የእለት ዜና

ትምህርት ሚኒስቴር በአማራ ክልል የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ለማቋቋም የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀው ህወሓት ወረራ ምክንያት በአማራ ክልል የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም የትምህርት ሚኒስቴር 100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን በአማራ ክልል በፈጸመው ጥቃት ከኹለት ሺህ 950 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገልጸዋል። በጉዳቱም ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ ተገደዋል ብለዋል።
“እብሪት የወለደው ድንቁርና ሕፃናት በወርኃ መስከረም እንዳይማሩ አድርጓል” ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ ችግሩን የከፋ የሚያደርገው በጦርነቱ ወላጆቻቸውን ያጡ እና የተጎዱ ሕፃናት መኖራቸው ነው ብለዋል።
ችግሩን ከስር ከስር መፍታት እና ማቃለል አሰፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል ያሉት ሚኒስትሩ፣ በመደበኛ ከሚደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ትምህርት ቤቶቹን ለመጠገን 100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል ሲሉ ነው የገለጹት።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com