የእለት ዜና

በዩኒቲ አካዳሚ መዘጋት የተበተኑ የ1420 ተማሪ ወላጆች የራሳቸውን አካዳሚ አቋቋሙ

ወላጆች ያቋቋሙት አካዳሚ ከኤልፎራ ጋር የቦታ ኪራይ ውል ተፈራርሟል

ዩኒቲ አካዳሚ ባሳፍነው ሰኔ ወር ላይ መዘጋቱን ተከትሎ የተበተኑ የ1420 ተማሪ ወላጆች “ፓሽን አካዳሚ” የተሰኘ አዲስ ትምርት ቤት ለልጆቻቸው ማቋቋመቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ዩኒቲ አካዳሚ ቀራንዮ ቅርንጫፍ 1420 ተማሪዎችን በ2014 የትምህርት ዘመን አላስተምርም ማለቱን ተከትሎ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካል የሆነው ኤልፎራ አግሮ ኢንደስትሪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የትምህርት ቤቱን ግቢ ለሌላ ትምህርት ቤት አከራይቸዋለሁ በማለቱ በተማሪ ወላጆች ቅሬታ መቅረቡ የሚታወስ ነው።

የተማሪ ወላጆች “ልጆቻችን አይበተኑ” በማለት ለሦስት ወራት ለመንግሥት እና ለሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ከቆዩ በኋላ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር አደራዳሪነት ከኤልፎራ አግሮ ኢንደስትሪስ በኪራይ ለመማሪያ የሚሆን ቦታ መረከባቸውን አዲስ የተቋቋመው ፓሽን አካዳሚ የቦርድ አባል ሳባ ኃይለማሪያም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተማሪ ወላጆች የተቋቋመው ፓሽን አካዳሚ ከኤልፎራ በኪራይ የተረከበው ቦታ 10 ሺሕ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ ጦር ኃይሎች አላሙዲ ፕላዛ ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ጀርባ የሚገኝ መሆኑ ተገልጿል። የተማሪ ወላጆች ለአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ባቀረቡት ቅሬታ መሠረት፣ የከተማ አሥተዳደሩ ባለሥልጣናት ከኹለት ሳምንት በፊት ዩኒቲ አካዳሚን፣ ሜድሮክ አካዳሚን እና የተማሪ ወላጆችን ለማግባባት ቀጠሮ ይዘው ዩኒቲ አካዳሚ በለመገኘቱ የከተማ አሥተዳደሩ የተማሪ ወላጆችን እና ሜድሮክ ኢንቨስትመንትን አስማምተዋል ተብሏል።

የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አሕመድ ከተማሪ ወላጆች ጋር ባደረጉት ውይይት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ፣ የተማሪ ወላጆች ቀድሞ ትምህርት ቤቱን ለማስተዳደር በጠየቁት መሠረት ሕጋዊ ሆነው ከኤልፎራ ጋር ተፈራርመው ቦታውን በኪራይ ማስተዳደር እንዲችሉ ፈቃድ ማግኘታቸውን ሳባ ጠቁመዋል።

የሜድሮክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተማሪ ወላጆች ሕጋዊ ሆነው ቦታውን በኪራይ ማስተዳደር እንደሚችሉ ፈቃድ ከሰጡ በኋላ፣ የተማሪ ወላጆች አዲስ ባቋቋሙት ፓሽን አካዳሚ አማካይነት ባሳለፍነው ነሐሴ 28/2013 ከኤልፎራ ጋር ቦታውን በኪራይ ለማስተዳደር ውል መፈራራመቸውን ሳባ ገልጸዋል።

በተፈረመው ውል መሠረት የትምህርት ቤት ቦታውን ፕሽን አካዳሚ በኪራይ ከተረከበ በኋላ በ2014 ትምህርት ዘመን ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ሳባ ጠቁመዋል። በወላጆች የተቋቋመው ፓሽን አካዳሚ በ2014 ትምህርት ዘመንት ከኬጂ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት እንደሚሰጥ ተመላክቷል። አካዳሚው በአዲሱ የትምህርት ዘመን ትምህርት ለመስጠት የትምህርት ቁሳቁስ ከማሟላት አስክ መምህራን ቅጥር ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ፓሽን አካዳሚ በተማሪ ወላጆች የተቋቋመ መሆኑን ተከትሎ ወላጆች የትምህርት ቤቱ ባለቤት በመሆናቸው አክሲዎን እየሸጠ መሆኑ ተገልጿል። የአክሲዎን ሽያጩ እንደቀጠለ መሆኑን የጠቆሙት ሳባ፣ የአንድ አክሲዎን ዋጋ 10 ሺሕ ብር መሆኑን ገልጸዋል። አንድ የተማሪ ወላጅ መግዛት የሚችለው አንድ አክሲዎን ብቻ ነው ተብሏል።

ፓሽን አካዳሚ በወላጆች የተቋቋመ ማኀበረሰብ ዐቀፍ የትምህርት ተቋም መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ዋና ዓላማው ተማሪዎች እንዳይበተኑ ለማድረግ ተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው ተብሏል። ዩኒቲ አካዳሚ መዘጋቱን ተከትሎ ልጆቻቸውን ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ያስገቡ ወላጆች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ፓሽን አካዳሚ መቋቋሙን ሲሰሙ እየተመለሱ መሆኑ ተመላክቷል። አቅም ለሌላቸው የተማሪ ወላጆች ልጆቻቸውን ሌላ ትምህርት ቤት ለማስተማር የከፈሉትን ክፍያ ደረሰኝ በመቀበል ፓሽን አካዳሚ ወደ አክሲዎንነት በመቀየር ድጋፍ እንደሚደርግ ሳባ ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!