የእለት ዜና

በሰሜኑ ጦርነት የተዘነጉ ችግሮች

ሦስት ዓመት ወደ ኋላ ተመልሰን መጋቢት 24/2010 ኢትዮጵያ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾሟን ተከትሎ በአገሪቱ ዘርፈ ብዙ ለውጦች መከሠታቸውን መንግሥት ይገልጻል። መንግሥት ባለፉት ሦስት ዓመታት ለውጥ አምጥቻለሁ ቢልም፣ በነዚያ ዓመታት ኢትዮጵያ በተለይ በፖለቲካው ዘርፍ በርካታ ችግሮችን አስተናግዳለች። ችግሮቹ ተባብሰው ወደ ጦርነት በማምራት የሰሜኑ የአገሪቱ ከፍልን ለከፋ ቀውስ ዳርገውታል።

በፌደራል መንግሥቱ እና ከለዉጡ ሐሳብ ጋር ቅራኔ ከነበራቸው አካላት ጋር በተለያየ ጊዜ ለማግባባት የተሞከረ ቢሆንም፣ በትግራይ ክልል የቀድሞ የህወሓት ባለሥልጣናት በኩል ያፈነገጠ ሐሳብ በመንጸባረቁ የጋራ መግባባት ሳይፈጠር ቆይቷል። የትግራይ ክልል የቀድሞ አስተዳደርም እራሱን በክልሉ ብቻ ወስኖ መቆየቱ የሚታወስ ነው። በቅርቡ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ከፌደራል መንግሥት ጋር የነበረው ግንኙነት በመቋረጡ እና ልዩነቱም እየሰፋ እና ሥር እየሰደደ በመሄዱ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል።

ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ካለመግባባቱም ባለፈ ተነጥሎ ምርጫ በማካሄዱ ያላበቃው የኹለቱ ኃይሎች ፍጥጫ እና እሰጥ አገባ እየተባባሰ በመምጣቱ ነገሩ ወደ ግጭት እና ጦርነት አምርቷል። ጥቅምት 24/2013 ይህ የኹለቱ ወገኖች አለመግባባት መባባሱን ተከትሎ በሰሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ጥቃት ተፈፀመ። በዚህም ምክንያት የፌደራል መንግሥቱ የሕግ ማስከበር ዘመቻ በማካሄድ ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለሕግ ለማቅረብ ቢሞክርም ግጭቱ እየተባባሰ መምጣቱ ግን ዕውን ሆነ።

ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እና እየተስፋፋ የመጣው ግጭት በሕግ ማስከበር ዘመቻ ብቻ ሊቆም ባለመቻሉ፣ ችግሩ የተወሰኑ አካሎች ጦርነት ብቻ ሳይሆን እየሰፋ መጥቶ “ሕዝባዊ ጦርነት” ወደ መሆን ከተሸጋገረ ሰነባብቷል። ከተጀመረ አስር ወር ያስቆጠረው ጦርነት አሸባሪ በተባለው ህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ ብቻ ተወስኖ የነበር ቢሆንም፣ አሁን ግን ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች እየተስፋፋ መጥቷል።

ጦርነቱ እየተስፋፋ መሄዱን ተከትሎ በአማራ እና አፋር ክልሎች በብዙ መንገድ በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት የተለያዩ ጥፋቶች ደርሰዋል። አሁንም በክልሎቹ በጦርነቱ ምክንያት የሟቾች እና የተፈናቃዮች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሆኑ ሌላዉ በአገሪቱ ላይ የተፈጠረ ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ሁኖ ቀጥሏል።

በትግራይ ክልል በተጀመረው እና አሁን “ሕዝባዊ” ተብሎ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ ኢትዮጵያ በየአቅጣጫው ብዙ ችግሮችን እያስተናገደች ትገኛለች። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት አብዛኛውን የጸጥታ ኃይል ትኩረት የሳበ በመሆኑ ነው። በዚህም የተነሳ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከዚህ በፊት ባሉት ጊዜያት የፀጥታ ችግር የሚስተዋልባቸው አንዳንድ አካባቢዎች መዘንጋታቸው ይነገራል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ አቅጣጫዎች ችግሮች እየገጠሟት እንደሆነ ይታወቃል። በተለይም በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና አማራ ክልል ድንበር እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች ጥቃቶችና እና መፈናቀሎች እየተባባሱ መምጣታቸው የማይካድ ሐቅ ስለመሆኑ አሁን ላይ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አካባቢዎች ያሉበትን ሁኔታ ማየቱ በቂ ማረጋገጫ ይሆናል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በየአቅጣጫው የሚነሱ ችግሮች እና የእርስበእርስ ግጭቶች አሁን አገሪቱ በገጠማት ጦርነት ምክንያት እየተባባሱ መቀጠላቸዉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ይመስላል። በዚህም አገሪቱ ወስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በየጊዜው ቅርፅና ይዘታቸውን እንዲሁም የትኩረት አቅጣጫቸውን የሚቀያይሩ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መምጣታቸውን በመጥቀስ ለወደፊት የኢትዮጵያ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል የተለያዩ ባለሙያዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ። መንግሥት በእነዚህ እና መሠል ጉዳይ ላይ ጠንካራ ዕርምጃ በመውሰድ የሕግ ማስከበር ሥራውን በኹሉም አቅጣጫ ሊከዉን እንደሚገባም ይጠቁማሉ።

በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የዓለም ዐቀፍ ጥናት መምህር ታደሰ አክሎግ(ፕ/ር) እንደሚሉት፣ ጦርነቱ በሰሜን ግንባር ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ እና በጦርነቱ ምክንያት በየአቅጣጫው የሚፈጠሩ ችግሮችን ከጦርነቱ ለይቶ ማየት ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ። ፀረ- ኢትዮጵያ ኃይሎች በትግራይ ክልል በተፈጠረው ጦርነት የመንግሥት ትኩረት ጦርነቱ ላይ ብቻ መሆኑን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ጥፋቶችን እያደረሱ ይገኛሉ ብለዋል።

ከዚህ ጋር አያይዘውም፣ ጦርነቱ አሁን ላይ በኹሉም አቅጣጫ ነው እየተካሄደ ያለው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ ቡድኖች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚደረግ ጥረት ስለሆነ ጦርነቱ ከትህነግ ጋር ብቻ የሚደረግ አለመሆኑን ይገልጻሉ። በዚህም ምክንያት በጦርነቱ ሽፋን ሌሎች አካባቢዎች ላይ ጥፋቶችን እያስተዋልን ነው በማለት መንግሥት ምናልባትም እነዚህ የተዘነጉ አካባቢዎች ላይ እየተደረገ ያለውን የሰው ሕይወት ማጥፋት እና ማፈናቀል በቸልተኝነት ሊያየው እንደማይገባ ያሳስባሉ።

“ጦርነቱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚፈልጉ እና ኢትዮጵያን ለማዳን በሚፈልጉ መካከል የሚካሄድ እንጂ በመንግሥት እና በህወሐት መካከል ብቻ የተወሰነ ባለመሆኑ ጦርነቱ በሁሉም አቅጣጫ ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር ታደሰ። ላለፉት በርካታ ዓመታት ህወሓት በሥልጣን በነበረበት ወቅት በሚያሰራጫቸው የሐሰት ትርክቶች የማኅበረሰብ አደረጃጀቶች፣ የኃይማኖት ተቋማት እና አባቶች ተዳክመዋል። ከዚያም ባለፈ የኢኮኖሚውን አቅጣጫ ወደ አንድ አካባቢ በማድረግ ብሎም ከአገር ውጭ ኢንቨስትመንት በማቋቋም ጭምር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሠራ ቆይቷል የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ ለጊዜው እየተፈጠሩ ያሉ ጦርነቶች እና ችግሮች ብዙ ዋጋ ሊያስከፍሉ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። መፍትሔው ፖለቲካዊ ድርድር ሳይሆን በወታደራዊ ዕርምጃ ህወሓትን እና ግብረ አበሮቹን ማጥፋት ነው በማለት ይጠቁማሉ።

የቦሮ ዲሞክራሲ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ዶክተር መብራቱ አለሙ ከላይ በተነሳው ሐሳብ ዙሪያ እና አሁን ያለውን ወቅታዊ ኹኔታ እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል። “አብዛኛው ትኩረት ማድረግ ያለበት መንግሥት ቢሆንም፣ እኛ እንደ ፓርቲ አሁንም ጦርነቱ በፈጠረው ችግር የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት እና በቀጥታ ጦርነቱ እየተካሄደ ካለባቸው አካባቢዎች ባልተናነሰ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠረ ያለው ሆኖም ግን በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ባለው ጦርነቱ ምክንያት የተዘነጉና ትኩረት የሚሹ አካባቢዎች ችግር ያሳስበናል” ሲሉ ነው የገለጹት።

ቢሮ ኃላፊው አክለውም፣ “መንግሥት ከዚህ በፊት ታጥቀው እና ሸፍተው የነበሩ ታጣቂ ቡድኖችን ወደ ድርድር ለማምጣት አቅጣጫ በማስቀመጡ ወደ ተሐድሶ እና ድርድር ደርሰው የነበሩ ኃይሎች ቢኖሩም፣ በመንግሥት እና በታጣቂ ኃይሎች መካከል የተፈጸመው ሥምምነት ግን ከተገቢው አካል ጋር ባለመሆኑ ብዙም ውጤታማ አልነበረም” ብለዋል። መንግሥት ታጥቀው እና ሸፍተው ንጹኃንን ሲገድሉ እና ሲያፈናቅሉ የነበሩትን ቡድኖች ሕጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ለሥልጠና እና ተሐድሶ ማቅረቡ፣ እነዚህ ሽብርተኛ ቡድኖች የልብ ልብ እንዲሰማቸው አድርጓል በማለት ልክ በትግራይ ክልል እያደረገ እንዳለው በተመሳሳይ በሌሎች አካባቢዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ ባሉ ታጣቂዎች ላይም የሕግ ማስከበር ተግባር ማካሄድ ነበረበት ይላሉ። ይህም ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ትኩረቱን ወደ አንድ አቅጣጫ በማድረጉ ሌሎች አካባቢዎች ጸትታን በማስፈን ረገድ ተረስተዋል ይላሉ።

ዶክተር መብራቱ አያይዘውም፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ትኩረት የተነፈጋቸው አካባቢዎች በተለይም እንደ መተከል እና ምስራቅ ወለጋ ያሉ የቤንሻንጉል እና የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ውስጥ በርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች መሰንዘራቸውን እና የመንግሥት የጸጥታ ኃላፊዎችም ምላሽ አለመስጠታቸውን ይናገራሉ።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ችግሮች መባባሳቸውን የጠቆሙት የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊው፣ በታጣቂ ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጠሩ ችግሮች ሕፃናት፣ ሴቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶች እና ሽማግሌዎች የጥቃቱ ሰለባዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ዓላማቸው ያልታወቀ እና በየጊዜው በንጹሐን ዜጎች ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን እያደረሱ ያሉት ታጣቂ ቡድኖች የእምነት ቤቶቸን፣ የትምህርት መሠረተ ልማቶችን እና ሌሎች ለማኅበረሰቡ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን እንዳወደሙ ይናገራሉ።

ባለፉት ኹለት እና ሦስት ሳምንታት ከ200 በላይ ንጹሐን ሞተዋል። ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ እና የኑሮ ውድነት አጋጥሟል። የሕብረተሰቡ ማኅበራዊ እሴቶች ተሸርሽረዋል። ከዚህም ባለፈ በቤንሻንጉል አካባቢ ቁጥራቸው በርካታ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ሞተዋል የሚሉት ኃላፊው፣ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ በርካታ አርሶ አደሮች በመፈናቀላቸው የተዘሩ ሰብሎች ሊሰበሰቡ አልቻሉም። ወደፊትም ቢሆን መንግሥት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ካልመለሳቸው እና በሠላም እንዲኖሩ ካላደረገ በአካባቢው አሳሳቢ የሆነ የምግብ ዕጥረት ሊከሠት እንደሚችል ገልጸዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ከ123 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ተመልሰዋል ያለው ከእውነት የራቀ ነው። ከካምፕ ወደ ካምፕ ነው የተቀያየሩት እንጂ ወደ ኑሯቸው አልተመለሱም፤ እርሻም አላረሱም፤ አምና የተዘራው ዘንድሮ አልተሰበሰበም በማለት መንግሥት ይህንን ጉዳይ በቸልተኝነት ሊያየው እንደማይገባ መብራቱ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል። በተጨማሪም ጉዳዩ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ እና መንግሥት ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ካልሠራ፣ እንዲሁም አሁን እየተከሰተ ላለው ችግር እልባት መስጠት ካልቻለ ጉዳዩ የከፋ ችግር ሊያደርስ እንደሚችል ጠቁመዋል። ይህን እና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ብሎም ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር እንድትወጣ ለማድረግ ከመንግሥት እና ከተለያዩ የዕርዳታ ሰጪ ተቋማት፣ እንዲሁም ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሠራን ነው በማለት፣ በተለይም ቀይ መስቀል ማኅበር በአሁኑ ወቅት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቶናል ሲሉ ሐሳባቸውን ይቋጫሉ።

ሌላው በዚህ ጉዳይ ላይ ለአዲስ ማለዳ ማብራሪያ የሰጡት የእናት ፓርቲ ጸኃፊ ጌትነት ወርቁ ናቸው። ጌትነት እንደሚሉት፣ አሁን አገራችን ላይ በተለይም በሰሜኑ አካባቢ የተከሰተው ጦርነት በፍጥነት እየተስፋፋ እና በብዙ ቦታዎች ላይ የከፋ ጉዳት እያደረሰ ነው። የጸጥታ ኃይሉን ሚዛን እና ትኩረት ወደ አንድ አቅጣጫ በማድረጉም በሌሎች አካባቢዎች ያለውን ችግር መንግሥት በአግባቡ እየተከታተለው እንዳልሆነ ይገልጻሉ።

በተለይም በሰሜን ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጥፋት በማንሳት፣ “የኹለት ዝሆኖች መራገጥ የሚጎዳው ሳሩን ነው” በማለት የመንግሥት ኃላፊነት ምን እንደሆነ እንኳን ማወቅ እንዳልቻሉ ነው የተናገሩት። ጦርነቱ በፈጠረው ችግር የጸጥታ ኃይሉ ትኩረት ወደ ሰሜን አቅጣጫ ብቻ በማመዘኑ ሌሎች ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ተዘንግተዋል። ይህም ጉዳት እና ጥፋቱን ከወትሮው በተለየ የጎላ ያደርገዋል ይላሉ። “በምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በኦሮሚያ ክልል መንግሥት እንዝላልነት እና ቸልተኝነት ምክንያት የተፈጠረው ችግር እና የጠፋው የሰው ሕይወት፣ እንዲሁም የተፈናቀሉ ንጹሃን ዜጎች ጉዳይ ጦርነቱ ከፈጠራቸው ተጓዳኝ ችግሮች መካከል ጎልተው የታዩ እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አመራሮችን ሚና ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገቡ ናቸው” ሲሉ ያብራራሉ።

የፌደራል መንግሥት ትኩረት ማነስ እና የጸጥታ ኃይሉን ለአንድ ጦርነት ብቻ ማዋል፣ እንዲሁም የዜጎችን ሠላምና ደህንነት የማስጠበቅ አቅሙ ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት ችግሩን እንዳባባሰው ጠቅሰዋል። በአጠቃላይ የፌደራል መንግሥት ሠላምን የማስፈን እና ጸጥታን የማስከበር ተልዕኮው አናሳ መሆን፣ እንዲሁም የክልል መንግሥታት አመራሮች ቸልተኝነት እና አቅመ ቢስነት ለሕገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኖች ምቾት የሚሰጣቸው በመሆኑ መንግሥት አሁን እያደረገ ካለው ጦርነት ጎን ለጎን እነዚህን አካባቢዎች በቅርብ ሊከታተላቸው እና የዜጎችን ሠላምና ደኅንነት ሊያረጋግጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።

“አሸባሪው ህወሓት በተለያየ የጦርነት ስትራቴጂ እየተጠቀመ ነው” የሚሉት የእናት ፓርቲ ጸኃፊው ጌትነት ወርቁ፣ ከጦርነቱ መከሰት ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ክልሎች የተከሰቱ ችግሮች ትኩረት ይሻሉ ብለዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በየጊዜው አሰለጠንኩ የሚላቸው የልዩ ኃይል አባላት ይሔ ሁሉ ችግር ሲፈጠር የት እንደሆኑ እና ሚናቸው ምን እንደሆነ መንግሥት ሊያጤነው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነም ይጠቅሳሉ።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በኹሉም አቅጣጫ ጦርነት ውስጥ መሆኗን በማንሳት ለገጠማት ችግር እንደመፍትሔ፣ “ይህንን ችግር የሚገነዘብ እና የመፍትሔ ሐሳብ የሚፈጥር አመራር ሊኖር ይገባል” በማለት፣ እንደ አገር ለመቀጠል ዋስትናችን ሊሆን የሚገባውም ግልጽ የሆነ የአሠራር ለውጥ ማምጣት፣ የአሥተዳደር መዋቅሮችን መፈተሸ እና መገምገም ነው ይላሉ። የመንግሥት እውነትን መሸሽ እና ችላ ማለት ዋጋ የሚያስከፍል ስለሆነ ሊቆም ይገባል የሚሉት ጌትነት፣ በአመራር እና አስተሳሰብ ደረጃ ብቁ ግለሰቦችን ወደ አሥተዳደራዊ መዋቅር ማምጣት ተገቢ መሆኑን ይጠቅሳሉ። አክለውም አገራቸውን መርዳት የሚፈልጉ እና አቅም ያላቸውን ግለሰቦች እና የፓርቲ አመራሮች በማስተባበር ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት መሠራት አለበት ይላሉ። ጦርነቱ የደበቃቸው እና መሞቱ እና መፈናቀሉ ያልቀረላቸው ወገኖች ግን ትኩረት ይሻሉ ሲሉ ሐሳባቸውን ያጠቃልላሉ።

አገር እንደዚህ አይነት ፈተና ሲገጥማት እና ችግሮች በየቦታው እየተባባሱ ሲመጡ ከሚያስከትሉት ጉዳቶች መካከል በሰው ሕይወት ላይ የሚደርሰው ጉዳት፣ የሥነ ልቡና ውጥረት፣ ሞት እና መፈናቀል በቅድሚያ ይጠቀሳሉ። መንግሥትም ሆነ ሌላው ለአገሬ እቆማለሁ የሚል እና በተለያየ የሙያ ዘርፍ የተሠማራ ሁሉ፣ እነዚህን እና መሰል ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ ለመቀነስ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባው የሚጠበቅ ነው።

አሁን ኢትዮጵያ ከገጠማት ጦርነት ጋር በተመሳሳይ የሚስተዋሉ ችግሮች ቀስበቀስ ሥራቸውን እየሰደዱ በመምጣታቸው ለመንግሥትም ሆነ ለሕዝብ የማይደፈኑ ቀዳዳዎች እንደሆኑ ይስተዋላል። በዚህም በርካታ ንጹኃን ለሞት እና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፤ ቤት ንብረታቸውን ጥለውም ብዙዎች ተሰደዋል። የመንግሥት ተግባርም ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ እንዳያስብል፣ በተረሱ እና ችላ በተባሉ አካባቢዎች ያሉ ችግሮች አሁንም ትኩረት ይሻሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com