የእለት ዜና

የ ‘Ethiopian Business Review’ 100ኛ እትም እንዲሁም የ’ቻንፕየን ኮምዩኒኬሽንስ’ 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በድምቀት ተካሄደ

የ ‘Ethiopian Business Review’ መፅሄት፣ የአዲስ ማለዳ ጋዜጣ እና የአዲስ ማለዳ መፅሄት አሳታሚ የሆነው ‘ቻንፕየን ኮምዩኒኬሽንስ’ 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እንዲሁም የ ‘Ethiopian Business Review’ (EBR) 100ኛ እትም የምስጋና መርሃ ግብር በትናንትናው ዕለት በራድሰን ብሉ ሆቴል በድምቀት ተከናውኗል።

በመርሃ ግብሩም ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ምክር ቤት የስራ አስፈፃሚ ሰብሳቢ አማረ አረጋዊ፣ ከፍተኛ የመንግስት ኅላፊዎች፣ አጋር ድርጅቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የ’ቻንፕየን ኮምዩኒኬሽንስ’ መስራች አማንይሁን ረዳ ስለ ድርጅቱ አመሠራረትና አጠቃላይ የስራ ሂደት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

‘Ethiopian Business Review’ (EBR) በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማጎልበት የሚያግዙ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ አላማው አድርጎ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ሥራ የጀመረ መሆኑን የገለፁት አማንይሁን መፅሄቱ በ10 ዓመታት የህትመት ጉዞው የተለያዩ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ በአገራችን የኢኮኖሚ እድገት ላይ የራሱን የሆነ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሚድያዎች ብዙ ፈተናዎችን ውስጥ አልፈዋል፤ በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ አልፎና ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ለውጤት መብቃት ደግሞ ከፍተኛ ድል ነው።” ያሉ ሲሆን፤ በተለይም የግል የመረጃ ሰጪ ተቋም ሆኖ ይህን ያህል ዓመት በህትመት ላይ መቆየት በራሱ ከፍተኛ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም “መፅሄቱ በአሁን ወቅት 100ኛ እትሙ ላይ ቢገኝም፤ በጥረትና በቁርጠኝነት ከተሰራ 100ኛ ዓመትም ቢሆን መድረስ ይቻላል።” ብለዋል።

የ’ቻምፕየን ኮምዩኒኬሽንስ’ ዋና ሥራ አስኪያጅ ታምራት አስታጥቄ በበኩላቸው የመፅሔቱ 100ኛ እትም የመድረስ ጉዞ ቀላል እንዳልነበር አውስተዋል። ይልቁንም በኢትዮጵያ ካለው ያልዳበረ የንባብ ልምድ እንዲሁም ብዙዎች በጅምር በሚያቋርጡበት ሁኔታ ላይ፤ ዘልቆ ዓመታትን መቆየቱ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

አያይዘውም በድርጅቱና አጠቃላይ የህትመት ሂደቱ ላይ የገጠሙ ተግዳሮቶችን አንስተዋል። ከእነሱ ውስጥም መፅሄቱ በእንግሊዘኛ ቋንቋ እንደመዘጋጀቱ ውስን የኅትመት መጠን፣ ኋላ ቀር የስርጭት ስርዓት፣ የኅትመት ዋጋ በየወቅቱ መናርና የጋዜጠኞች የሙያ ብቃትና በህትመት ሚዲያው ላይ የተፈለገውን ያህል ያለመቆየትን ችግር ጠቅሰዋል።

“የ ‘Ethiopian Business Review’ (EBR) የአዲስ ማለዳ ኅትመቶቻችንን የበለጠ ተደራሽ፣ ታማኝ የመረጃ ምንጮች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆነው እንዲቀጥሉ ለማስቻል፤ እንዲሁም ከዲጂታል ዓለም የሚገኙ መልካም አጋጣሚዎችንም ለመጠቀም የዲጂታል ክፍላችንን የበለጠ በማጠናከር ላይ እንገኛለን።” ያሉት ታምራት በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ለውጦችን ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

በንግግራቸውም ለመገናኛ ብዙኀን መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ “እንደተቋም ለጋራ ፍላጎት ራስን ማደራጀትና መንግሥትም ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት እንዲጨምር ተፅዕኖ ማሳረፍ ይገባል።” ሲሉ ተናግረዋል።

የ10ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና የምስጋና መርሃ ግብሩም ለአጋር ድርጅቶችና በመፅሄት እትመቱ ላይ እስከአሁን ድረስ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና ሰርተፍኬትና ዋንጫ ሽልማት በመሰጠት ተጠናቋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!