የእለት ዜና

ኮሚሽኑ በተለያዩ ከተሞች ያገኛቸውን 200 ቶን ኬሚካሎች ሊያስወግድ ነው

የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በ739 ከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ የሕግ ተከባሪነት ክትትል እና ቁጥጥር ካደረገ በኋላ 200 ቶን ኬሚካል ሊየስወግድ መሆኑ ተገለጸ።
አዲስ ማለዳ ከኮሚሽኑ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው በአገር ውሰጥ የሚመረትን እና ከውጪ የሚገባውን ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ኬሚካል መመዝገብና ማስተዳደር የሚያስችል አገራዊ የኬሚካል ምዝገባ ቋት ተመስርቷል። በዚህም በ2013 በጀት ዓመት 160 ቶን ዲዲቲ ከአገር ወጥቶ አካባቢያዊ ተቀባይነት ባለው መንገድ እንዲወገድ የተደረገ ሲሆን፣ 200 ቶን ታሸጎ ለጎዞ ዝግጁ ተደርጓል ተብሏል።

በ11 ተቋማት በተለያየ አይነት ምድብ ኬሚካሎች 335 ሺሕ ሊትር ፈሳሽ፣ 141 ሺሕ ኪ.ግ. ጠጣር፣ መጠኑ ያልታወቀ የጠርሙስ ኮዳ፣ ከረጢት ኬሚካሎች በመጀመሪያ ደረጃ በቆጠራ እንዲለዩ ተደርጓል። በተያያዘም የውኃ ብክነት እና የአየር ጥራት ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል አገራዊ ፍኖተ ከባለድርሻ አካላት አካላት ጋር እንዲዘጋጅ መደረጉን አዲስ ማለዳ የደረሳት መረጃ ያሳያል።

ኮሚሽኑ በስኳር ልማት ፕሮጄክቶች ባደረገው ክትትል የፋብሪካ ግንባታ ተረፈ ምርት በማሰባሰብ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የሥራ ዕድል መፈጠር ችሏል።
በፌደራል፣ በክልል እና በከተማ አስተዳደሮች የአካባቢ ብክለት ይወገድልኝ አቤቱታዎችን እና ጥቆማዎችን በመመርመር ምላሽ ለመስጠት ታቅዶ 5529 የአካባቢ ብክለት ይወገድልኝ አቤቱታዎች ተለይተው ምላሽ እንዲያገኙ ተደርጓል።
በፌደራል አገልግሎት መስጫ እና ማምርቻ ተቋማት ላይ ክትትልና ቁጥጥር የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ ማስገንባታቸው፣ለማቅለሚያ የሚጠቀሙበትን ክሮም እንደገና ለመጠቀም ክሮም ሪከቨር ፕላንት መገንባታቸው፣የደረቅ ቆሻሻ ግቢያቸው ውስጥ በዓይነት በመለየት ለማስወገድ ጥረት ማድረጋቸው እና የራሳቸውን አነስተኛ ላብራቶሪ ክፍል ሠርተው ወደ ሥራ መግባታቸው ታውቋል።

በተመሳሳይ የድሬደዋ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ አየርን ሊበክሉ የሚችሉ ብናኞችን ከምንጫቸው በአግባቡ የሚሰበስብበት ቴክኖሎጂ ባለመግጠሙ እንዲዘጋ የተደርገ ሲሆን፣ በተሰጠው ምክረ-ሃሳብ አዲስ ቴክኖሎጂ አስገንብቷል።
ቢሾፍቱ የሚገኙት አሻም አፍሪካ ሪዞርት እና ፒራሚድ ሪዞርት በዓመቱ አዳዲስ የብክለት መቀነሻ ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ ካስገቡ ድርጅቶች የሚጠቀሱ ናቸው።

በተጨማሪም በ40 እርሻዎች ላይ ክትትል በማድረግ በዝቀተኛ ደረጃ የሚገኙትን እርሻዎች የመጨረሻ የስድስት ወር የጊዜ ገደብ በመስጠት እንዲያሻሽሉ ለማድረግ ታቅዷል።
በ46 የፕላስቲክ አምራች ተቋማት የምርት ግብዓት እና ውጤት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ በታቀደው መሠረት በኦሮሚያ ክልል ሰበታ፣ቡራዩ፣ ዱከም፣ ሱሉልታ እና ለገጣፎ እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ፋብሪካዎች በተደረገ ቁጥጥር በስበሶ ከአፈር የማይዋሀድ ፕላስቲክ ከረጢት እንደሚያመርቱ የተረጋገጠ ሲሆን፣ በቀጣይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን 86 አርሶ አደሮች ከገቡበት የተፈጥሮ ደን ውስጥ ተከሰው እንዲወጡ በማድረግ 211 ሔክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ የተደረገ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ጉዳያቸው በክስ ተይዞ ይገኛል። በሕገ-ወጥ
ከተወረሱ የደን ምርት ዉጤቶቸ ሽያጪና ከቅጣት 4ሚሊዮን 294 ሺሕ ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል። በተጨማሪም በአማራ ክልል በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የተወረሱ የደን ውጤቶች ተሸጠው አንድ ሚሊዮን ብር ለመንግስት ገቢ ተደርጓል።
በአማራ ክልል ደብር-ብርሃን ከተማ የሚገኙት ዳሽንና ሐበሻ ቢራ ፍብሪካዎች ከፋብሪከው የሚወጣ ተርፍ ምርትንበከፍተኛ ሙቀት የሚያቃጥል ቴክኖሎጂ በመግጠም ሻገታው እንዲቃጥል በማድረግ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች ለከብት መኖ እንዲጠቀሙበት እየተደረገ እንደሚገኝ የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!