የእለት ዜና

አፍሪ ኤግዚም ባንክ ለኢትዮጵያ ባንኮች ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ብድር ሊሰጥ ነው

የአፍሪካ ኢምፖርት-ኤክስፖርት ባንክ (አፍሪ ኤግዚም ባንክ) ለኢትዮጵያ ባንኮች ግማሽ ቢሊየን ዶላር ብድር ለማቅረብ ማጽደቁን ይፋ አደረገ።

የአፍሪካ ኢምፖርት-ኤክስፖርት ባንክ (አፍሪ ኤግዚም ባንክ) ለአህገራዊ ንግድ ትስስርና ልማት የማጎልበት ዓላማ በማንገብ በአውሮፓዊያኑ 1993 በግብጽ – ካይሮ የተቋቋመ የፋይናንስ ተቋም ነው።

ኢትዮጵያ መስራችና ባለድርሻ የሆነችበት አፍሪካ ኤግዚም ባንክ 51 የአፍሪካ አገራት በአባልነት አቅፏል።

የአፍሪ ኤግዚም ባንክ የደንበኞች ግንኙነት ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ረኔ አዋምበንግ እንዳሉት፤ ባንኩ ከሌሎች አፍሪካዊ ባንኮች ጋር መወዳደር ሳይሆን በፋይናንስ ዘርፍ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ለመፍታት ይሰራል።

እስካሁንም ከ25 ቢሊዮን ዶላር በላይ በአፍሪካ ንግድ ፋይናንስ ዘርፍ ለፕሮጀክቶች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
ላለፉት ዓመታት በአፍሪካ መንግስታት ፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ ድጋፍ ሲያደረግ መቆየቱን ገልፀው፤ ባንኩ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለተመታው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማገገሚያም ሶስት ቢሊዮን ዶላር ለባንኮች ድጋፍ መስጠቱን ተናግረዋል።

አሁንም ተጨማሪ ለጸረ ኮቪድ ክትባት ግዥ የሚውል ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማቅረብ ከአፍሪካ ህብረትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ውድቀት ውስጥ ሆነው በፈጣን ለውጥ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከ110 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ ምቹ ገበያ እንደሆነች ገለጸው፤ ባንኩ በፓን አፍሪካ ማዕቀፍ የአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረግ የንግድ ልውውጥ እንዲሰጥ ድጋፍ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የተዘጋጀው መድረክ ዓላማም ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር ስለመሆኑ አንስተዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት አጀንዳዎች ማስፈጸም በሚያስችሉ ዘርፎች ለመደገፍ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ባንኮች 500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ባንኩ ውሳኔ ማሳለፉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ባንኩ ካሁን በፊት በኢትዮጵየ በአጠቃላይ በተለያዩ ዘርፎች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

በመስከረም መጨረሻም ሁሉም ሂደቶች ከባንኮች ጋር ከተፈጸሙ በኋላ ብድሩ እንደሚቀርብም ግምታቸውንም የገለፁ ሲሆን፤ ለእያንዳንዱ ባንክ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚቀርብላችውም አሳውቀናል ብለዋል።

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com