የእለት ዜና

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የአንድ – አለቅ የድንበር አገልግሎት ስምምነት ለመስማማት በዝግጅት ላይ ናት

ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችላትን፤ የአንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት ስምምነት ከኤርትራ ጋር ለመስማት በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ተገለፀ።

ይህ የተባለው ኢትዮጵያና ኬኒያ የሞያሌ አንድ – አለቅ የድንበር አገልግሎት ማዕከልን ወደ ስራ ለማስገባት የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረሙበት ሥነ ሥርዓት ላይ ነው።

በሥነ ሥርዓቱ ላይም የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ካቤታ “እኛ የጉምሩክ ፕሮቶኮል አዘጋጅተናል። የኢትዮጵያ መንግሥት አስቀድሞ፤ ለኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስገብቷል። በኢትዮጵያ በኩል እያንዳንዱን ዝግጅት አጠናቀን፤ ከኤርትራ በኩል ምላሾችን በመጠባበቅ ላይ ነን” ሲሉ ተናግረዋል።

የአንድ – አለቅ የድንበር አገልግሎት ማዕከል የድንበር ነክ ጉዳዮችን የሚቆጣጠሩ የመንግሥት ተቋማትና ሰራተኞች የተቀናጀ የድንበር አስተዳደር ሥራዎችን በተሳካ መልኩ መተግበር እንዲችሉ የሚያስችል ነው።

በተጨማሪም ነጋዴዎች፣ የጭነት አገልግሎት አቅራቢዎች ወይም አጓጓዦችና ሌሎች መንገደኞች ድንበር አቋርጠው ለመሻገር የሚያልፉባቸውን ሂደቶችን ቀላል፣ ፈጣን እና ወጪ ቆጣቢ እንዲሆኑ በማድረግ የድንበር ተሻጋሪ እንቅስቃሴዎችን የተቀላጠፉ እንደሚያደርግም ታምኖበታል።

ኢትዮጵያ የሞያሌው ስምምነት ከተሳካ በኋላ ተመሳሳይ የድንበር አገልግሎት ማዕከሎችን ከሱዳን፣ ከሶማሊያ እና ከጅቡቲ ጋር ለማቋቋም አቅዳለች።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 90 በመቶ የሚሆነው የውጭ ንግዷን በጅቡቲ በኩል የምታካሄድ ሲሆን በኬንያ፣ በሶማሊያ፣ ሶማሊላንድ፣ ሱዳን እና ኤርትራ የወደብ መዳረሻዎች በኩል የውጭ ንግዷን ማካሄድ ብትችል በጅቡቲ መስመር ያለውን መጨናነቅ ይቀንሰዋል ተብሏል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!