የእለት ዜና

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በመተከል

ኢትዮጵያ እጅግም ባልተለመደ ኹኔታ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለበርካታ ዜጎች የሥቃይ ምድር ከሆነች ዋል አደር ብላለች። ሥደት እርዛቱ፣ መጠማት መራቡና ጉስቁልናው እንዳለ ሆኖ፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ዜጎች በየቦታው ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ይገደላሉ። ልጅ እናቱ ፊት ይገደላል፤ እናትም ልጇ ፊት ትገደላለች። እርጉዝ፣ አራስ፣ ደካማ፣ ሕፃን፣ ሽማግሌ ሳይባል ማንም በተገኘበት ይገደላል። በክብር መሞትና መቀበር እሰኪናፈቅ ድረስ ክፍለ ዘመኑን በማይመጥን ኹኔታ በርካታ ሰዎች ያልቃሉ።

ከሞት ያመለጡት ደግሞ ወልደው የሳሙበትን፣ አሳድገው የዳሩበትን፣ የእትብታቸውን መገኛና ለዘመናት የኖሩበትን ቀየ ጥለው ይሰደዳሉ። ሥደት ሲባል ማንም ቁጭ ብሎ አንደሚሰማውና በቴሌቪዥን እንደሚያየው ቀላል አይደለም። መውለጃ ቀኗ እምብዛም ያልራቀ ሴት ዳገት ቁልቁለት እየወጣችና እየወረደች ትሠደዳለች። መንገድ ላይ ምጥ ልትያዝ መቻሏ እንዳለ ሆኖ፣ ምንም በሌለበት ምድረ በዳ መውለዷ ሥደቷን እጅግ የከፋ ያደርገዋል። ወዲህ ደግሞ ልጆቿን ሰብሥባ የምትሠደድ እናትም አለች። ምሳ ተበልቶ እራት ጭንቅ በሚሆንበት፣ ልጅ በልቶ እናት ጦሟን በምታድርበት፣ መተኛ፣ አልጋና የሚለበስ ብርድ ልብስ ብርቅ በሆነበት ዳስ ውስጥ ለወራት ብሎም ለዓመታት መኖር አገሪቱ ለዜጎቿ እንደምን ያለች ብትሆን ነው ያስብላል።
በአገሩ እየኖረ የማይሠጋ፣ የማይፈራና የማይጨነቅ ሰው ጥቂት አይደለም። የሚሞተው፣ ቤት ንብረቱን ትቶ የሚፈናቀለው እና የሚያነባው ሕዝብ እልፍ ነው።

ኹሌም ድረሱልን ባይ፣ ኹሌም ከሞት ለመዳን የሰው ያለህ ባይ ጯሒ በየቦታው አለ። ኹሌም ደግሞ የሚታደግ ፈጥኖ ደራሽ ጠፍቶ ወይም ዘግይቶ ሟች የገዳይን አስፈሪ ገጀራ አይቶ ተሰቃይቶ ይሞታል፤ አልያም እግሬ አውጭኝ ይፈረጥጣል። ይህ የተለመደ የየቀን ስንክሳር ሆኗል።

የተባለው ኹሉ ሰቆቃ በአራቱም የኢትዮጰያ አቅጣጫ መልህቁን የጣለ ነው። በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ መተከል ዞን ደግሞ ሥቃዩ ከመበርታቱ በላይ ጊዜው መርዘሙ ከሁሉም ለየት ያደርገዋል። ለረዥም ጊዜ ያውም መቼ እንደሚያበቃ ሳይታወቅ እጅግ ብርቱ ስቃይና ግፍ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ይገኛል። በክልሉ ከሚገኙት ሦስቱ ዞኖች ውስጥ አንጻራዊ ሰላም ያለው በአሶሳ ብቻ ነው። በካማሺ እና በመተከል ዞኖች ከዓመት በላይ ያስቆጠረው የጸጥታ ችግር እንደቀጠለ ነው።
በመተከል ያለው የሠላም ዕጦት መፍትሔ ባለማገኘቱ ዞኑ በኮማንድ ፖስት አንዲመራ ተደረጎም ነበር። ነገር ግን፣ ይህ ተደርጎም እልባት ባለመገኘቱ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራ አዲስ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ዞኑን በመረከብ ወደ ሥራ መግባቱም የሚታወስ ነው።

የጸጥታ ችግር ባለባቸው የክልሉ አካባቢዎች ሠላም ያመጣል ተበሎ የተሞከረው ኹሉን ዜጎች ከሞትና ከሥጋት ማዳን ስላልቻለ፣ በቅርቡ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ኃይሉን ወደ መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ማስገባቱ ተነግሯል። የኹለቱ ክልል መንግሥታት መሪዎች አሻድሊ ሐሰንና አገኘሁ ተሻገር ነሐሴ 22/ 2013 በባህር ዳር ከተማ ታሪካዊ ያሉትን የጋራ የልማትና የሠላም የትብብር ሥምምነት ከተፈራረሙ ከቀናት በኋላ ነው የአማራ ከልል መንግሥት የጸጥታ ኃይሉን ወደ ቤኒሻንጉል ክልሉ ቡለን ወረዳ ያሠማራው።

በሥምምነቱ ወቅት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር 53 ሺሕ የሚጠጉ የአማራና የአገው ብሔር ተወላጆችን ወደ ቀያቸው በመለስንበት ማግስት የተፈራረምነው ይህ ሠነድ ታሪካዊ ነው ያሉ ሲሆን፣ ሥምምነቱ አደረጃጀት ያለውና በተቋም የሚመራ ነው ብለውታል። ለዚህም የፌደራል መንግሥቱ እስካሁን ሲያግዛቸው እንደነበርና ወደፊትም እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።

ኹለቱ ክልሎች በጤናና በትምህርትም አብረው ለመሥራት የተዘጋጁ መሆናቸውን የገለጹት አገኘሁ ተሻገር፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚኖሩ ዜጎችን ደኅንነት ከመጠበቅም አልፎ እዚያ አካባቢ የምንገነባው የሕዳሴ ግድብ ዕንቅፋት እንዳያጋጥመው በአስቸኳይ የጋራ ግብረ ኃይል እናቋቁማለን ሲሉ ተደምጠዋል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሐሰን በበኩላችው፣ ሕዝቡ ለም መሬት እያለው ድኃ ነው፤ ማዕድናት እያለው ደኃ ነው፤ የተለያየ የተፈጥሮ ፀጋ እያለው ደኃ ነው። ይህን የፈጠረውን ሥርዓት ለመቅበር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መሆን ሲገባቸው የአሸባሪው ተላላኪ ሲሆኑ ያሳዝናል ብለዋል። እነዚህን የሽፍታ አማጽያን ቡድን ብለው የአሸባሪው ተልዕኮ አስፈፃሚ ተላላኪ ቡድኖች ናቸው ያሏቸውን ለማጥፋት ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር በጋራ እንደሚሠሩም በሥምምነት መድረኩ ላይ ጨምረው ተናግረዋል።

ይህ ከሆነ ከቀናት በኋላ እንደተባለውም የአማራ ክልል ልዩ ኃይል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ገባ። በዚህም ወረዳው በይፋዊ የማኅበራዊ የትስስር ገጹ ለዘላቂ ሠላም የሚንቀሳቀሰው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በቡለን ከተማ አቀባበል ተደርጎልታል በማለት ጽፏል። የከተማዋ ወጣቶችና ነዋሪዎች፣ እንዲሁም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞችና አመራሩ ከከተማዋ ወጣ ብሎ አቀባበል እንዳደረገለትም ወረዳው ማስታወቁ የሚታውስ ነው።

በወቅቱ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ወደ ቡለን ከተማ መግባቱ በወረዳው ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታትና ማኅበረሰቡ በሠላም ወጥቶ እንዲገባ ለማድረግ ያስችላል ተብሎ ቢነገርም፣ ይህ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳለችው ብዙዎች ይገልጻሉ። በፌደራል መንግሥቱም ሆነ በክልሉ መንግስት በየጊዜው መግለጫ ከማውጣትና የማያዳግም ዕርምጃ እንወስዳለን ከማለት ውጭ በክልሉ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም እንዳልተፈጠረ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ኖረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሠላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ የክልሉን ወቅታዊ ጉዳዮች በተመልከተ ነሐሴ 7/2013 ባወጣው መግለጫ፣ በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ የሆነ የሠላም ድርድር ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ቡድኑ ጥሪውን ወደ ጎን በመተው የጥፋት ሥራውን ስለቀጠለ የክልሉ ኹሉም የፀጥታ አካላት ልዩ ኃይል፣ ፖሊስ፣ ሚሊሻ፣ በግል የጦር መሣሪያ የታጠቁ በሙሉ ከነሐሴ 8/2013 ጀምሮ ከመከላከያ ሠራዊትና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን የማያደግም ዕርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል።

አሁን ደግሞ ከወትሮው በተለዬ መልኩ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ወደ ክልሉ እንዲገባ መደረጉ ችግሩን በዘላቂነት ላይፈታው ይችላል የሚሉ የመኖራቸውን ያህል፣ ቀድሞ ከነበረው የተሻለ ዕልባት ይገኝ ይሆናል ብለው የሚያስቡም አሉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ በባህር ዳር ዩንቨርስቲ ሕግ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ደሳለኝ ጥጋቡ ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን እንዲህ ይገልፃሉ፤ “ፌደራል መንግሥቱ አሁን ላይ ካለበት ጫና የተነሳ እንደዚህ አይነቱን ግጭት የክልል መንግሥታት በመተባበር መፍታት ይችላሉ። በአገር አቅም ችግሩን ለመፍታት የፀጥታ ኃይሉን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወር ችግር የለውም።”

ደሳለኝ አክለውም፣ “አሁን ላይ የሌሎች ክልሎች የፀጥታ አካላትም ለሕልውና ዘመቻ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች መሰማራታችውን ጠቅሰው፣ በዚህ ሰዓት ከሕገ-መንግሥቱ አንፃር ይቻላል ወይ ብለን የምንጠይቅበት ጊዜ አይደለም” ብለዋል።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የሌሎች ክልሎች ኃይሎችም እንደሚሳትፉ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር መግለጻቸው ይታወሳል። በመሆኑም ክልሉ በራሱ የፀጥታ ኃይል ችግሩን መፍታት አቅቶት ነው ወይስ ምክንያቱ ሌላ ነው ለሚለው ጥይቄ መልስ መስጠት ያሰቸግራል። ይህ ቢሆንም ለዓመታት የክልሉን ሠላም ለማረጋገጥ ሲደክም ስለነበር ክልሉ የኃይል ማነስ እንዳለበት በግልጽ ማየት ይቻላል ብለዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በንጹኃን ላይ ጥቃት በመፈጸም ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ ከማድረስም በላይ በክልሉ ልማት እንዲጓተት አድርገዋል። ክልሉ ከሱዳን ጋር በስፋት ስለሚዋሰን ይህን እንደመልካም አጋጣሚ እንደሚጠቀሙበት ይገለፃል። ክልሎች በጋራ ተቀናጅተው በካማሺና በመተከል ዞኖች ያለውን ሠላም ማረጋገጥ ካልቻሉ ቀጣይስ ዘላቂ ሠላም ሊመጣ የሚችልው በምን መንግድ ነው ሲሉ ብዙዎች ስጋታቸውን ይገለጻሉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ማለዳ ከቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ተጨማሪ ማብራሪያ ፈልጋ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ሳይሳካላት ቀርቷል።

የአገርን ሰላም ለማምጣት ኹሉም አካል ባለድርሻ መሆኑንና ከጥላቻ ትርክት የፀዳ ሥርዓት መገንባት እንደሚያሰፈልግ ብዙዎች ይስማሙበታል። ኹሉም ዜጋ ለዚህ የበኩሉን አስተዋፆ ለማበርከት ቁርጠኛ ከሆነ ኢትዮጵያ ከዳር ዳር ሠላም የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 1

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

  1. በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው የተለየ ጥቅም ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ስላሉ እና መንግስትም ተሳዳጅ የሆነውን ማህበረሰብ እራሱን እንዲከላከል ፍላጎት አለመኖሩ ነው እንጂ የሚፈለገውን ሰላም ለማምጣት ከባድ ሆኖ አይደለም

This site is protected by wp-copyrightpro.com