የእለት ዜና

ኹለት አዳዲስ የብረታብረት አምራች ድርጅቶች ወደ ገበያ መግባታቸውን ኢንስቲትዩቱ አስታወቀ

የብረታብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ኹለት አዳዲስ የብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ገበያ መግባታቸውን አስታወቀ።
ኢትዮጵያዊ የሆኑት ኹለቱ ግዙፍ ተቋማት የመሠረታዊ ብረታብረትና የመኪና መለዋወጫ ምርት ማምረት የሚያስችሉ መሆናቸውን በኢንስትቲዩቱ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ፌጤ በቀለ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የኢንቨስትመንት ዘርፉን የተቀላቀሉት ኹለት ፕሮጀክቶች፣ በመሠረታዊ ብረታብረት ዘርፍ “ጆሪ” ኃ.የተ.የግ.ማኅበር እና በአውቶሞቲቭ ምርት ዘርፍ ደግሞ “ዜድ ዋይ ስፔር ፓርትስ ማኑፋክቸሪንግ” ኃ.የተ.የግ. ማኅበር በመባል ይታወቃሉ። እነዚህ ተቋማት ወደ ገበያ መግባታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በብረታብረት ዘርፍ የሚመረቱ ምርቶችን መጠን በአንድ ሚሊዮን ቶን ማሳደግ ያስችላል ሲሉ ፊጤ ጠቁመዋል።

በመሠረታዊ ብረታብረት ኢንዱስትሪ የሚመደቡት ከብረት ማጣራት ጀምሮ የተለያዩ መጠን ያላቸውን የመጀመሪያ ደረጃ ምርቶችንና እነዚህን ምርቶች በግብዓትነት በመጠቀም ዝርግና ጥቅል ልሙጥ ብረቶችን፣ የተለያዩ ቅርፅ ያላቸው ድፍንና ክፍት ረጃጅም የብረት ምርቶችን፣ ሽቦዎችን፣ የሽቦ ገመዶችን፣ ቆርቆሮዎችንና ምስማሮችን የማቅለጥ፣ የማሞቅና የመዳመጥ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚያመርቱ ናቸው።

እንደ አገር በብረታብረት ኢንዱስትሪዎች የሚመረተው የምርት መጠን 10 ሚሊዮን ቶን ሲሆን፣ ኹለቱ ተቋማትን ጨምሮ በቅርቡ በሚቀላቀሉ አዳዲስ ተቋማት አማካይነት ምርቱ ወደ 11 ሚሊዮን ቶን ይደርሳል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ እነዚሀ ድርጅቶች ይዘው የመጡት አዳዲስ ቴክኖሎጂ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ይፈጥራል ብለዋል።

መሠረታዊ የብረታብረት አምራች የሆነው ጆሪ የተባለው ተቋም 115 ሺሕ 149 ቶን ዓመታዊ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፣ የመለዋወጫ አምራቹ ዜድ ዋይ ደግሞ 100 ሺሕ ቶን ያህል ዓመታዊ የማምረት አቅም አለው ሲሉ ፊጤ ተናግረዋል።
እነዚህ ኹለት ድርጅቶች በከፍተኛ ወጪ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በመቀነስ የአገር ውስጥ ምርትን የሚያሳድጉ ናቸው ተብሎላቸዋል።

እንደነዚህ ያሉ በዓመት እስከ 300ሺሕ ቶን ብረታብረት የሚያመርቱ ተቋማት ላይ በዋናነት የጥሬ እቃ ግብዓት ዕጥረት ችግር መኖሩን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ከአገር ውስጥ ውድቅዳቂ ብረታብረቶች መጠቀም የሚችሉበትን ሥራ ኢንስቲትዩቱ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ድርጅቶቹ እነዚህን ውድቅዳቂ ግብአቶች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና ከግል የመኪና ዕቃ አምራቾቹ እንዲያገኙ ኢንስቲትዩቱ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየሠራ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪ ከመንግሥት በሚገኝ የውጭ ምንዛሬ ጥሬ ዕቃዎች እንዲያስገቡ ለማድረግ ታቅዷል።

የብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ለአገር ትልቅ የኢኮኖሚ መሠረት እንደመሆኑ መጠን ድጋፍ የሚሰጠው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 182/2002 የተቋቋመ ነው።
እንደ አገር የተለያዩ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ድርጅቶች የውጭ ንግድ የጀመሩ ሲሆን፣ እንደነዚህ አይነት አዳዲስ ተቋማት ወደ ገበያው መቀላቀላቸው ወደ ጎረቤት አገራት የምንልካቸውን ምርቶች ለመጨመር ያስችላል ሲሉ ፊጤ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በአገር ውስጥ ቢሆን ከፍተኛ የሆነ የምርት ፍላጎት በመኖሩ ይህንን ያልተሟላ ፍላጎት ለማዳረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ሲሉ ፊጤ ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com