የእለት ዜና

በአዲስ አበባ የሚገኙ መምህራን የኮቪድ-19 ክትባት ካልተከተቡ ሥራ ላይ መገኘት አይችሉም ተባለ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙ ኹሉም የግል እና የመንግሥት ትምህርት ቤት መምህራን እና ሠራተኞች የኮቪድ-19 ክትባት ካልተከተቡ ሥራ ላይ መገኘት እንደማይችሉ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በቀን 25/12/2013 በጻፈው ደብዳቤ፣ በከተማዋ በሚገኙ ኹሉም የግል እና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላሉ መምህራን እና ሠራተኞች ከነሐሴ 28/2013 እስከ ጳጉሜ 5/2013 ድረስ በዘመቻ ክትባቱ የተሰጠ መሆኑን ጠቅሶ፣ በዚህ መሠረት በኹሉም የግል እና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ መምህራን እና ሠራተኞች የኮቪድ-19 ክትባት የመከተብ ግዴታ እንዳለባቸው እና ክትባቱን ተከትበው የማረጋገጫ ሠርትፍኬት የማያቀርቡ ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው መግባት እንደማይችሉ ያስጠነቅቃል።

አዲስ ማለዳ እንደተረዳችው፣ ደብዳቤው ለኹሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳ ትምህርት ቢሮዎች የተላከ ሲሆን፣ በይዘቱም ያልተከተበ ማንኛውም ሠራተኛ ወደ ትምህርት ተቋማት አገልግሎት ለመስጠት መግባት የማይችል መሆኑን የሚገልጽ እንደሆነ አረጋግጣለች። በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክትር ዮሐንስ ጫላ፣ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በመወያየት እና አዲስ የኮቪድ-19 ክትባት መድረክ (ፕላትፎርም) በማስቀመጥ በከተማዋ የሚገኙ ኹሉም መምህራን እና ሠራተኞች ክትባቱን እንዲወስዱ ስምምነት ላይ መድረሱን ጠቅሰዋል። አያይዘውም በተለይ አሁን የተከሰተው አዲሱ እና ዴልታ ቫይረስ በመባል የሚታወቀው ዝርያ በስፋት እየተሠራጨ የሚገኘ እና ወጣቶችንም ጭምር የሚያጠቃ በመሆኑ፣ ክትባቱን ለኹሉም በከተማዋ ለሚገኙ መምህራን ለመስጠት እየሠሩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

ዶክተር ዮሐንስ፣ በከተማዋ ከ60 ሺሕ በላይ መምህራን እንደሚገኙ እና የሥራ ባህሪያቸው ደግሞ ከብዙ ተማሪዎች ጋር የሚያገናኛቸው በመሆኑ ክትባቱን መከተባቸው አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፣ በአሁኑ ሰዓት በፍጥነት እየተዛመተ የሚገኘውን እና ወጣቶችን በስፋት እያጠቃ ያለውን አዲሱን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ለመቀነስ ታስቦ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ደብዳቤው ማንኛውም በየትምህርት ተቋሙ የሚሠራ መምህርም ሆነ ሠራተኛ የኮቪድ-19 ክትባት የወሰደበትን የማረጋገጫ ሠርትፍኬት ካልያዘ ወደ ተቋሙ አገልግሎት ለመስጠት መግባት የማይችል መሆኑን እና ክትባቱን መከተብ ግዴታ መሆኑን የሚያስጠነቅቅ ይዘት ያለው ስለመሆኑ አዲስ ማለዳ ለጤና ቢሮ ኃላፊው ላቀረበችው ጥያቄ፣ “ክትባቱን ለመስጠትም ሆነ ለመከተብ የመምህራን ፈቃድ መጠየቅ የለበትም፤ ይህም የሆነው ከወረርሽኙ አሳሳቢነት የተነሳ ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ መሰል ወረርሽኞች በተለያየ ጊዜ የተከሰቱ ቢሆንም፣ በቀጥታ በሽታውን ለመከላከል የተገኘ ክትባት ግን በታሪኳ አልነበረም። ስለዚህ ሕብረተሰቡ ይህንን ሁኔታ በመገንዘብ ክትባቱን እንዲወስድ የተመቻቸለትን ዕድል መጠቀም አለበት እንጂ፣ ቅሬታ ማንሳት ተገቢ አይደለም” በማለት በተለይ መምህራን የተማሪዎቻቸውን ጤንነት ለመጠበቅ እና እራሳቸውንም ከወረርሽኙ ለመከላከል ሲባል ክትባቱን መከተባቸው መልካም እንደሆነ ተናግረዋል።

ክትባቱን በግዴታ መከተብ እንዳለባቸው የተነገራቸው አንዳንድ መምህራን እና ሠራተኞች በበኩላቸው፣ ክትባቱን በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት መዉሰድ እንዳለባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ለዚህም እነደምክንያት ያቀረቡት ከመምህራን እና ሠራተኞች መካከል የተለያዩ ተጓዳኝ በሽታዎች ያሉባቸው መኖራቸውን በመጥቀስ እና የኮቪድ-19 ክትባት ደግሞ ችግሩን የሚያባብስባቸው መሆኑ ነው። የተላከው ደብዳቤ የኹሉንም ፈቃደኝነት እና ያሉባቸውን ተያያዥ ችግሮች ያላማከለ በመሆኑ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ነው መምህራኑ ለአዲስ ማለዳ የጠቆሙት።
አዲስ ማለዳ የመምህራን እና ሠራተኞችን ቅሬታ በመያዝ ጉዳዩን ለአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ለማቅረብ እና ቢሮው በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን አቋም እና በተነሳው ቅሬታ ላይ የሚሰጠውን ምላሽ ለማግኘት ጥረት ብታደርግም ሳይሳካላት ቀርቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!