የእለት ዜና

የቡድን 20 የበይነ ሃይማኖት ጉባኤ የሃይማኖት ተቋማትን አሳሰበ

በአለም ላይ የሚከሰቱ ግጭቶች፣ ቀውሶችና አለመግባባቶች እንዲፈቱ የሃይማኖት ተቋማት ከጸሎት ባለፈ ተጨባጭና ውጤታማ ተግባራትን እንዲያከናውኑ የቡድን 20 የበይነ ሃይማኖት ጉባኤ ማሳሰቡ ተገለጸ።

“ሐይማኖቶችን አስተምህሮ በመረዳት በተለያዩ ልዩነቶች መሀል ሰላምን ለማምጣት ጊዜው አሁን ነው” በሚል መሪ ቃል በጣሊያን ቦሎኛ ከተማ ከመስከረም 2 – 4 ቀን 2014 ሲካሄድ የቆየው የቡድን 20 የበይነ ሃይማኖት ጉባኤ ተጠናቋል።

በጉባኤው የተሳተፉት የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ታጋይ ታደለ በጉባኤው የሃይማኖት መሪዎች ከእምነት ባሻገር ባሉ ዓለማቀፋዊ የጋራ አጀንዳዎች ላይ እንዲሰሩ መጠየቁን ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል የኮሮና ቫይረስ ክትባት በእኩልነት እንዲዳረስና ድጋፍ ለሚያሻቸው የአለም ህዝቦች አስፈላጊው እርዳታና ድጋፍ እንዲያገኙ የበኩላቸውን ጥረትና ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተጠይቋል ብለዋል።

“ጉባኤው በተለያዩ ሀገራትና አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች፣ ቀውሶችና አለመግባባቶች በዚህም ምክንያት ለችግር ስለሚጋለጡትና ከመኖሪያቸው ስለሚፈናቀሉት ንፁኃን በተለይም ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ በእጅጉ እንደሚያሳስበው” ገልጿል ነው ያሉት።

“ዓለማችን ከዚህ መሠሉ ቀውስ ትፈወስ ዘንድ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች ከጸሎት ባለፈ ተጨባጭና ውጤታማ ተግባራትን እንዲያከናውኑና በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ጉባኤው ማሰሳሰቡን “ሊቀ ትጉኃን ታጋይ ተናግረዋል።

የሀገራት መንግስታትም በዚህ ጉዳይ ላይ ተባባሪ እንዲሆኑ በመድረኩ አጽንኦት እንደተሰጠው ነው የገለጹት።

ከዚህ ባለፈ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የልዑካን ቡድንም በመድረኩ ላይ በመሳተፍ ለቀጣይ ሥራው የሚያግዙ አዳዲስ ሃሳቦችንና ግንዛቤን ከማግኘቱ ጎን ለጎን ተቋሙ ከተለያዩ ዓለማቀፋዊ ተቋማት ጋር በጋራና በትብብር ለመስራት ስለሚችልበት የሁለትዮሽ የትብብር ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል ብለዋል፡፡

በቀጣይ የጀመራቸውን ተቋማዊ ግንኙነቶችና አጋርነቱን በማጠናከር ተቋሙ በዓለማቀፍ ደረጃ የሚኖረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በቡድን ሃያ ሀገራት የበይነ እምነት ምክር ቤት በአፍሪካ የመጀመሪያው በመሆን መሳተፉ ይታወቃል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com