የእለት ዜና

በአማራ ክልል በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች የማገገሚያ ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ

Views: 83

በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ባደረሰው ጥቃት የተጎዱ የተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች መልሰው ማገገም እንዲችሉ ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ግብርና ቢሮው በሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ዋግኸምራ አካባቢዎች ጦርነቱ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የገለጸ ሲሆን፣ ሰብልን በተመለከተ በዋናነት ሦስት ዕቅድ መነደፉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተስፋሁን መንግስቴ ገልጸዋል።

ተስፋሁን እንደተናገሩት ከሆነ፣ በመጀመሪያ አብበውና አፍርተው በፍጥነት የሚደርሱ እንደ አተር፣ ጓያና በቆሎ አይነት ሰብሎችን ሰብስቦ፣ በትንሽ ዝናብ ለፍሬ የሚበቁ እንደ ሽምብራና ጤፍ አይነት ሰብሎችን በመዝራት የዳግም ማሻሻያ ዕቅድ መያዙን ነው ያብራሩት።
በግብርና ቢሮው በኩል በኹለተኛ ደረጃ የተያዘው ዕቅድ ወንዞች በቅርብ በሚገኙባቸው ማሳዎች ያለውን ሙሉ ውኃ አሟጦ ለመስኖነት መጠቀም ሲሆን፣ በሦስተኛ ደረጃ የተያዘው ደግሞ በኹሉም አካባቢ ያሉ ሰብሎች ከተሰበሰቡ በኋላ በልግ በመዝራት የምርት ዕጥረትን መቅረፍ የሚያስችል እቅድ መንደፍ መሆኑን ምክትል ኃላፊው ጠቁመዋል።

አክለውም መስኖ የመጠቀም ዕቅዱ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በሠነዘረው ጥቃት ምክንያት በዘር ሳይሸፈኑ ፆም ባደሩ ማሳዎች ምክንያት የሚከሰተውን የምርት ዕጥረት ለማካካስ ያስችላል ብለዋል።
የተፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን ዕቅዱን አጠናቅቄያለሁ ያለው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ፣ ኹሉንም የመስኖ ውኃ አማራጮች አሟጦ በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ የጓሮ አትክልቶችን፣ ቅጠላቅጠሎችን፣ ሽንኩርትና ቀይ ሥር የመሳሰሉ ሥራሥሮችን ለማምረት መወሰኑን ነው የገለጸው።

ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቅረፍ በአቅራቢያቸው ወንዝ ያለባቸውን ቦታዎች እና ምንም ሰብል የሌለባቸው ማሳዎችን አጥንተናል ያሉት ተስፋሁን፣ ጥናቱ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህውሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎችም ነጻ ሲወጡ በሒደት ይቀጥላል መባሉን ነው ለአዲስ ማለዳ ማረጋገጥ የቻሉት።

ዕቅዱን በመስከረም ወር እንተገብራለን ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ ዕቅዱን ሥራ ላይ ለማዋል የግብርና ሚኒስቴርና የክልሉን መንግሥት ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
በጦርነቱ ምክንያት መጋዘን ተከማችተው የነበሩ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶች፣ ምርጥ ዘሮችና ማዳበሪያዎች መዘረፋቸውንና ከጥቅም ዉጭ መሆናቸውን የጠቆመው ግብርና ቢሮው፣ የዳግም ማካካሱን ሥራ ለመሥራት ሰፊ የዘርና ማዳበሪያ አቅርቦት ያስፈልጋልም ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ጠላት በለቀቃቸው በሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደርና ዋግኸምራ አካባቢዎች እንዲሁም በሒደት በሚለቃቸው ሌሎች ቦታዎች በአካል በመገኘት የሥነ ልቦና ግንባታ በማድረግ፣ ’’ርሃብ፣ትግል፣ ዝናብ ተፈራርቆበት’’ የሚገኘውን ማኅበረሰብ እንዲያገግም የማድረግ ሥራ እንደሚያከናውኑም አብራርተዋል።

የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ እንደገለጸው ከሆነ፣ በሽብርተኝት የተፈረጀው ህወሓት ጥቃት መሠንዘር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ፣ በሰሜን ጎንደር፣ በዋግኸምራ፣ በሰሜን ወሎ እና በደቡብ ጎንደር ዞኖች በተለይም በግብርና ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንዳጋጠመ ተናግረዋል።
በሰብል ያልተሸፈኑ ማስዎች እንዳሉ ሆነው፣ ጦርነቱ ከመፈጠሩ በፊት የተዘሩት ቡቋያዎች በተባይና በእንሰሳት ከመጥፋታቸው በተጨማሪ በጦርነቱ መውደማቸውን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

ግብርና ቢሮው አያይዞም በጦርነቱ ለግብርና የሚያገለግሉ መሠረታዊ ልማቶች መፍረሳቸውን፤ በሬዎችና ሌሎች እንሰሳት መታረዳቸውን እና ከመበላት የተረፉት መገደላቸውን፣ የመኸር ሽንኩርት ማሳ ላይ መውደሙን፣ እንዲሁም ጤና ጣቢያዎችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መፍረሳቸውን የገለጹ ሲሆን፣ እነዚህን ለማቋቋም ከመንግሥት ጋር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።

ጦርነቱ አሁንም ገና ያልተቋጨ በመሆኑ ውድመት የደረሰባቸው ቁሶች መጠን በዕቅዱ መነሻነት ጥልቅ ጥናት ከተካሄደባቸው በኋላ እንደሚገለጽም የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጠቁሟል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com