የእለት ዜና

ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን የማበረታታት ውጥን

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ በእጅጉ አናሳ መሆኑ፣ ሴቶችን በፖለቲካው እንዳይሳተፉ እድል እንደመንፈግ እንደሚቆጠር ይነገራል። የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አናሳ መሆኑ ሴቶች ለፖለቲካ የተገቡ እስከማይመስል ድረስ በተለይ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል እምብዛም ሴቶችን ሲሳትፉ አይታይም።

ለሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ አናሳ መሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የሚታየው ሴቶችን ወደ መሪነት የማምጣት አመለካከት ችግር እና ሴቶችን ከአባልነት እስከ ፖለቲካ ፓርቲ መሪነት እንዲሳተፉ እድል የመስጠትና የማበረታታት ከፍተቶች በመኖራቸው መሆኑን በፖለቲካው ውስጥ የመሳተፍ እድል ያለገኙ ፖለቲከኞች ይናገራሉ። የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አናሳ ይሁን እንጅ አሁን አሁን ቀድሞ ከነበረው መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።

የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እየታዩበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሴቶችን ወደ ፖለቲካው እንዲገቡ የሚያበረታቱ እንቅስቃሴዎች በገዥው ፓርቲውም ይሁን በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ መሻሻሎች እየታዩ ነው።
ሴቶችን በፖለቲካው እንዲሳተፉ በር የሚከፍቱ መሻሻሎች እንዳሉ ሆኖ፣ ባሳለፍነው ነሃሴ መጨረሻ ሳምንት የሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የጋራ ምክር ቤት ተመስርቷል። የጋራ ምክር ቤቱ መመስረት በሚፈለገው ልክ መሻሻል ያላሳየውን የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲነቃቃ እና ሴቶች ወደ ፖለቲካውን እንዲገቡ በሚደረገው ጥረት አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል።

የጋራ ምክር ቤቱን ምስረታ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አባላት እና የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑ ሴቶች የተሣተፉበት መሆኑን ምርጫ ቦርድ መግለጹ የሚታወስ ነው። በጋራ ምክር ቤቱ ምስረታ ላይ የተገኙት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ፣ ሴቶች በፓለቲካ ያላቸው ተሣትፎ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ምርጫ ቦርዱም የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ መሻሻል እንዲያሳይ የተለያዩ ሥራዎችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለመሥራት ቢሞክርም ከሚፈለገው ለውጥ አንጻር ግን ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
የሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የጋራ ምክር ቤት ምሥረታ ጅማሮ ከኹለት ዓመት በፊት የተጀመረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ላይ የጋራ ምክር ቤቱ ምስረታ እውን መሆን ለሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተጠቁሟል።

የጋራ ምክር ቤቱ ምስረታ ወቅት የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢውን ንግግር ተከትሎ በቦርዱ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀውን የአሰራር ስርዓት ሰነድ ላይ ውይይት እንደተደረገ ከቦርዱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። የሴት ፓለቲካ ፓርቲ አባላት የጋራ ምክር ቤትም ሴት አባላት እንደ ፓለቲከኝነታቸው በጋራ ከሴቶች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ አገራዊ ጉዳዮቹን የሚያዩበት እንደሚሆን የተጠቆመ ሲሆን፣ የጋራ ምክር ቤቱ መመስረት ለጋራ የሴቶች የፓለቲካ ስራ መነሻ እንሚሆን ተገልጿል።

የጋራ ምክር ቤቱን የመመሥርቱ ጉዳይ የዘገየ እንደሆነ የጠቀሱት የቦርድ አመራር አባል ብዙወርቅ ከተተ፤ አገር ዐቀፍ ምርጫው ላይ ለሴት ዕጩዎች የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንደተሰጡና በሥልጠናውም ወቅት የተሰበሰቡትም አስተያየቶች የምክር ቤቱን መመሥረት አስፈላጊነት የሚጠይቁ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በገዥው ፓርቲም ይሁን በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የቀረቡ እጩ ተወዳዳሪዎች አብዛኛዎቹ ወንዶች ቢሆኑም፣ ሴቶችን ከዚህ ቀደሙ የተሻለ የተሳተፉበት ሲሆን፣ በተለይም በገዥው ብልጽግና ፓርቲ እና በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ሴቶችን በመጠኑም ቢሆን በእጩነት ቀርበው እንዲፎካከሩ እድል ከሰጡ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የጋራ ምክር ቤት የሥራ ግንኙነትና በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሠራር ሥርዓት የቃል ኪዳን ሠነድ ላይ የተጠቀሱት አስተያየቶች ተሻሽለው የጋራ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ሰነድ ጸድቋል። አዲሱ የሴቶች የጋራ ምክር ቤት በቦርዱ የፖለቲካ ሥራ ክፍል አስተባባሪነት የምክር ቤቱ ጊዜያዊ አመራሮች የተመረጡ ሲሆን፣ ነቢሃ መሃመድ ሊቀ-መንበር፣ ቆንጂት ብርሃኑ ምክትል ሊቀ-መንበር፣ እንዲሁም መሊሃ ጂሃድ ፀሃፊ ሆነው መመረጣቸውን ቦርዱ መግለጹ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ ተዋቅሮ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ዝግጅት ማድረግ መጀመሩን ተከትሎ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተመስርቶ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከምርጫ ቦርድ ጋር በጋራ በመሆን በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ችግር መፍትሔ ለማበጀት ጉልህ ሚና እንዳለው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ዝግጅት ላይ ታይቷል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዘጋጅነት፣ 107 የሚሆኑት ፖለቲካ ፓርቲዎች መክረው የቃል ኪዳን ሰነድ ከፈረሙ በኋላ የጋራ ምክር ቤቱ መመስረቱ የሚታወስ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በርስና በተናጠል የሚፈፅሙት ተግባርና ግንኙነት የሚመራበት የቃል ኪዳን ሰነድ መፈረማቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ድርጅታቸውን የወቅቱ ኢሕአዴግን የአሁኑ ብልጽግናን ወክለው፣ ከ106 የፓርቲ መሪዎች ጋር የፈረሙት የቃል ኪዳን ሰነድ ዋናኛ ዓላማ የፓርቲዎች ግንኙነት ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማጠናከር እና በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሔ ለመስጠት እንደሆነ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በተለይም ባሳለፍነው 2013 ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት በተጨማሪ በአገራዊ ጉዳዮች እና በፖለቲካው ጉዳዮች ላይ የጋራ ሀሳብ የሚንጸበረቅበት ምክር ቤት መሆኑ የሚታወስ ነው።

ይሁን እንጅ በምክር ቤቱ አባላት ማለትም በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ምክር ቤቱ የሚሰነዝራቸው ሀሳች እና አንዳንድ ጊዜ የሚያወጣቸው መግለጫዎች ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች የማይወክሉና ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ያልተደሰባቸው ናቸው በሚል ሲተች ነበር።
ምክር ቤቱ በተለይም በ2013 ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ግር በተያያዘ ሲስተናግዳቸው የነበሩ ቅሬታዎች፣ ሁሉም የምርክር ቤት አባላት ያልተስማሙበትና የልተሳተፉበት ነገር ላይ የጋራ መግልጫ መስጠትና በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ በሚጋጥሙ ችግሮች ለሁሉም እኩል አይሰራም የሚሉ ትችቶችን አስተናግዷል።

በሌላ በኩል ስድስተኛ አገራዊ ምርጫን በማሳለጥ ጉልህ ሚና እንዳለው የሚነሱ የጋራ ምክር ቤቱ አባል የሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሲኖሩ፣ ችግሮች ሲገጥሟቸው የጋራ መፍትሔ በማፈላለግ እና ለምርጫ ቦርድ ቸግሮችን በማሳወቅ በጋራ የሰራበትን ሁኔታ በአወንታዊ ጎን ያነሱታል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ የማስቻል ሥራዎች እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ነፃና ገለልተኛ ተቋም እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪ፣ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሂደት ላይ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር የምክር ቤቱ አባል የሚሆኑበትን ሁኔታ በማስቀረት ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ፓርቲዎች ብቻ አባል እንዲሆኑ ለማድረግ ማሰቡን መግለጹ የሚታወስ ነው።

ምክር ቤቱ ሲቋቋም አባል የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማሙበት የጋራ መግባቢያ የቃል ኪዳን ሰነድ የነበረው ሲሆን፣ የቃል ኪዳን ሰነዱ ማሻሻያው ተደርጎበት ምክር ቤቱ ነጻነቱን በጠበቀ መልኩ ሕጋዊ እውቅና እንዲኖረው ይሆናል መባሉ አይዘነጋም። ለዚህም ምክር ቤቱ እንደ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት እንዲመዘገብ፣ በሕገ መንግሥቱ መሰረት በአዋጅ ተቋቁሞ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ለምርጫ ቦርድ እንዲሆን ሀሳብ መቅረቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉንም ፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀፈ ሲሆን፣ በክልል ደረጃ የክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት በመመስረት በጋራ ጉዳዮች ላይ እየሰሩ ነው። በተለይ በስደስተኛው አገራዊ ምርጫ ዝግጅት እና የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሰኔ 14/2013 ከተካሄደ በኋላ በገጠሟቸው ችግሮች ላይ የጋራ መፍትሔ በመፈለግ እና ከዚህ ቀደም እንደነበረው ከመነቋቆር በተወሰነ ሁኔታ በትብብር የሰሩበት ሁኔታ እንደነበር መታዘብ ይቻላል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴቶች ተሳትፎ አናሳ የሆነበትን ችግር ያቃልላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የሴት ፖለቲካ ፓርቲ አባል የጋራ ምክር ቤት፣ ሴቶችን ወደ ፖለቲካው እንዲገቡና የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የራሱን ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com