የእለት ዜና

የመተሳሰብ ባህላችንን እንመልሰው!

Views: 53

መስከረም ወር ዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን የብዙ ተግባሮች መጀመሪያ የዓመቱ ምሳሌ የሆነ የወቅቶች መነሻ ነው። አሮጌ እየተባለ የሚያልቀው ዘመን ተሸኝቶ አዲሱ ወቅት የሚጀምርበት እንደመሆኑ በታላቅ ጉጉት የሚጠበቅ ነው።
ዕንቁጣጣሽን የመሳሰሉ ዓውድ ዓመቶች ከሌሎች ቀናት የሚለዩት በብዙ ተደግሶ በመብላት መጠጣቱ ብቻ አይደለም። የተረሳሳ ይጠያየቃል፤ የታመመ ይጎበኛል፤ ዘመድና ጎረቤት ይጠራራል። የሚተዋወቅ ብቻ ሳይሆን የማይተዋወቅም እንኳን አደረሳችሁ ተባብሎ መልካም ጊዜንና ዘመንን የሚመኝበት ነው። ይህ መልካም ምኞት በአፍ ብቻም የወረት እንዳይሆን ያለው ለተቸገረ እጁን የሚዘረጋበት መሆን እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በዓል የደስታ ወቅት መሆኑ ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ በዕለቱ ሁላችንም ደስተኛ ሆነን እንደማንውል ይታወቃል። በተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ በሆነ ምክንያት ሐዘንና ጉዳት ላይ ያሉትን ሳይጨምር በኑሮ ውድነትም ሆነ ሥር በሰደደ ድህነት፣ ደግ ጊዜን እያስታወሱ የሚተክዙ አለፍ ሲልም የሚያዝኑና ቀንተው የሚያለቅሱ ልጆቻቸውን እያዩ የሚቆጩም እንደማይጠፉ ይታመናል።

በቀደሙት ዘመናት ሰዎች ደግሰው የሚያውቁትን ብቻ እንዲገኝላቸው መጥራትም ሆነ፣ በበዓላት ወዳጅን ብቻ መጠየቅ እንደነውር የሚቆጠርበት ጊዜ እንደነበር በዕድሜ የገፉት ይናገራሉ። አሁን የማያውቁትን አስገብቶ ማቋደሱ ሙሉ በሙሉ ባይጠፋም፣ በገጠሪቷ የኢትዮጵያ ክፍል አሁንም መተዛዘኑና መደጋገፉ በስፋት እንዳለ ይነገራል። ትውውቅም ሆነ ማንኛውም የኑሮ ደረጃ ከግምት ውስጥ ሳይገባ፣ በራቸው ላይ ቆመው አላፊ አግዳሚው ገብቶ እንዲቀምስ የሚጋዙ ስለመኖራቸው ያጋጠመው ያውቀዋል።

ሰው ለሰው ልጅ በሽታውም ሆነ መድኃኒቱ እንደሆነ ሲነገር ይሰማል። ሰው ሲያዝን ላፅናናውና ሐዘኑን ለተካፈለው በገንዘብ የሚተመን ምንም ነገር ባያደርግለት እንኳን ምስጋና ማቅረቡ የተለመደ ነው። ሰው ደስ ሲለውም ደስታዬን ተካፈሉልኝ ብሎ ጠርቶ መጋበዙም ሆነ ሌላው ደስ እንዲለው መጨነቁ አሁንም ድረስ አለ። ልዩነቱ ግን የተጋባዡና የተጠሪው ማንነት መለያየቱ ላይ ነው።

በቀደምት ዘመን ነገስታቱ እንደ ደሴው አይጠየፍ አይነት አዳራሾችን ተጠቅመው ከመኳንንቱ ጀምረው ተራውን ዜጋ ቢያንስ በዓመት አንዴ ግብር ያበሉ ነበር። ባለሀብቶችም የሀብት ደረጃቸው የሚታወቀው ድሃውን በምን መንገድ እንደጋበዙ እንጂ፣ እንደአሁኑ ሀብታም ወገንን ብቻ ለይተው በመጥራትና ለእነሱ ውድ ወጪ በማውጣት በመጋበዛቸው እንዳልነበር ይነገራል። ከበፊት አባቶቻችን ይህን መሰሉን በጎ ባህላችንን መውረስ እንደሚገባን አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

የድሮ ዘመን ነገስታትም ሆኑ አቅም ያላቸው ግለሰቦች ሠንጋ ቢያሳርዱ ብቻቸውን አቆይተው ሊበሉት አይቻላቸውም። እንደዘመናችን ፍሪጅም ስለሌላቸው በር ዘግተው የሚበሉበት አጋጣሚ እንዳልነበር ይታወቃል። ሱቅ ሔደው ለራሳቸው ብቻ የሚበቃን የሚገዙበትና ገንዘባቸውን የሚቆጥቡበት መንገድም ስለሌለ የተትረፈረፈ ድግስ ይደገስ እንደነበር ታሪክን የሚውቁ የሚናገሩት ነው። ሰው ባንክ የሚያስቀምጠው የተቆለለ ሐብትም ስለማይኖረው ያለውን ኹሉም ስለሚያውቀው ለሥሥትም አይዳረግም ነበር።

በዘመናችን ልግስና እንደሞኝነት እየተቆጠረ፣ ንፉግነት እንደዘመናዊነት እየታየ በመምጣቱ ያለችንን ተካፍለን ለመብላት እንኳን አስቸጋሪ ሁኖብናል። ከ30 ዓመት በፊት የነበረውን እንኳን ብናስታውስ ከአሁኑ ብዙ ልዩነት አለው። በዓውድ ዓመት ይቅርና በአዘቦቱም ቢሆን ጎረቤት እየተጠራራ ይገባበዛል። ግንኙነቱም ጠንካራ ስለሆነ ሰው እንደተቸገረ ሳይናገር አስቀድሞ ይረዳም ነበር። እንጀራንና ሌሎች ትንንሽ ነገሮችን መሰጣጠት ብቻም ሳይሆን፣ በርካታ የአካባቢው የችግረኛ ልጆችን በመደበኛነት የሚመግቡ በየሰፈሩ ነበሩ። ይህን ለማድረግ የበዛ ሀብት መኖር ሳያስፈልግ ከሌላው በትንሹም ቢሆን የተሻሉ ሆኖ መገኘት በቂ እንደነበር ይስተዋላል።

ሰው ሁሌም ተቸግሮ እንደማይኖርና ሁሌም ደልቶት እንደማይገኝ ያለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን እንደኛ ያሳየው አገር ያለ አይመስልም። ሀብት አላቸው ተብለው የነበሩ ተነጥቀው የሰው እጅ ያዩበት፣ በድህነት ሲኖሩ የነበሩ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው የዘለቁበት፣ ሥልጣን ላይ ሆነው “እዩኝ! እዩኝ!” ሲሉ የነበሩ “ደብቁኝ!” ያሉበትን ዘመንን እስኪበቃን አይተናል። ከቅርቡ ታሪካችን ተምረን መተጋገዝንና መተሳሰብን የበለጠ አጠንክረን መጓዝ እንዳለብን አዲስ ማለዳ በአፅንኦት ታሳስባለች።

የሌላው ችግርና ዐቅም ማነስ ሊታየንና ልናግዝ የሚገባን ታዲያ በዓውድ ዓመት ብቻ አይደለም። ሁሌም ዘወትር መቀጠል ያለበት እንጂ የጋራ ጠላት ሲመጣ ብቻ መተግበር ያለበት የክት ባህሪ መሆን አይገባውም። “ዕርዱኝ” የሚል ወገን ባይኖርም፣መረዳዳት ሁሌም መኖር ያለበት ተግባር ነው። አገራችን የምትከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲም ሆነ አጠቃላይ ሥርዓቱ ሕዝብን በዕኩል ማስተዳደር ስለማይቻለው፣ ኹሉም እንደልፋቱ ዕኩል ተጠቃሚ የሚሆንበት ፍትሐዊ መንገድም ስለማይኖር በተቻለን መጠን መረዳዳቱን እንደግዴታችን ልንቆጥረው ይገባናል።
አንዱ ባንዱ ላይ አዛዥ ናዛዥ መሆን ባይገባውም፣ ያለንን የጋራ ሐብት በጋራ እንድናሥተዳድረው፤ በጥቂት ሀብታሞች እጅ ያለውም ሀብት በእነሱው አማካይነት ለብዙኃኑ ጥቅም እንዲውል ቢደረግ መልካም ነው። ባለሀብቶች ገንዘባቸውን በምንም መንገድ ይሁን ያገኙት ከሕዝብ ላይ እንደሰበሰቡት ሊያውቁ ይገባል። ሕዝቡ ከሌለ ምቾታቸውም እንደማይቀጥል ተረድተው፣ መተጋገዝ የሚቻልበትን መንገድ በትብብር ነድፈው ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል።

እንደበፊቱ በር አንኳኩቶ የሚለምን በሚወቀስበት፣ ቁጭ ብሎ መመጽወትም በሚያስተችበት ዘመን መደበኛ የመርጃ መንገድን ማመቻቸቱ ቀላል ባይሆንም ተግባራዊ መደረግ አለበት። ቅዱስ ላሊበላ በዘመኑ ሰብሥቧቸው የነበሩ ተረጂዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚረከባቸው ባለመኖሩ ለሦስት ተከፍለው በመላው አገሪቱ ከተበተኑበት ታሪክ ልንማር እንደሚገባን አዲስ ማለዳ አበክራ ታስገነዝባለች።

በተለያዩ አገራት የመረዳጃ መንገዶች ይፋ ተደርገው ሕዝብ ማንም ሳይወተውተው እርስበርሱ ይረዳዳል። ተረፋቸውን ምግብ የሚያደርጉበት እያጡ በላስቲክ አሽገው ገንዳ ውስጥ የሚጨምሩ በበዙበት በዚህ ወቅት፣ እንደኢራን ያሉ አገራት ተሞክሮን መቅሰም ይገባናል። እኛ ቆሻሻ የምንጥልባቸውን የመሳሰሉ በየጎዳናው ያሉ ንጹህ ሳጥኖች ተቀምጠው፣ ሰው የማይበላውን ሊበላሽበት ያለውን እህል አስቀምጦ አራዊት እንዳይለክፈው ይዘጋዋል። የበሰለውን የቸገራቸው አውጥተው የሚበሉት ሲሆን፣ ያልበሰለውን እየመረጡ የሚወስዱ አብስለው የሚመግቡ መመገቢያ ጣቢያዎችም አሉ። እኛም ከእነሱ አይተን ተመሳሳዩን ባናደርገም በየደጃፋችን እንደሰቀልነው ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ምግብ ማስቀመጫ ብናዘጋጅ መልካም ነው። ይህ ለምግብ ብቻ ሳይሆን ለአልባሳትም የሚሆን ሲሆን፣ እስክንጠየቅ የማንጠብቅበት የመተሳሰብ መንገድን አመቻችቶ ባህል ያደርገዋል።

ሌላው ከመተሳሰብ ጋር በተገናኘ መታየት ያለበት የነጋዴው ጠባይ ነው። በፊት በፊት አንድ ነጋዴ የዕቃ ዋጋ ሲጠየቅ እየማለ የመጣበትን ጭምር ይናገር ነበር። “አያዋጣም” እያለ እንደዘመኑ ቸርቻሪ በደፈናው የሚመልስ ሳይሆን፣ “ከቦታው አልመጣም” እያለ አስረድቶ ይከራከርም ነበር። “የመጨረሻው ስንት ነው?” የምንባባልበት ባህል ቀርቶ መተዛዘኑም ጠፍቶ፣ “ካልፈለግህ ተወው” የሚል የግዴለሽነት ጠባይ በአብዛኛው ነጋዴ ላይ እንደሚታይ የሚናገሩ አሉ። ሳንቲም ለቅመው ከብዙ ደንበኛ ለመጠቀም የሚሹ የቀደሙ አንጋፋ ነጋዴዎች ያልደረሱበት ማማ ላይ፣ የአሁኖቹ በመተባባር በአጭር ጊዜ አላግባብ ለመበልጸግ ይሽቀዳደማሉ። ነጋዴው ተባብሮ ሕዝቡን መጥቀም ሲኖርበት በተቃራኒው ሕዝብ ላይ ሲያድም ተጎጂው ኹሉም እንደሆነ መገንዘብ ተስኗል።

መንግሥት ኹሉን ነገር በግድ ፍትሓዊ እንዲሆን ለማድረግ ባይቻለውም፣ ዋናው መንግሥት የሆነበትን ተግባሩን ተረድቶ ቅድሚያ አቅሙ ላላው ባለሀብት ሳይሆን ለድሃው መቆም እንዳለበት የአዲስ ማለዳ ዕምነት ነው። መተሳሰብ ለእገሌና ለእገሌ ብቻ ተብሎ የሚተው በቡድንም የሚነገር ሳይሆን፣ ኹሉም ለኹሉም መሆን ያለበት ነው። ሰው ለሰው ብቻም ሳይሆን ለእንስሳትም ጭምር ማሰብ እርስበርሳቸውም እንዲተሳሰቡ ማስተማር ያለብን እኛው ነን። የሩቅ ቤት ሲቃጠል እያየች አያገባኝም ብላ የፈነጠዘችው እንቁራሪት፣ እንደስሟ ባለመራራቷ እሳት ውስጥ ከገባችበት ስነቃላዊ ታሪክ ልንማር ግድ የሚለን ጊዜ ላይ እንገኛለን።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com