የእለት ዜና

የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ ሊመዘገብ መሆኑ ተገለጸ

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ መዘጋጀቱን አስታወቀ።
በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ናቃቸው ብርሌው እንደተናገሩት፣ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በአገራችን ካሉ ትላልቅ ፓርኮች በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገና በርካታ ብዝኃ ሕይወት ያለበት በመሆኑ በዩኔስኮ ለማስመዘገብ የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ ከ50 ዓመት በላይ እንዳስቆጠረው እና እንደ አገር በብቸኝነት በዩኔስኮ እንደተመዘገበው ሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ባሌንም ለማስመዝገብ ታስቧል።
ዓለም ዐቀፍ ዕይታና ትኩረት እንዲያገኝ፣ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቱን በጠበቀ ልክ የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በዓለም ቅርስነት ለማስመዘገብ ታቅዷል ሲሉ ናቃቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እንደ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ፣ የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ለማስመዝገብ ላለፈው አራት ዓመት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ናቃቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት ደረጃዎችን የማሟላት (የኖሚኔሽን ፋይል) ሥራ ተዘጋጅቶ ወደ መጠናቀቁ ደርሷል።

ደረጃዎችን የማሟላት (የኖሚኔሽን ፋይል) ማለት ማንኛውንም የተፈጥሮ ሀብትም ሆነ ቅርስ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የተቀመጠ መሥፈርት ማለት ነው።
አንድ የተፈጥሮ ሀብትም ሆነ ቅርስ በዩኔስኮ ለመመዝገብ የሚያበቃውን ጉዳይ ለመለየትና ለማወቅ የሚያስችል መሠረታዊ መጠይቆችን የሚያሟላ ነው። ይህንን መጠይቅ አሟልቶ በመገኘት ተዘጋጅቶ የሚቀርብ ነው።
ከዚህ ደረጃ በመነሳት የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ምን እንዳለው፣ የት እንደሚገኝ እንዲሁም ወቅታዊ ቁመናው ምን እንደሚመስል የሚያጠና ሠነድ (ዶክመንት) ተዘጋጀቶ መጠናቀቁ ታውቋል።

ፓርኩ በዩኔስኮ ይመዝገብ ሲባል በዋናነት ፓርኩ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መቅረፍ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ናቃቸው፣ በአገራችን የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች የዱር እንስሳት መጠለያዎች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ቁጥር የተፈጥሮ ሀብት ፍላጎት ከፍ እንዲል በማድረጉ ፓርኮቹ ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።

እንደ ግጦሽ፣ እርሻ፣ ደን ጭፍጨፋ እና ምንጠራ፣ እንዲሁም ሕገ-ወጥ ሰፈራዎች ከችግሮቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
እነዚህን ሕገ-ወጥ ተግባራት በማስተካከል እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን በማስፋፋት፣ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማድረግ ከጎባ ወደ ዶሎመና የሚወስደውን ቀይ ቀበሮ የሚገኝበትን የፓርኩን ሥፋራ የሚያቋርጥ 100ኪ.ሜ. የሚጠጋ መንገድ በሌላ መንገድ የመቀየር ሥራ ታቅዷል። ለዚህም ደግሞ የአካባቢው አስተዳደሮች ጋር ስምምነት በመፍጠር የዲዛይን ሥራ ተሠርቶ ወደ ተግባር ለመግባት መታቀዱን ናቃቸው ጠቅሰዋል።

ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የቅያስ መንገድ ሥራ በመሠራቱ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ይደርስ የነበረውን ተጽዕኖ በመቀነስ ዩኔስኮ ላይ የማስመዝገብ ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በባሌ ፓርክም ለመተግበር ታቅዷል።
ከዚህ በተጨማሪ በፓርኩ ሌላኛው አቅጣጫ የሚገኘውን ከአዳባ ወደ ዌጌ ሐረና ቀበሌ የሚሄደው መንገድ የፓርኩን ይዞታ እና የተፈጥሮ ሀብቱን የሚጎዳ በመሆኑ አዲስ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ በአማራጭ የቀረቡ መንገዶች ለመሥራት ታስቧል ብለዋል።
እነዚህ ኹለት አቋራጭ መንገዶች ምን ያህል ብር እንደሚያስፈልጋቸውና በትክክል መቼ እንደሚጀመሩ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አዲስ ማለዳ መረጃ ማግኘት አልቻለችም።
ባሌ ብሔራዊ ፓርክ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ ቀይ ቀበሮዎችና አእዋፋት የሚገኙበት፣ እንዲሁም መልካም ገጽታ ያለው ትልቅ የሀገር ሀብት መሆኑን ናቃቸው ጠቁመዋል።

ይህን ትልቅ ሀብት የተለያዩ ጥበቃዎቸ እየተደረጉለት ስለሆነ ጥበቃው ውጤት እንዲያገኝና ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን በዩኔስኮ መመዝገቡ ዓለም ዐቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ ያስችለዋል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ቀድሞ ይቆጣጠረው ከነበረው ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1999 ጀምሮ ሲያስተዳድረው የቆየ ተቋም ነው።
በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ማሟላት ከሚገቡ መሠረተ ልማቶች አንዱ ፓርኩን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉና ፓርኩን አቋርጠው የሚሄዱ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ያሉ ዝርጋታዎች በሌላ አቅጣጫ የማዛወር ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉም ናቃቸው አንስተዋል።:
ከዚህ በተጨማሪ ፓርኩ ላይ ሰፍረው የነበሩ ሕገ-ወጥ ነዋሪዎችን 160 ሚሊዮን ብር በመመደብ የማስወጣት ሥራ ተሠርቷል።

እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮች ቀድመው ከተፈቱ ዩኔስኮ ላይ ለማስመዝገብ የሚያግድ ነገር እንደማይኖር ናቃቸው ጠቁመዋል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ 575/ 2000 ከተቋቋመ ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚገኙ የዱር እንስሳትና የመኖሪያ አካባቢያቸውን የሚያለማ ነው።
በአገራችን የሚገኙ ሰሜን፣ ባሌ እና ነጭሳር ብሔራዊ ፓርኮች በዓመት እስከ 60 ሺሕ ቱሪስቶች ያስተናግዱ የነበረ ቢሆንም፣ የኮቪድ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ከፍተኛ መቀዛቀዝ ታይቷል። በመቀጠልም የአገሪቷ ሠላም ማጣት በተለይ ሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ላይ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት እንዲቀነስ አድርጓል ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!