የእለት ዜና

በበዓላት ወቅት የሚስተዋለው የትራንስፖርት ችግር

Views: 139

ቀን ቀናትን እየተካ፣ ወርም ለተረኛው ፈቀቅ በማለት ብዙ ወራት ተቆጥረው አሮጌው ዘመን ተራውን ለአዲሱ በመስጠት እነሆ አዲስ ዘመን ሆነ መስከረምም ጠባ። “መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ” በሚለው ኢትዮጵያዊ ባህል፣ በዓላት ሲመጡ የአዲስ ዓመት መባቻ ሲሆን ዘመድ መጠየቅ፣ ከቤተሰብ ጋር በመሆን በዓል ማሳለፍ፣ በዓላትን አስመልክቶ የሚዜሙ የልጆች ዘፈኖች መስማት እና የበዓል ስጦታዎች መለዋወጥ፣ ጨዋታዎች መጫዎት፣ የአዲስ አመት መልካም ምኞት መግለጫዎች መቀያየር እንዲሁም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የተለመደ ተግባር ነው።

ክረምት አልቆ መስከረም ሲጠባ የጸደይ ወራትን ተከትለዉ አበቦች ሲፈነዱ፣ ሰዎች በአዲስ ተስፋ መጭውን ጊዜያቸውን ማለማቸው እና ኹሉም ነገር በአዲስ የተስፋ ጅማሮ የሚወጠንበትን አዲሱን ዘመን በማስመልከት ኹሉም በያለበት መሯሯጡ የማይቀር ነው። ዓመት በዓል በራሱ የሚያመጣው ድባብ፣ ደስታ እና የተስፋ ስንቅ እንዳለ ሆኖ፣ በየመንገዶቹ የምናያቸው እና አዲሱን ዘመን አስመልክቶ የሚመጡ ልዩ ልዩ ኹነቶች፣ በዓሉን ተተርሰው የምናገኛቸው ዕቃዎች በዓል በዓል የሚሸቱበት እና ገበያዎች ሁሉ የሚደምቁበት ነው አዲስ ዓመት።

ታዲያ ይህን የአዲስ ዓመት በዓል ግማሹ ከቤተሰብ ጋር በመሆን እና ቤተሰብ በመጠየቅ፣ ሌላው ደግሞ ከጓደኞቹ ጋር በመገናኘት፣ እንዲሁም አንዳንዱ ደግሞ ባለበት አካባቢ ሆኖ በተለመደ ቅኝት ያሳልፈዋል። በዓልን ለማክበር በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ኹሌም ከማይጠፉ ተግባራት መካከል የትራንስፖርት ጉዳይ አንዱ ነው። ሰዎች እንኳንስ ዘመን ተለውጦ በአዘቦት ቀንም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሳቸው አይቀርም። ታዲያ ሰዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሳቸው የተለመደ ከሆነ ምን ይህን በዓል አስከትሎ የሚመጣውን ወቅት ልዩ አደረገው ቢባል፣ በዚህ ወቅት በተለይም በዓላትን አስመልክቶ የሚኖረው የመንገደኛ ቁጥር ከወትሮው በተለየ የበዛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የትራንስፖርት መጨናነቅ እና የዋጋው ዉድነት ስለመሆኑ ይነገራል።

በተለይም ወቅቱ አዲስ ዓመት በመሆኑ በዚህ በዘመን መለወጫ ሰዎች ከየአሉበት አካባቢ ሰብሠብ ብለው በዓሉን ለማክበር መነሳታቸው አየቀርም። ታዲያ ይህ በዓልን ከቤተ ዘመድ ጋር ለማክበር የሚያደርጉት ጉዞ ግን እንዲህ እንደ ወትሮው ቀላል አይደለም።
እንደ ዛሬው ኢትዮጵያ ችግር ላይ ባልነበረችበት እና የኑሮ ውድነቱ ጣራ ባልነካበት ጊዜ በዓላትን ተከትሎ የሚመጣው የትራንስፖርት ችግር እምብዛም ትኩረት ሲሰጠው አይስተዋልም። መንገደኛውም ቢሆን ምሬቱን እና ችግሩን በሆዱ አምቆ በመያዝ ካሰበው ቦታ ለመድረስ እና ከቤተሰብ ጋር በዓልን ለመዋል ያለውን ተስፋ ሙሉ ለማድረግ የቻለውን ያደርጋል እንጂ “የመንግሥት ያለህ” ብሎ ሲጮህ አይሰማም።

አዲስ ዓመት መሆኑን ተከትሎ የትራንስፖርት መጨናነቅ እንደሚያጋጥም ይነገራል። በአዲስ አበባ ከሚኖሩት መካከል 42 በመቶ ያህሉ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ታዲያ እነዚህ የከተማዋ ነዋሪዎች በዓላትን ምክንያት በማድረግ ወደየትውልድ ቀያቸው ጎራ በማለት ከቤተሰብ ጋር ማሳለፋቸው የተለመደ ሆኗል። ነገር ግን በዚህ በዓልን ከቤተሰብ ጋር ለማሳለፍ በሚደረገው ጉዞ የትራንስፖርት ችግር አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ ይነገራል።

በተለይም በአዲስ ዓመት የተጓዦች ቁጥር ስለሚጨምር ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት እጥረት እና መጨናነቅ እንደሚያጋጥም ይታወቃል። ከዚያም አልፎ ከተለመደው መደበኛ ታሪፍ በላይ ለመክፈል እንደሚገደዱ ተጓዦች ይናገራሉ። የትራንስፖርት መጨናነቅ፣ የታሪፍ ጭማሪ፣ እንዲሁም በአሰቡበት ጊዜ እና ሰዓት ለመሄድ አለመቻል ከበዓሉ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ችግሮች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው።

ህሊና ትባላለች፤ በዓልን ከቤተሰቦቿ ጋር ለማሳለፍ በማሰብ የጉዞ ትኬት ለመቁረጥ ወደ አውቶብስ ትኬት መቁረጫ ጎራ ማለቷም አልቀረም። ህሊና ወደ ሻሸመኔ የሚያደርሳትን የአውቶብስ ትኬት ለማግኘት ብዙ እንደተቸገረች ትናገራለች። በየበዓሉ ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ሻሸመኔ እንደምትሄድ በመጥቀስ በዓልን ከቤተሰብ ጋር ለማሳለፍ ትራንስፖርት የምታገኝበት መንገድ ግን አሰልቺ እንደሚሆንባት ትናገራለች። በተለይ በትኬት መቁረጫው አካባቢ የኮሚሽን ሥራ የሚሠሩ ልጆች ቀድመው ትኬቱን በመግዛት እስከ 200 መቶ ብር ድረስ አትርፈው ነው የሚሸጡልን ትላለች። ይህ እንዳይሆን ግን ቢያንስ ከሳምንት በፊት መቁረጥ ቢኖርብኝም አንዳነደ ጊዜ ከሥራ ጫና ጋር በተያያዘ ይህን ማድረግ ይረሳል በማለት አሁን ያለውን የትራንስፖርት ችግር ትገልፃለች።

በዓሉን ደብረ-ማርቆስ ከሚገኙ ቤተሰቦቹ ጋር ማሳለፍ ፈልጎ ነገር ግን ትኬት ከሳምንት በፊት እንዳለቀ እና ኹሉም አውቶብሶች ሙሉ እንደሆኑ ተነግሮኝ አማራጭ እየፈለኩ ነው የሚለው እስጢፋኖስ አካባቢ በሚገኘው የትኬት መቁረጫ ያገኘነው ሰለሞን አለበል የተባለ ተጓዥ ነው። ሰለሞን የአውቶብስ ትኬት ማግኘት በተለይ በአሁኑ ወቅት ካለዉ የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ በጣም ከባድ እንደሆነበት እና ምናልባት አማራጭ ካላገኘ ሊቀር እንደሚችል ነው የተናገረው።

አዲስ ማለዳ ባደረገችው ምልከታ በሕዝብ መናኸሪያዎች ቁጥራቸው የበዛ መንገደኞች የመኖራቸውን ያህል ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት ዕጥረት መኖሩን ለማየት ችላለች። በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ባለው የኢኮኖሚ እና ሌሎች ተያያዥ ማኅበራዊ ችግር፣ እንዲሁም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መስፋፋት እና ሠላምን ለማስፈን ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የተነሳ የሚስተዋለው የትራንስፖርት መጨናነቅና ችግር ከቀድሞው የተለየ እንደሆነ ይጠቀሳል።

ወቅቱ በዓል መሆኑን ተከትሎ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ተጓዦች ከአገሪቱ ዋና ከተማ ወደ ተለያዩ የክልል ከተሞች የሚያደርጉት ጉዞ በእጅጉ የበዛ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኤፍ ኤም አውቶብስ ሠራተኞች ይናገራሉ። መጪዉ በዓል መሆኑን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ከተለመደው የጨመረ ቁጥር ያለው መንገደኛ እንዳለ ነው የተገለጸው።

በዚህ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የተለያዩ መንገደኞች አሁን ላይ የሚስተዋለው የትራንስፖርት ዕጥረት በተለይም የታሪፍ ጭማሪዉ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል። በዓል በመሆኑን ብዙ ደንበኞች እንደሚመጡ የሚናገረው ደግሞ ስሙን መጥቀስ ያልፈለገዉ እና ትኬት በማስቆረጥ የኮሚሽን ሥራ በመሥራት የተሰማራው ወጣት ነው። ወጣቱ አሁን በዓል በመሆኑ ተሳፋሪዎች ከሳምንት በፊት ትኬት እንደገዙ እና አብዛኛው ትኬትም እንዳለቀ ይናገራል። አያይዞም የአውቶብስ ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች እስከ በዓል ዋዜማ ድረስ ያለውን የጉዞ ትኬት ቀድመው እንደገዙም ሳይናገር አላለፈም ወጣቱ። በዚህ ምክንያት በርካታ ተጓዦች በዓሉን ከቤተሰብ ጋር ለማሳለፍ ብዙ አማራጮችን ለመጠቀም ቢሞክሩም፣ እስከ ጳጉሜ ኹለት ድረስ የነበረው የአውቶብስ ትኬት ወደ ሐዋሳ ለሚደረግ ጉዞ ብቻ እንደነበር ወጣቱ ለአዲስ ማለዳ ጠቁሟል።

የኤፍ አም ባስ ትኬት ቆራጭ የሆነችው አብነት መኮንን እንዲህ ስትል በዓልን ጠብቆ የሚከሰተውን የትራንስፖርት ዕጥረት ትገልጸዋለች። “አሁን በተለይ መጪው በዓል መሆኑን ተከትሎ ባሶች ከሳምንት በፊት ነው ሙሉ የሚሆኑት። እኛ በሦስት ፈረቃ ነው የምንሠራው፤ ሌሊት አስር ሰዓት፣ ጠዋት አራት ሰዓት እና ከሰዓት ስምንት ሰዓት። ግን እንደዛም ሆኖ ተጓዦች ብዙ በመሆናቸው እስከ አርብ ድረስ ማለትም እስከ አዲስ ዓመት ዋዜማ በሦስቱም ፈረቃ ያሉት ኹሉም ባሶች ሙሉ ናቸው።”

ኹሌም በበዓላት ወቅት በሚኖረው የተጓዥ ቁጥር መጨመር ምክንያት የትራንስፖርት ዕጥረት ማጋጠሙ የተለመደ ነው። ከዚሁ ዕጥረት ጋር ተያይዞ የሚመጣው መጉላላት እና መንገላታት እንዳለ ሆኖ፣ አሁን አሁን የትራንስፖርት ክፍያ ከመደበኛው ብዙ ጭማሪ እየታየበት መሆኑ ለመንገደኞች ሌላ የራስ ምታት እንደሆነባቸው ይናገራሉ።

በዚህ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ቢሮ ኃላፊ ይግዛው ዳኘ በጉዳዩ ላይ ተመሳሳይ ጥቆማዎች እንደደረሷቸው በመጥቀስ፣ የሁኔታውን እርግጠኛነት በማጣራት ላይ እንደሚገኙ እና ከታሪፍ ጭማሪ እና አንዳንድ ሕገ-ወጥ ተግባራት ጋር በተገናኘ ክትትል እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት። አያይዘውም ከኮቪድ-19 ፕሮቶኮል ጋር በተያያዘ መንገደኞች ብዙ እንቅስቃሴ ባያደርጉ ይመረጣል ሲሉ ይመክራሉ።

በዓላትን ምክንያት በማድረግ ኹልጊዜም የትራንስፖርት መጨናነቅ፣ ዕጥረት እና የዋጋ መናር ቢኖርም ይህ ችግር የመንገደኞችን ከቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመድ ጋር ሰብሠብ ብሎ በዓልን የማሳለፍ ሐሳብ አለማስቀየሩ ሁነቱ የበዓሉ እንደኛው ድምቀት እና መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com