የእለት ዜና

በአዲስ አበባ ጫማ በማጽዳት የሚተዳደሩ ወጣቶች የመሥሪያ ቦታቸውን እየተነጠቁ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ጫማ በማጽዳት ሥራ የተሠማሩ ወጣቶች ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የሥራ ቦታቸውን መነጠቃቸውን እና ሥራ መሥራት እንዳይችሉ መከልከላቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የሥራ መሥኮች ተሠማርተው በሥራ ላይ የሚገኙ ወጣቶች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ እነዚህ ወጣቶች ከተሠማሩባቸው ሥራዎች መካከል ደግሞ የጫማ ማጽዳት ወይም ሊስተሮ ይገኝበታል። በተለይ የክረምት ወቅት ጫማ በማጽዳት የተሠማሩ ወጣቶች ደህና ገቢ ያሚያገኙበት እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን አሁን እነዚህ ወጣቶች ሥራቸው ላይ ችግር እንደተጋረጠባቸው ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እነዚህ ወጣቶች፣ ከአራት ዓመት በፊት መንግሥት በየቀበሌያቸው እንዳደራጃቸው እና የሥራ አጥነት ፎርም በማስሞላት ፎቷቸውን በወረዳ እና ቀበሌዎች እንዳስገባ በመጥቀስ፣ አሁን ምክንያቱን በማናውቀው ሁኔታ የሥራ ቦታችንን እንድንለቅ፣ ለፀሐይ እና ለዝናብ መከላከያ የምንዘረጋውን ጥላ እንድናነሳ እና ከዚህ በፊት በግለሰቦች የተሰጠንን የብረት መቀመጫ እንዳንጠቀም በደንብ አስከባሪዎች እየተከለከልን ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ለደኅንነታችን እንሠጋለን በማለት ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉት እና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስታዲየም ዙሪያ አካባቢ ተቀምጠው የሊስትሮ ሥራ በመሥራት የሚተዳደሩት ወጣቶች እንደሚሉት፣ ካሳለፍነው እሁድ ጀምሮ የሥራ ቦታቸው በደንብ አስከባሪዎች እንደፈረሰባቸው እና በቀጣዮቹ ቀናትም ወደ ሥራ ቦታቸው ሲመለሱ መሥሪያቸው ሌሊቱን ፈርሶ እንደጠበቃቸው ብሎም ላሜራዎች እና ሌሎች ለሥራ የሚገለገሉባቸው የሊስትሮ ዕቃዎችን እንደተወሰዱባቸው ተናግረዋል።

ወጣቶቹ አያይዘውም ሌላ የሥራ ቦታ እንደሚሰጠን ነግረውናል ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን ቦታው የት እንደሆነ፣ ማን እንደሚሰጠን እና መቼ እንደምንረከብ አልተነገረንም ብለዋል። በዘርፉ የተሠማሩት ወጣቶች ኑሯቸውን የሚገፉት በየዕለቱ በሚያገኙት ገቢ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ አሁን ግን ለአካባቢው ጽዳት ሲባል፣ እንዲሁም በበዓላት ምክንያት እንግዶች ስለሚመጡ እናንተ እዚህ መሥራት አትችሉም፣ ላሜራውም ሕጋዊ አይደለም የሚሉ አካላት ሥራ እንዳንሠራ እየከለከሉን እና ዕቃዎቻችንንም ሌሊት በአይሱዙ መኪና እየጫኑ እየወሰዱብን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

“እኛ በሌብነት ወይም በሌላ የወንጀል ሥራ አልተሠማራንም፤ በየቀኑ ለፍተን ደክመን ዝቅ ብለን የደንበኞቻችንን ደስታ ለመጠበቅ የምንሠራ እና ቤተሰብ የምናስተዳድር ሰዎች ነን” የሚሉት ወጣቶቹ፣ “ከእኛ መካከል ልጆች ያሏቸው፣ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ እና ተማሪ የሆኑ አሉ። የዕለት ዳቦ የምናገኝበትን ሥራ ለምን እንደተከለከልን እሰካሁን ግልጽ አልሆነልንም” በማለት ነው ምሬታቸውን የገለጹት።

በተመሳሳይ፣ ካዛንችስ አካባቢ በዚሁ ሥራ የተሠማራው ወጣት ስሜን መናገር አልፈልግም በማለት ጉዳዩ በጣም እንዳሳሰበው እና የሥራ ቦታውን መከልከሉ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት እንኳን ከባድ እንዳደረገበት ይናገራል። ወጣቱ አያይዞም “እኛ ያጠፋነው ጥፋትም ሆነ የፈጸምነው ወንጀል ካለ መንግሥት በአግባቡ ሊጠይቀን ይገባል እንጂ የሥራ ቦታችንን ማፍረስ እና ሥራ እንዳንሠራ መከልከል ተገቢ አይደለም” ሲል ነው ለአዲስ ማለዳ የተናገረው።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የደንብ አስከባሪ አባላትም “እኛ የታዘዝነውን ሥራችንን ነው የምንሠራው” ያሉ ሲሆን፣ አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽሕፈት ቤትን ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!