የእለት ዜና

የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት በጥፋት ቡድን ላይ “የማያዳግም ዕርምጃ” ሊወስድ መሆኑን ገለጸ

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል እና በከማሺ ዞን እየተባባሰ የመጣው የጸጥታ ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ የክልሉ መንግሥት እና የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት በጥፋት ቡድኑ ላይ “የማያዳግም ዕርምጃ” ሊወስዱ መሆኑን አስታውቀዋል።
የበኔኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግሥት እና የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከየክልሎች የልዩ ኃይል አባላት፣ ከሚሊሺያ አባላትና ከግል ታጣቂዎች ጋር በመሆን በጥፋት ቡድኑ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወሰደውን ዕርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከወትሮ የተለየ ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ መንግሥት ጳጉሜ 4/2013 በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን ባለፉት ጊዜያት በመተከል እና በካማሽ ዞኖች “የጁንታው የህወሓት ቡድን ቀንደኛ ተላላኪ” ያለውና በክልሉ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ኃይል የፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ከተወሰደው ዕርምጃ ባሻገር የተለያዩ አማራጮችን አስቀምጦ ሲሠራ ቢቆይም ለውጥ አለማምጣቱን ተናግሯል።

የክልሉ መንግሥት ችግሩን በሠላማዊ መንገድና በውይይት ለመፍታት ከፍተኛ የሆነ የበጄት፣ የጊዜ፣ የሰው ኃይል በመመደብ ለወራት የዘለቀ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉ የገለጸ ሲሆን፣ በመተከል እና ካማሺ ዞኖች ከሚንቀሳቀሰው የጥፋት ቡድኑ አባላት መካከል የተወሰኑት የቀረበውን “ሠላማዊ ድርድር” በመቀበላቸው የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱም መደረጉን አስታውሷል።

“ነገር ግን መንግስት በሆደ ሠፊነት እና ንጹኃን ዜጎች አብረው እንዳይጎዱ በሚል ሠፊ ጊዜ ወስዶ ባለፋት ወራት ያስቀመጠውን የሠላማዊ ድርድር ዕድል እንደ ፍርሃትና ሽንፈት በመቁጠር የአሻባሪውን የህወሓት ቡደን ተልዕኮ ለማስፈጸም የተሃድሶ ሥልጠና የወሰዱት የጥፋት ቡድኑ አባላት ሳይቀር ወደጫካ በመግባት አሁንም ድረስ በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት ከማድረስ ባሻገር፣ ዜጎች ደክመው ያፈሩትን ሀብትና ንብረት መዝረፍን አጠናክረው ቀጥለውበታል” ብሏል።

በክልሉ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ቡድን በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በፈጠረው የጸጥታ ችግርና ጥቃት በሰው ሕይወት፣ በአካል፣ በንብረት ከደረሰው ጉዳት ባሻገር በርካታ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኖል ሲል መግለጫው ጠቅሷል።
የክልሉ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በሚንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወስዱ ከዚህ ቀደም ለጸጥታ አካላት ትዕዛዝ ማስተላለፉን አስታውሷል።፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት “ተላላኪ” ነው የተባለው በክልሉ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ኃይል፣ “በክልሉ ዘላቂ ሠላም እንዳይኖር ለማድረግ አሁንም ድረስ ከሠላም ይልቅ “ሽፍትነትን” የኑሮው አንድ አካል አድርጎ በመቀጠሉ፣ ንጹኃን ዜጎችን ከመግደል፣ ንብረት ከመዝረፍና ሕብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር ከማድረግ አልተቆጠበም” ተብሏል።

በመሆኑም፣ የክልሉ መንግሥት እና የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከየክልሎች የልዩ ኃይል አባላት፣ ከሚሊሺያ አባላትና ከግል ታጣቂዎች ጋር በመሆን የማያዳግም ዕርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል። በመግለጫውም “በተለይም በመተከል እና ካማሺ ዞኖች ጸረ-ሠላም ኃይሉ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኀብረተሰብ ክፍሎች ይህንን አውቀው ራሳቸውን ከጥፋት ቡድኑ እንዲነጥሉ የክልሉ መንግስት በጥብቅ ያሳስባል” ብሏል።

በተጨማሪም፣ መግለጫው ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ለሚወስደው ሕግ የማስከበር ዕርምጃ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የመንግሥትና የግል ታጣቂዎች፣ ወጣቶች፣ እንዲሁም ኹሉም የሕብረተሰብ ክፍል ቅድሚያ በመስጠት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ የክልሉ መንግስት እና የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት ጥሪ አቅርቧል።

በክልሉ በተለይም በመተከል እና በካማሺ ዞኖች ያለው የጸጥታ ችግር እልባት አለማግኘቱን ተከትሎ የንጹሐን ዜጎች ግድያና እና መፈናቀል እንደቀጠለ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!