የእለት ዜና

ከሰሜን ወሎ ተፈናቅለው በአዲስ አበባ የሚገኙ ከአንድ ሺሕ በላይ ዜጎች ዕርዳታ እየተደረገላቸው ነው

ከአማራ ክልል ከሰሜን ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአዲስ አበባ ለሚገኙ ከአንድ ሺሕ በላይ ዜጎች ዕርዳታ እየሰጠ መሆኑን በከተማዋ በሚኖሩ የሰሜን ወሎ ተወላጆች የተቋቋመው ኮሚቴ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
በሽብረተኝት የተፈረጀው ህወሓት በአማራ ክልል ባደረሰው ጥቃት ከሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአዲስ አበባ የሚገኙ ዜጎች “ችግር ላይ ናቸው’’ ያለው ኮሚቴው፣ ከተለያዩ ርዳታ ሰጪዎች ድጋፍ አሰባበስቦ እየረዳ መሆኑን አስታውቋል:: የመጀመሪያው ዙር ድጋፍ ባሳለፍነው ጳጉሜን 3/2013 ለተፈናቃዮቹ የተሰጠ መሆኑ ተመላክቷል።

ከዞኑ ተፈናቅለው በአዲስ አበባ የሚገኙ ዜጎች ከሦስት ሺሕ በላይ መሆናቸውን የገለጸው ኮሚቴው፣ ለጊዜው በጣም ለተቸገሩ አንድ ሺሕ ሰዎች 11 ሺሕ ኪሎ ግራም መኮረኒ በመጀመሪያ ዙር ዕርዳታ መሰጠቱን የኮሚቴው ሰብሳቢ ታመነ መኮነን ገልጸዋል።
ኮሚቴው ዕርዳታ ለማድረግ የመዘገበው ከኮረም ጀምሮ እስከ መርሳ ድረስ ተፈናቅለው አዲስ አበባ የሚገኙ ዜጎችን ሲሆን፣ እስካሁን የተመዘገቡት አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ከራያ ቆቦ፣ ከሐራ፣ ከወልዲያ፣ ከመርሳ እና ከግዳን ወረዳ የመጡ መሆናቸውን ሰብሳቢው አብራርተዋል።

ሰብሳቢው አክለውም በዞኑ አራብሮ ወረዳ ድሬ ሎቃ በተባለው አካባቢ ያሉ ሰዎች በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በሰነዝረው ጥቃት፣ “እናቶችና ሕጻናት ከቤታቸው መፈናቀላቸውንና ነፍሰጡሮች ሜዳ ላይ እየወለዱ ዝናብና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸው እንደሚገኙ አረጋግጠናል” ሲሉ ገልጸዋል።

በአራብሮ ወረዳ ድሬ ሎቃ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ናቸው ላሏቸው ሴቶችና ሕፃናት፣ አይ አር ሲ ከተባለው በመዲናችን ከሚገኘው የዕርዳታ ድርጀት ያገኙትን 200 የቁሳቁስ ጥቅል ድጋፍ ወደ አካባቢው በመሔድ አርዳታ አድርገናል ብለዋል።
አይ አር ሲ ለኮሚቴው ባበረከተው በእያንዳንዱ ጥቅል ዉስጥ ምንጣፍ፣ ሳሙና፣ የምግብ ማብሰያ፣ ጭልፋና የውኃ መቅጃ ጀሪካን የተካተተ ሲሆን፣ በዚህም ለ 200 የቤተሰብ አባላት ቁሳቁስ ለመርዳት አስችሎናል ሲሉ ነው ታመነ የገለጹት።

ከ 200ው የቁሳቁስ ዕርዳታ በተጨማሪ ኮሚቴው ለዱቄት መግዣ የሚሆን 250 ሺሕ ብር፣ ብርድ ልብስ እና ለሕፃናቱ የሚሆን አራት ማዳበሪያ ልብስ እንዳበረከተም አብራርተዋል።
ኮሚቴው ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ዕርዳታ ለማድርግ የሚያስችሉትን የተለያዩ የባንክ አካውንቶች በመክፈት ከአገር ውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል።

የኮሚቴው አባላት አያይዘውም፣ በደሴና በኮምቦልቻ በሚገኙ 16 ጣቢያዎች ተጠግተው ላሉ ተፈናቃዮች አንድ አይሱዚ ልብስ፣ 300 ኩንታል መኮረኒ፣ 150 ብርድ ልብስ፣ ብስኩትና ፓስታ ባሳለፍነው ሳምንት ዕርዳታ አድርገናል ሲሉ ገልጸዋል።
በደሴና ኮምቦልቻ ዕርዳታ ማድረጉን ለአዲስ ማለዳ የገለጸው ኮሚቴው፣ በ16ቱ ጣቢያዎች በጠቅላላ ከ110 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቁሟል።

አዲስ ማለዳ ከተለያዩ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች በመፈናቀል በአዲስ አበባ ከሚገኙ ግለሰቦች ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ ተፈናቃዮቹ በመዲናችን ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ የመጠለያ፣ የምግብና የአልባሳት ዕጥረት እንዳለባቸው ነው የነገሯት።
አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ተፈናቃዮች መካከል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ወጣት “ሰው በጦርነቱ ደመ-ነፍሱን ነው ሸሽቶ የመጣው፤ አብዛኛው በረንዳ አዳሪ ነው የሆነው። አዲስ አበባ የኑሮ ውድነት መኖሩ ይታወቃል እናም መንግሥት ይህን ችግር ተረድቶ ዕርዳታ እንዲያደርግልን ነው የምንፈልገው” ሲል ነው የገለጸው።

አሁንም በችግር ላይ የሚገኙ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የገለጹት የኮሚቴው አባላት፣ የድጋፍ ተግባሩን ለማስቀጠል ማንኛውም ፈቃደኛ የሆነ አካል ዕርዳታ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 1

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

  1. እባካችሁ ኮሚቴው የሚገኝበትን አድራሻ ጠቁሙን። ብዙ ስለርዳታው ያልሰሙ ተፈናቃዮች አሉ።

error: Content is protected !!