽ በዓል ሰሜን ወሎ አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ’’በመሰባሰብ ፈንታ ተበትነን፣ በመቦረቅ ፈንታ አዝነን’’ ልናሳልፍ ነው በሚል የሐዘን ድባብ ውስጥ እንደገቡ ሰምተናል።

ከ 300ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከተለያዩ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ቤታቸውን ለቀው በመሰደድ በደሴና ኮምቦልቻ እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ስትዘግብ መቆየቷ ይታወሳል።
ከእነዚህ ተፈናቃዮች መካከል 110ሺሕ የሚሆኑት ዜጎች በደሴና ኮምቦልቻ ከተማ ለመጠለያነት በተዘጋጁ 16 ጣቢያዎች ሲኖሩ፣ ከ3 ሺሕ በላይ የሚሆኑ እማወራወችና አባውራዎች በመዲናችን አዲስ አበባ ይገኛሉ። ቀሪዎቹ በደሴና ኮምቦልቻ ቤት ተከራይተው እየኖሩ መሆናቸውን ለተፈናቃዮች ዕርዳታ በማድረግ ላይ የሚገኘውና በአካባቢው ተወላጆች የተቋቋመው ኮሚቴ አባላት ይናገራሉ።

“ቤታችን እየናፈቀን በዓሉን በስደትና በጭንቀት ልናሳልፈው ነው’’ የሚሉት ሰዎች፣ በዋነኛነት ለዚህ ችግር የዳረጋቸው ደግሞ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት የሰነዘረውና የሚሰነዝረውን ጥቃት እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
አዲስ ማለዳ የዕንቁጣጣሽ በዓልን በማስመልከት ከተለያዩ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴ፣ በኮምቦልቻና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሰዎች ጋር ቆይታ አድርጋለች።

ኤፍሬም ከበደ ይባላል። ተወልዶ ያደገው የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወልዲያ ከተማ ልዩ ቦታው አዳጎ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን፣ ሞት አባቱን በጨቅላነት ዕድሜው ስለነጠቀው ቤተሰብን የማሥተዳደር ኃላፊነት ተጥሎበት ከትምህርት ገበታው ጎን በጎን በስልክ ጥገና የሥራ መስክ በመሰማራት ሕይወትን በመምራት ዘመናትን ሸኝቷል።

ኤፍሬም በአባቱ እግር ተተክቶ ቤተሰብን የማሥተዳደር ኃላፊነቱን ለመወጣት እያንዳንዱን ቀን በፕሮግራም በመከፋፈል ደፋ ቀና ብሎ መሥራቱን ተያይዞታል።
አጋሯን በሞት የተነጠቀችው እናቱ እንዳይከፋት ብሎም የእሷ የደስታ ምንጭ ለመሆን የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ ይናገራል። ሌሊት በጥናት፣ ቀን በሞባይል ጥገና ተግባር ተሰማርቶ የሚገኘው ኤፍሬም፣ የእርሻ ወቅት ሲደርስ ከትምህርት ገበታው ጎን ለጎን በሬዎቹን ይዞ ወደ እርሻ ቦታ ማቅናቱም ወቅቱን የጠበቀ ተግባሩ ነበር። በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ አልፎ በሚያገኘው ገቢ ታላላቅ ዓመታዊ በዓላት ሲመጡ ለበዓላቱ የሚያስፈልገውን እርድ አከናውኖ እና ቤተሰቡን አልብሶ እነሱ በደስታ ሲቦርቁ ማየት የትየለሌ እፎይታን ይሰጠዋል።
ኤፍሬም የክረምት ዕረፍቱን መስዕዋት በማድረግ፣ የሞባይል ጥገና ሙያውን አሻሽሎ ለመመለስ ወደ ኮምቦልቻ ከተማ ጎራ ብሎ ነበር። በወቅቱ በፖለቲካ አለመረረጋጋት የሚከሰተው ችግር በሚዲያ ተቋማት ሲዘገብ የሚሰማው ኤፍሬም፣ ጧት ማታ እየደወለ ቤተሰብ ጋር መገናኘት የዕለት ተዕለት ተግባሩ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል።

አሁን ላይ ነገሮች ተቀይረውበታል። በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን የወልዲያ ከተማን መቆጣጠሩን ተከትሎ መንገድ በመዘጋቱና ኔትወርክ በመቋረጡ፣ የቤተሰቡን ደኅንነት ለማወቅ ተቸግሯል። በየሰዓቱ ስልክ መደዋወሉን ባያቋርጥም፣ “ቴሌፎኑ ለጊዘው ጥሪ አይቀበልም’’ የሚለውን ድምጽ ከመስማት የዘለለ ነገር ማግኘት የሕልም እንጀራ ሁኖበታል።

ኤፍሬም ለጊዜው የያዛትን ብር የቤት ኪራይና የሥልጠና ክፍያ ከቀለብ ጋር በመተባባር አመናምነው ጨርሰዋታል። ይህ ሁኔታ በኮምቦልቻ ከተማ ለተፈናቃዮች በተዘጋጀው ጊዜያዊ መጠለያ እንዲጠጋም ሳያስገድደውም አልቀረም።
አሁን ላይ ከተፈናቃዮች ጋር ተቀላቅሎ ድጋፍ አድራጊ ድርጀቶችና የአካባቢው ማኅበረሰብ በሚያደርጉት ዕርዳታ ቀናትን እየገፋ ይገኛል።
ኤፍሬም አሁን አሁን ባህሪው እንደተቀየረ ይናገራል። ቤተሰቦቹ ያሉበት ሁኔታ ጨዋታውን ሁሉ አጥፍቶ ፍዝዝ ድንግዝ በሐሳብ ጭልጥ ያደርገዋል።

ኤፍሬም በስደት ቢሆንም እንኳ እጅ እግሩን አጣጥፎ መቀመጥን አልመረጠም። ችግርን ለመቋቋም በማንኛውም የሥራ መስክ መሳተፍ እንዳለበት ቤተሰብን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተረዳው ወጣቱ፣ በቀን ሥራ ተሰማርቷል።
በሥራ ላይ ቢሆንም እንኳ የበዓሉ መድረስ ትውስ ሲለው ከቤተሰቦቹ መለየቱ በጭንቀት ሰመመን ውስጥ ይከተዋል። በማኅበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው የዕለት ተዕለት ወሬ ቤተሰቡን ለማግኘት ያለውን ጭላንጭል ተስፋ እያዳከመው ቢመጣም፣ ስልክ የመደወል ተግባሩ እንዳልቀነሰ ይናገራል።

ኤፍሬም ከበደ በዓሉን ከቤተሰቡ ጋር የማሳለፍ ተስፋው እየተሟጠጠ ቢመጣም፣ ድምጻቸውን ለመስማት በተደጋጋሚ ስልክ መደወሉን ግን ተያይዞታል። ነገር ግን ሙከራው ያተረፈለት ውጤት እስካሁን የለም። አሁንም “ለጊዜው ጥሪ አይቀበልም’’ የሚለው ቃል የቤተሰቡን ድምጽ ለመስማት በተጠንቀቅ በሚጠባበቀው ጆሮው አልፎ በውስጡ ያለውን ጭላንጭል ደስታ ሲያጨልመው ይሰማዋል።

ሕይወትን እንደዚህ እየገፋ የሚገኘው ኤፍሬም፣ ኔትወርክ በእርሱ ላይ አድማ የያዘ እየመሰለው መጥቷል። ቤተሰብ ያለበትን ሁኔታ አለማወቁ፣ ናፍቆቱና ዕንቁጣጣሽን በስደት ማሳለፉ ቀላል የማይባል የሥነ ልቦና ስብራትብ እንዳስከተለበት ያምናል። ቤተሰቦቻችን ያሉበትን ሁኔታ እናውቅ ዘንድ የሚመለከተው አካል፣ መንግስትን ጨምሮ፣ አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል ሲል ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጸው።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት በደሴ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃይ እናት በበኩላቸው፣ “ድሮ ጦርነት ቢኖር እንኳ የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ይዋጋሉ እንጅ የአካባቢው ኗሪ ቤትህን ልቀቅ ተብሎ ለዘራፊ እንዲሰጥ ተገዶ አያውቅም። አሁን ላይ ግን በክረምት ቤታችንን ለቀን በዓሉን በልመና ልናሳልፈው ነው፤ ሲቀጥል ልጆቻችን የት እንዳሉ አናውቅም። መንግስት ሊደርስልን ይገባል’’ ነው ያሉት።

ሌላኛው በመዲናችን የሚገኘው ንጉስ አየነ የተባለው ወጣት “ቤተሰቦቼ እንዴት እንደሆኑ አላውቅም። በዓልን ከቤተሰብ ተለይቶ መዋል ከምለው በላይ ይደብራል፤ በዛ ላይ የትስ ይዋላል? አሁንስ ቤተሰቦቼን የማገኝበት ቀን በጣም ናፍቆኛል’’ በማለት ነው የተናገረው።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ከሥነ ልቦና ምሁራን ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፤ ምሁራኑም ሐሳባቸውን አንደሚከተለው አብራርተዋል።

እንኳን በበዓል ወቅት በሌላኛው ቀንም ቢሆን ሰው ከቤቱ ሲፈናቀል በሚያጣቸው ብዙ ነገሮች ጭንቀት ውስጥ ይገባል ያሉት የሥነ ልቦና ባለሙያው ሙዘየን ጀማል ናቸው። በተለይም በዓላትን ከቤት ተፈናቅሎ መዋል “አሁን እቤቴ ብሆን እንደዚህ አደርግ ነበር?’’ የሚል ቁጭትን ስለሚያጭር፣ አእምሮ በከፍተኛ ጭንቀት ይወጠራል። ጭንቀት ደግሞ ለአእምሮ ሕመም ከሚያጋልጡ መንስኤዎች አንዱ ነው በማለት ነው የገለጹት።

ሰዎች በግጭት ምክንያት ሲፈናቀሉ በመንገድ ላይ የሚገጥሟቸው የደም መፍሰስ፣ የመውደቅ፣ አገር ሲወድም የማየት ክስተቶች ለከፍተኛ ጭንቀት ይዳርጓቸዋል። በበዓል ጊዜ ከተለመደው በተቃራኒ ከቤተሰብ ጋር ተለያይቶ መዋል፣ በዓሉን የሚያሳልፉበት መጠለያም ሆነ ገንዘብ ማጣት ደግሞ ሌላ ለመቋቋም የሚከብድ ጭንቀት እንደሚያስከትልም ሙዘየን አብራርተዋል።

“መከራ ሲገጥም የመጨነቅ ውጤቱ መፍትሔ ሳይሆን እራስን ማውጣት ወደማይችሉበት አረንቋ ውስጥ መክተት ነው’’ የሚሉት የሥነ-ልቦና ባለሙያው፣ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችሉ መፍትሔዎችንም ጠቁመዋል።
የሚሰማውና የሚስተዋለው ነገር ክፉ ቢሆንም፣ ክፍውን ወደጎን የመተው ልምድን በማዳበር መልካም መልካሙን ነገር በተደጋጋሚ ማሰብ የመጀመሪያውና ዋነኛው መፍትሔ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ይኸውም አሁን “ምን ተፈጥሮ ይሆን? ለምን እንደዚህ ሆነ? ደብሮኛል!” የሚሉ ጭንቀትን የሚያባባሱ ነገሮች የአእምሮን በር ሲያንኳኩ አሜን ብሎ ተቀብሎ የጭንቀት ምርኮኛ ከመሆን ይልቅ “ያልፋል፤ ያጋጥማል፤ ይሁን ለበጎ ነው፤ መሆን ያለበት ይሆናል፤ እርግጠኛ ነኝ ምንም አይፈጠርም” የሚሉ መልካም ሐሳቦችን በመተካት የሚከወን መሆኑን ሙዘየን አብራርተዋል።

ኹለተኛው የድብርት ማስወገጃ መፍትሔ የድብርቱን መነሻ ማወቅና የሚቻል ከሆነ የታጣውን ነገር ለመተካት መሞከር ነው። ይህ ካልሆነ ደግሞ በጥልቅ ጸሎት ከፈጣሪ ጋር መቆራኘት አማራጭ የሌለው ተመራጭ መፍትሔ ነው ይላሉ።
ሙዘየን የታጣዉን ነገር መተካት የሚለውን ቃልም በዓሉን በስደት ለሚያሳልፉ ሰዎች መንግሥትም ሆነ ማኅበረሰቡ ተጋግዞና ተሰባስቦ ያለውን በማካፈል ከድብርት እንዲወጡ ማድረግ መቻል ይኖርበታል ብለው ነው የሚያምኑት።
ከዚህም በተጨማሪ ተፈናቃዮች ባሉበት አካባቢ ተገኝቶ የሥነ-ልቦና ምክር መለገስ ቀላል የማይባል መፍትሔን ሊያመጣ እንደሚችል ይናገራሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!