የእለት ዜና

የመተሳሰብ ባህላችንን እየሸረሸረው ያለው የዋጋ ንረት

“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር’’ እንዲሉ የአገራችን ዜጎች አንደኛው ለሌላኛው እንደሚያስፈልገው በማመን የመደጋገፍ ባህልን አንግበው ዕልፍ ዘመናትን እንደሸኙ ይነገራል።
ገበሬው አርሶ፣ ዘርቶ፣ አርሞ፣ ምርቱን ሠብስቦ እንዲሁም አርብቶ በግብርና ዘርፍ ላልተሠማሩ ዜጎች በማቅረብ ብር ሲቀበል፣ በመንግሥትና በግል ሥራ ተሠማርተው በቀንም ሆነ በወር ብር እየተቀበሉ የሚኖሩ ዜጎች በበኩላቸው ምርቱን ይገዛሉ።
ምንም እንኳን ይህ አይነቱ ድርጊቱ አሁንም የቀጠለ ቢሆንም፣ ከዓመት ወደ ዓመት የመተሳሠብና የመደጋገፍ ባህሉ እየቀረ መምጣቱን ብዙዎች ይናገራሉ። በተለይም የፖለቲካ አለመረጋጋቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በየዕለቱ መሠረታዊ አስቤዛዎች ላይ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ የመተሳሠቡን ባህል እያመናመነው እንደሆነ ይስተዋላል።

በአገሪቱ የግብይት ሒደት ውስጥ በመሠረታዊ አስቤዛዎች ላይ ያለው የዋጋ ግሽበት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሔዱን በየአካባቢው ያሉ ማኅበረሰቦች በተደጋጋሚ ሲናገሩ መስማት እየተለመደ መጥቷል።
በዚህም ከመንግሥት ጀምሮ እስከ ታችኛው የሕብረተሰብ ክፍል ድረስ የሚገኙ አካላት በበኩላቸው የኑሮ ውድነቱን በማስመልከት ውይይት ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል።

ምሁራን በበኩላቸው ከመፍትሄው ይልቅ ለዋጋ ንረት መከሰት ምክንያት ስለሆኑ ጉዳዮች አበክረው ሲናገሩ ይደመጣል። በወቅቱ እየተስፋፋ ላለው የዋጋ ግሽበት መከሰት በምሁራኑ የሚጠቀሱ በርካታ መንስኤዎች አልጠፉም።
ከእነዚህም መካከል በየአቅጣጫው በሚገኙ የአገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የዶላር ምንዛሬ መጨመር፣ ዕጥረት ለመፍጠር ሲባል ዕቃዎችን በመካዝኖች ማከማቸት፣ በአምራቹና በሸማቹ መካከል የሚፈጠሩ ክፍተቶችና ተባብሮ ያለመሥራት ችግር ዋናዋናዎቹ ናቸው ይላሉ የኢኮኖሚክስ ባለሙያው ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)።

“ገፈቱን ቀመስን’’ የሚሉ ሰዎች እንደሚገልጹት ከሆነ፣ ከትራንስፖርትና ከቤት ኪራይ ዋጋ በተጨማሪ፣ በየወቅቱ የሚጨምረው የአስቤዛ ዋጋ ሕይወትን በኑሮ ውድነት ቅኝ አገዛዝ ሥር እንደትወድቅ እየዳረጋት የሚገኝ ግንባር ቀደም ችግር መሆኑን ነው።
የኑሮ ዉድነት መኖሩ በተደጋጋሚ ቢወሳም፣ የመፍትሔ መንገዱ ቢቀመጥም፣ ከወሬ አልፎ ተግባር ላይ የዋለ ባለመሆኑ ለችግሩ ሰለባ መሆናችን እየሰፋ እንጅ እየጠበበ አልመጣም የሚሉ ሰዎችም እየተበራከቱ መጥተዋል።

መንግሥት መፍትሔ እንደሚፈልግና ለችግሩ ምክንያት የሚሆኑ አካላትን የማስታመም ትዕግስቱ ያለቀ መሆኑን ቢገልጽም፣ “የኑሮው ውድነት የራስ ምታት ሆኖብናል’’ የሚሉ ሰዎች ቁጥር ግን በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ለማረጋገጥ መዲናችንን እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል።
አዲስ ማለዳ በዚህ ሳምንት ዕትሟ ጉዳዩን በማስመልከት ከተለያዩ አካላት ጋር ቆይታ አድርጋለች። አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ሰዎች መካከል ፍቅር በለጠ የተባሉት እናት የዋጋ ንረቱን በሚመለከት የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።

“በዋጋ ጭማሪ መማረራችንን በተደጋጋሚ ከመናገር አልተቆጠብንም፤ ሆኖም ግን ድካም አተረፍን እንጅ ጠብ ያለልን አጥጋቢ መፍትሔ የለም። እኔ በበኩሌ ተስፋ ቆርጫለሁ። መፍትሔ ካልተገኘ ችግሩን ብቻ መለፍለፉ ምን ይሰራል። ችግሩን አሁን ዘርዝሬ አልጨርሰውም፤ ምክንያቱም ትላንት የገዛሁት ዕቃ ዛሬ ጨምሮ ነው የማገኘው’’ በማለት ነው ምሬታቸውን የገለጹት።

በመዲናችን ሾላ ገበያ አስቤዛ እየሸመቱ ካገኘናቸው ሰዎች መካከል የሆኑት ጥሩዓለም ንጋቱ በበኩላቸው፣ ከኹለት ሳምንት በፊት 20ብር የነበረውን ኪሎ ሽንኩርት በ 40ብር፣ 47ብር የገዙትን ጤፍ በ 70ብር፣ 600ብር የነበረውን ዘይት 670 ብር እንደገዙ ነግረውናል።
አክለውም “ወይ ጉድ ያልጨመረ ነገር ምን ይሆን? ለምን ጨመራችሁ ስንላቸውም ስንረከብ ጨምረውብን ነው የሚሉት። ምን እናድርግ? ኹለት ብር የነበረው ዳቦ እንኳን አምስት ብር ገብቷል’’ በማለት ነው ፊታቸውን በኹለት እጃቸው ይዘው በመገረም የገለጹት።
የፖለቲካ አለመረጋጋቱን ተከትሎ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡና ገዝተው የሚመገቡ ’’የኑሮ ውድነቱ እንደኛ የተጋረጠበት የለም’’ የሚሉ ግለሰቦችም አልጠፉም።

ከወለጋ ተፈናቅለው በመዲናዋ የሚኖሩና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ግለሰብ የዋጋ ግሽበቱ በተለይ የቤት ኪራይና የአስቤዛው ጭማሪ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሆነባቸው ይናገራሉ።
“አንድ እንጀራ በ 10ብር ገዝቼ ነው ከእኔ ጋር የመጡ አምስት ቤተሰቦቼን የማስተዳድረው። ነጋዴዎች ቢያንስ ለተፈናቃዮች እንኳን አስተያየት ማድረግ ሲገባቸው በተቃራኒው እንደመልካም አጋጣሚ ነው የሚጠቀሙብን። በመሆኑም የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል” ሲሉ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

ተባብሮ አለመሥራትን ለዋጋ ንረቱ እንደመንስኤ ያስቀመጡት ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ፣ በተደጋጋሚ ችግሩን ማውራት ብቻውን መፍትሔ ሊሆን አይችልምና ችግሩን ለመቅረፍ በሦስቱ አካላት በኩል (ከሸማቹ፤ ከመንግስት፤ ከነጋዴ) ከወሬ ያለፈ ሥራ መሠራት አለበት ነው ያሉት።

ነጋዴም ቢሆን መንግሥት እስከሚቆጣጠረው ድረስ ከመጠበቅ ሕሊናው ወቅሶት ኹሉንም ያማከለ ሥራ ሊሠራ ይገባል ያሉት ደምስ፣ ማኅበረሰቡም እርስበርስ የመደጋገፍ ባህሉን ቢያስታዉስ የኑሮ ውድነት ይረግባል በማለት ነው ምክራቸውን የለገሱን።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ነጋዴዎችንም ጠይቃለች። ኑራ ካሲም ይባላሉ፤ የሚተዳደሩት በንግድ ሥራ ሲሆን የተለያዩ ዕቃዎችን ከጅምላ ከአከፋፋዮች ተረክበው በችርቻሮ ለማኅበረሰቡ ያደርሳሉ።

ኑሩ ካሲም ’’ምን ያልጨመረ ነገር አለ፤ ነገሮች ኹሉ በየጊዜው እየጨመሩ ነው የሚሄዱት። ከሳምንት በፊት የተረከብናቸውን ዕቃዎች ሽጠን ጨርሰን ድጋሚ ለመረከብ በምንሄድበት ወቅት ዋጋቸው ጨምሮ ነው የምናገኘው’’ ሲሉ ነው የዋጋ ግሽበቱን የገለጹት።
በየጊዜው ጨምሯል የሚለውን ከመስማት ውጭ ቀንሶ የሚያገኙት ዕቃ እንደሌለ አበክረው ይናገራሉ።

ኑራ ቃሲም እንደሚሉት የአስቤዛ ዋጋ መቀነሱ ይቅርና በአንድ ወቅት የተረከቡበትን ዕቃ በድጋሚ ለመረከብ ሲሄዱ ቀድሞ በነበረበት ዋጋ ማግኘት እንዳልቻሉ ነው።
አክለውም ’’ማኅበረሰቡ መጥቶ እኛ ላይ ነው የሚጮኸው። አከፋፋዮችን ስንጠይቅም አቅርቦት የለም ነው የሚሉን። በዚህ ሁኔታ ሕይወትን መምራት በጣም ይከብዳል’’ በማለት ነው የተናገሩት።
በዚህ ሰሞን የተረከቧቸው ዕቃዎችን በፊት ሲረከቡበት ከነበረው ዋጋ ጋር በማነጻጸር ይበልጥ የዋጋ ጭማሪ የተጠየቁባቸውን ዘርዝረዋል።

ይኸውም ከወር በፊት በ 540 ብር ሲረከቡ የነበረዉን ዘይት በ590፤ በ 570ብር የነበረውን አንድ ደርዘን ፓስታ በ 590፤ በ38 ብር ሲረከቡ የነበረውን አንድ ኪሎ ሩዝ በ45 ብር እንደገዙ ተናግረዋል። በዚህም ለደንበኞቻቸው አንድ ሊትር ዘይት በ 140ብር፣ አንድ እሽግ ፓስታ በ 50ብር፣ እንዲሁም ኪሎ ሩዝ በ 50ብር እንደሚሸጡ ገልጸዋል።

አያይዘውም የሚረከቧቸው ዕቃዎች ዋጋቸው መጨመሩ እንዳላቆመና ደንበኞች ’’ኹሌም የዕቃ ዋጋህ ሰማይ እየጠቀሰ ነው እንዴ የሚሄደው’’ የሚል ትችትን እንደሚያቀርቡ ነው የገለጹት።
የኢኮኖሚክስ ባለሙያው ደምስ እንደተናገሩት ከሆነ፣ በየዕለቱ የሚጨምረውን የኑሮ ውድነት ለማርገብ መንግሥት የራሱን ድርሻ መወጣት ቢኖርበትም፣ ጉዳዩን ኹሌም ለመንግሥት ብቻ መተው ሙሉ ለሙሉ ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል ጠቁመዋል።
አሁን የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት መቀነስ የሚቻለው መንግሥት፣ ነጋዴ፤ ሸማቾች እና ገበሬው ተናበው ከሠሩ ብቻ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ትስስሩንም አንደሚከተለው አስቀምጠዉታል።

አንደኛ መንግሥት በሸማቹና በነጋዴው መካከል ያለው ሒደት ሥርዓቱን የጠበቀ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለው ይታወቃል። ስለሆነም፣ የሥራ ሒደቱን እንዲከታተሉ የሚወክላቸው ባለድርሻ አካላት የሥራዉን ሰንሠለት እንዲጠብቁ ከዚህ የተሻለ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

አስፈጻሚ ባለሥልጣናቱ በበኩላቸው፣ መንግሥት እስከሚቆጣጠራቸው ከመጠበቅ ሰብዓዊነትን አንግበው ሥራቸውን የመሥራት ልምድ ማዳበር እንዳለባቸው ነው የጠቆሙት። ከአገር ውጭም ሆነ ውስጥ የሚመረቱ ዕቃዎች የት እንደሚቀመጡ ለአስፈጻሚዎቹ ድብቅ አይደለም፤ ስለሆነም እነዚህን ቦታዎች በተደጋጋሚ መፈተሸ ያስፈልጋል ብለዋል።

በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ ነጋዴው ከአስፈጻሚ ባለሥልጣናቱ ጋር ያለው ቁርኝት ከዚህ የተሻለ ጥብቅ ቢሆንና ነጋዴው አጋጣሚዎችን እየተጠቀመ ከልክ ያለፈ ገቢ ለማግኘት ከመሯሯጥ ይልቅ በልኩ በቃኝ ማለቱ ለኑሮ ዉድነት መቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አውቆ ይህን ተግባር ላይ በማዋል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።

ሦስተኛዉና የመጨረሻው መፍትሔ ደግሞ ሸማቾች ከነጋዴዎች በኩል የዋጋ ጭማሪ ሲገጥማቸው ዝም ብለው ከመቀበል ይልቅ ነጋዴዎችን አልፈው አከፋፋዮችን ቢጎበኙ ችግሩ ከየት በኩል እንዳለ በዚህ ሰንሰለታዊ ሒደት ማወቅ እንደሚቻል ነው ባለሙያው የጠቆሙት።
በመጨረሻም፣ ከውጭ በርካሽ ዋጋ የሚመጡ ዕቃዎችን በውድ ለመሸጥ የሚደረገው ሩጫ ላይ ማንኛዉም አካል ክትትል ቢያደርግ የተሻለ ለውጥ እንደሚገኝ ነው ደምስ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ባሳለፍነው ነሐሴ 25/2013 ሕገ-ወጥ ተግባራትን መቆጣጠርን አስመልክቶ በነበረው የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ጉዳዩን ለመከታተል በተቋቋመ ግብረ ኃይል አማካይነት በመሠረታዊ አስቤዛዎች ላይ የሚስተዋለው ችግር እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።

በሕገ-ወጥ መንገድ የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ አካላትን የመቆጣጠር ተግባራችን ይቀጥላል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፣ ማኅበረሰቡም የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ሲመለከት በነጻ የስልክ መስመር 9977 እየደወለ በመጠቆም ችግሩን በጋራ እንድንቀርፍ ሊያግዘን ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በምግብ ፍጆታና በመሠረታዊ አስቤዛዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን በንግድ ፍቃድ አዋጅ 980/2008 መሠረት ዕርምጃ የሚወስድ መሆኑንም የጠቆሙ ሲሆን፣ ድርጊቱ ሲፈጽም የሚያይ ማንኛዉም አካል በ0111115581 በመደወል ትብብር ማድረግ እንዳለበት ነው የገለጹት።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com