የእለት ዜና

የሴትነት ክብር!

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

በዚህ ዘመን ሴት ልጅ መከበር እንዳለባት የማያምን ትውልድ የለም ማለት ይቻላል። የእኩልነትና ጉዳይ ላይ ሲመጣ ግን ሙግት ይነሳል። ለሴት ልጅ የሚሰጠው ክብር በምን መንገድ መሆን አለበት የሚለው ብዙዎችን እያወያየ መሆኑም ይሰማል። በሠው ልጆች መካከል በፆታ፣ በዘርም ሆነ በኃይማኖት መድሎ መደረግ እንደሌለበት ግልፅ ነው። ሆኖም ሴቶች ላይ ሲደርስ የነበረን መድሎ ለማካከስና እኩል መደላድል እስኪፈጠር ሴት የበለጠ ክብርና እንክብካቤ ትሻለች የሚሉ አሉ።

ሴት ልጅ በቤት ውስጥ አሁንም ድረስ በሚኖርባት ተፅዕኖ ምክንያት ስለምትጎዳ በትምህርትም ሆነ በሥራው ዓለም ጉዳቷን ለማካካስ ልዩ ትኩረትም ሆነ ድጋፍ ሊደረግላት እንደሚገባ የሚያምኑ በርካቶች ናቸው። በተቃራኒው እኩልነት ማለት ማስበለጥ መሆን የለበትም በማለት እኩል የሆነ መሥፈርትና መመዘኛ መኖር እንዳለበት የሚናገሩ ይገኛሉ።

የእኩልነት መስመሩ በግልፅ ሊሰመር ባለመቻሉ፣ እንዲሁም ይሔ ነው ተብሎ የማብቂያው ጊዜ ባለመቀመጡም ሒደቱ ሴቶች በዘላቂነት የበታችነት እንዲሰማቸውና ራሳቸውን ያነሱ አድርገው እንዲመለከቱ ያደርጋል በሚል አስተሳሰቡን የሚተቹት አሉ። ሴት በተፈጥሮ ከወንድ ብትለይም እኩል ናት ብሎ ወንድን ማነጻጸሩን ራሱ ትክክለኛ አካሄድ አለመሆኑን የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። ወንድ ከሴት እኩል ነውም ሳይባል፣ ልዩነት የላቸውም በማለት መድሎ እንዳይፈጸም ከአስተሳሰቡ ጀምሮ ሊታሰብበት እንደሚገባ የሴቶች መብት እንቅስቃሴ መሪዎችና ቀስቃሾች አበክረው ይናገራሉ።

ሴትና ወንድ የተለያየ ተፈጥሯዊ ልዩነቶች ቢኖራቸውም፣ ለመስፈርትነትም ሆነ ለመለያ ሕጋዊ ሆኖ መወሰድ እንደሌለበት ይታመናል። በአስተሳሰብ ረገድ ሴት ብልጫ የምታሳይባቸው ኹኔታዎች እንዳሉ የሥነልቦና ባለሙያዎች ቢናገሩም፣ ይህ አይነት ሳይንሳዊ ልዩነቶችም ቢሆኑ ለመድሎ መንስዔ መሆን የለባቸውም። ለምሳሌ፣ እንክብካቤን በተመለከተ ሴት የተሻለ ትንከባከባለች ቢባልም በዘርፉ ወንድ ከማገልገል ሊገደብም ሆነ ልዩነት ሊፈጠርበት እንደማይገባ ይታመናል።

በሌላ በኩል፣ ጭራሹኑ ወንድ የበላይ አልነበረም፤ እንደውም ተበድሏል ብለው የሚያምኑም ምክንያታቸውን ሲያስረዱ ይሰማሉ። በሰው ልጆች ታሪክ ከባዱ ሥራ የተተወው ለወንድ ነው። በጦርነት የሚያልቁት አብዛኞቹ ወንዶች ናቸው፤ በየትኛውም ጊዜና ቦታ የወንድ እስረኞች ቁጥር ከሴቶቹ የሚቀራረብ አይደለም፤ እንዲሁም ወንዶች ሴቶችን ሲንከባከቡ ነው የኖሩት በሚል ጥቂት ወንዶች አብዛኛውን የዓለማችንን ሀብት ስለተቆጣጠሩት ብቻ ሥማቸው ሊጠፋ አይገባም ብለው ይናገራሉ።

አንዳንዶች ደግሞ ሴቶች እኩል ነን ብለው ካሰቡ ወንበር እንድንለቅላቸውና አደጋ ሲመጣ እንድናስጥላቸው ሊጠብቁ አይገባም ይላሉ። ኹለት ወዶ አይሆንም ይምረጡ የሚሉ እንዲህ አይነት ወንዶች ብቻቸውን ሳይሆኑ ሐሳባቸውን የሚጋሯቸው ሴቶችም አሉ።
እኩልነት በወሬ ብቻ ሳይሆን በተግባር መሆን አለበት የሚሉ በርካቶች ቢሆኑም፣ እንደ ምርጫ መሆን ይገባዋል የሚሉም አሉ። ፈቅዶ መብቱንም ሆነ ድርሻውን የሚሰጥን በግድ አስመልሰህ ውሰድ ብሎ ማስገደዱ በራሱ ሌላ ወንጀል ሊሆን ስለሚችል፣ የፈለገ እኩል ሆኖ እየተጋፋ፣ ያልፈለገ ደግሞ ልዩ ነኝ ብሎ የተሻለ እንክብካቤን በፍላጎት እንዲያገኝ ለኹሉም ፍትሐዊ የሆነ ዕድል ተመቻችቶ እንደፍላጎት ብንጠቀምበት የተሻለ ይሆናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!