የእለት ዜና

በ25 ሚሊዮን ብር 5 መኪና ለኃላፊዎቹ የገዛው ኢቢሲ ከሠራተኞቹ 40 ሚሊዮን ብር ቆረጠ

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት የአንድ ወር ደሞዝ መለገስ ግዴታችሁ ነው መባላቸው ቅሬታን አስነስቷል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ከሆነ የዝቅተኛ ደሞዝ ተከፋዮችን ባላገናዘበ መልኩ የአንድ ወር ደሞዝ ሊወሰድ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። “የኛን የደሀዎቹን ደሞዝ ከሚወስዱ ለአመራሮች ቅንጡ መኪና የተገዛበትን 25 ሚሊዮን ብር እና ለተለያዩ ወጪዎች የሚጠቀሙትን ገንዘብ መጠቀም ይችሉ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

የ2021 ምርት የሆነ ሀዮንዳይ ቱክሰን (Hyundai Tucson) የተባለ፣ የአንዱ ዋጋ አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ዘመናዊ መኪና ለአምስት አመራሮች ተገዝቷል። በጥቅሉ ግዥው 25 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን፣ አሁን አገሪቷ ካለባት የውጭ ምንዛሬ እና የበጀት ዕጥረት አኳያ ቅንጡ መኪና መግዛት የሚኖርበት አይመስለንም ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል።

ለመከላከያ ሠራዊት እና ለተፈናቃዮች ገንዘብ እንደሚያስፈልግ እየታወቀ፣ ተቋሙ መሠረታዊ ግብዓቶች ዕጥረት እያለበት፣ እንዲሁም ለመደበኛ ሠራተኛው ለሥራ የሚያስፈልገው የትራንስፖርት አገልግሎት ባልተሟለበት ሁኔታ ለአመራሮች የተገዛው እጅግ ውድ መኪና ቅር አሰኝቶናል ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በጷጉሜ ወር ላይ በኢትዮጵያ ሆቴል በተደረገ ስብሰባ የተቋሙ ሠራተኞች በ2014 አንድ ዓመት ውስጥ የአንድ ወር ደሞዛቸውን እንዲሰጡ ግዴታ ተጠሎባቸዋል።
ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋዮችን ብቻ ያካተተ ስብሠባ በኢትዮጵያ ሆቴል ተካሒዶ ነበር የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ ውሳኔው ያለውን የኑሮ ውድነት እና ዝቅተኛ ደሞዝ ተከፋዮችን ያላገናዘበ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢቢሲ በአንድ ወር ውስጥ ለሠራተኞች ደሞዝ የሚያወጣው ወጪ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑ ይታወቃል።

የአራት ሺሕ ብር ደሞዝተኛ የሆኑት እና ሦሰት ልጆች ያላቸው አንድ የተቋሙ ሠራተኛ፣ የቤት ኪራይ 2500 ብር እንደሚከፍሉ ቢናገሩም፣ ምንም ተሰሚነት ሳያገኙ የአንድ ወር ደሞዝ መስጠት የማይችል ካለ ተቋሙን ለቆ ይውጣ በሚል የግዴታ ልገሳ አድርጉ መባላቸውን ገልጸዋል።

ለመከላከያ ሰሠዊት ድጋፍ መደረግ እንዳለበት እናምናለን የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ ድጋፉ በበጎ ፈቃድ መሆን ነበረበት ብለዋል።
የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የነበሩት ንጉሴ ምትኩ (ዶ/ር) ከኹለት አመት በፊት የኢቢሲ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ በመሆን መሾማቸው ይታወቃል።

በወቅቱ የተቋሙን አሠራር ያሻሽላል የተባለለትን ጥናት ለማጥናት ተቋሙ ሰባት ግለሰቦችን በመምረጥ ከፍተኛ ዶላር ፈሰስ አደርጎ ያስጠናው ጥናት መኖሩን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል። ይህ ጥናት ሙያና ሙያተኛውን ያገናኛል፣ እንዲሁም አዲስ መዋቅር ይፈጥራል በሚል የተሠራ ነው። በተጨማሪም በጥናቱ በተቋሙ ከ2300 ሠራተኛ በላይ ቢኖርም በሠራተኛው ብዛት ልክ የሥራ ውጤት ባለመኖሩና ያለሥራ የሚቀመጠው ሠራተኛ በርካታ በመሆኑ አሠራሩን ለማስተካከል ያለመ ነበር። ነገር ግን፣ ጥናቱ ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ የተለያዩ ወቅታዊ ኹኔታዎችን ሰበብ በማድረግ ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የአገሪቱ መሪ ከመሆናቸው በፊት የኢቢሲ ቦርድ አባል እንደነበሩ የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ የተቋሙን የመልካም አሥተዳደር ችግር በቅርበት ከሚያውቁ ሰዎች አንዱ ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም የተቋሙን ክፍተት ያልተመለከቱት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ተወጥረው እንጂ የሠራተኞችን ቅሬታ በደንብ የተገነዘቡ ናቸው ብለዋል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት በአንድ ወቅት ዋቢ ሸበሌ ሆቴል በተካሄደ አጠቃላይ የሠራተኞች ስብሠባ ላይ ተነስቶ የነበረውን ቅሬታ ተገንዝበውት ነበር ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎች አስታውሰዋል።

ይህንን ቅሬታ የሰማችው አዲስ ማለዳ ጥያቄውን በመያዝ ወደ ኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ንጉሴ ምትኩ (ዶ/ር) ጋር የደወለች ሲሆን፣ ጉዳዩን ከሰሙት በኋላ ምላሽ ሳይሰጡ ስልኩን አቋርጠውታል። በመቀጠልም የዋና ሥራ አስፈጻሚው የጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ታከለ ኩየራ ጋር ብትደውልም ቅሬታውን ከሰሙ በኋላ ምላሽ ሳይሰጡ መልሳችሁ ደውሉልኝ በማለት ስልኩን ዘግተውታል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 3

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

  1. The cars are normally sold for 4.25 million. Obviously there was no transparent bidding process. It’s a shame the govt is wasting resources in such time of challenge.

error: Content is protected !!