የእለት ዜና

የ”ላይክ” አባዜ

ፌስቡክና መሰል ማኅበራዊ ድረ-ገፆች በአገራችን ጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩ ወዲህ የሰውን ባህሪ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ የተለያዩ ተግባራትን እያስተዋልን እንገኛለን። ከእነዚህ መካከል የትኩረት ፍለጋ መገለጫ የሆነ፣ የሰውን ቀልብ ለመያዝና ላለመረሳት የሚደረጉ ጥረቶች ግንባር ቀደሙን ቦታ ይይዛሉ። በተለይ ፌስቡክ ይበልጥ ጥቅም ላይ ሲውል የእያንዳንዱ ተጠቃሚውን ባህሪ ሳንፈልግ ባለንበት ማሳየት ጀምሯል።

በፌስቡክ “ላይክ” ለማግኘት ሲባል አሁን አሁን የማይፈነቀል ድንጋይ የለም። ዘግናኝ ነገሮችን ከማሳየት ጀምሮ፣ ነውር የሆነን ተግባር ባህል እየተጣሰ ይፋ ሲደረግ ይታያል። አንዳንዴም ለወሬ ሲባል ብቻ እንቅልፍ የሚያጡ የመኖራቸውን ያህል፣ የመጀመሪያ የወሬ ሰባሪ ለመሆን ብለው አላግባብ ጊዜያቸውን ኮምፒውተር ላይ አፍጠው የሚያሳልፉ አሉ። ለማኅበረሰቡ ጥቅም ነው በሚል ኹሉም በየፊናው ያመነበትን ማድረጉ ቢበረታታም፣ ለከት ያለፈ ባህላችንን የሚጥስ ተግባር ሲሆን ግን ዝም ተብሎ መታለፍ የለበትም።

የፌስቡክ አጠቃቀምን በተመለከተ በየጊዜው የሚነሱ የተለያዩ አስተያየቶች ቢኖሩም፣ በአጠቃቀም መንገዱ ላይ የሚያጠነጥኑ ትችቶችና ጥቅሞቹ ላይ ያተኮሩ ክርክሮች ናቸው። ማኅበራዊ ድረ-ገፆች ለጥቅም ብለው እንደመሠራታቸው ከጉዳታቸው ይበልጥ መጥቀማቸውን አብዛኛው ቢቀበልም፣ ጭራሹኑ ጥቅሙ የማይታያቸውም አሉ።

ስለፌስቡክ “ላይክ” መወደድ ይህን ያህል ያልናችሁ የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች የሚሉትን ችግሩንና ጥቅሙን ልናመዛዝንላችሁ አይደለም። ይልቁንም ሠሞኑን መነጋገሪያ የሆነውን የዕርዳታ ማሰባሰቢያ ዘዴ ላይ የተባለውን ልንነግራችሁ ነው። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም በሰሜን ወሎ የተከሰተውን ረሃብ ከተቻለ ለማስወገድ ካልተቻለ ደግሞ ለመቀነስ የሕብረተሰቡ ርብርብ የተጠየቀበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

ረሃቡን መቋቋም የሚያስችል ዕገዛ ብዙዎች እያደረጉ ቢሆንም፣ ከችግሩ አድማስ መስፋት አኳያ የሚደረገው በቂ ኹኖ ስላልተገኘ ኹሉም በቻለው መንገድ እንዲያሰባስብና እንዲለግስ ተጠይቋል። ኹሉም አሰባሳቢ ሆኖ የሚለግሰው ሰው ሐሳብ እንዳይበተን የክልሉ መንግሥት ከእኛ ዕውቅና ውጭ መሰብሠብ አይቻልም ቢልም፣ ኹሉም በየዘርፉ ሰብሣቢ መሆኑን ቀጥሏል። የሰብሣቢው መብዛትና ሌላው መከልከሉ ሳይሆን መነጋገሪያ የሆነው፣ በፌስቡክ ፎቶ እየለጠፉ ላይክ ከሰጣችሁኝ ይህን ያህል ብር፣ ሼርና ኮሜንት ከሆነ ደግሞ በቁጥሩ ልክ ይህን ያህል ገንዘብ እንለግሳለን እያሉ የለጠፉ ብዙ መሆናቸው ነው።

በተራበ ሰው ማላገጥ እያሉ ብዙዎች ይህን መንገድ የተቹት ቢሆንም፣ የራሳቸውንም ሆነ የልጆቻቸውን ፎቶ እየለጠፉ አድንቁልንና በዛው ልክ እንለግሳለን ማለታቸውን አላቋረጡም። ሐሳቡን የደገፉትን ያህል ባይሆኑም የኮነኑትም በርካቶች ናቸው። ላይክ ባያገኙ መለገስ እየቻሉ ላይሰጡ ነው? የሚችሉትንስ መጠን ሰው እንዲወስንላቸው ማለት ምን ማለት ነው? እያሉ የላይክ አዳኞቹን ተግባር አሳፋሪ በማለት በርካቶች ገልጸውታል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com