የእለት ዜና

የሴቶች አመራር ሰጭነት እና የፖለቲካ ተሳትፎ

Action For Social Development And Environmental Protection Organization (ASDEPO) 2006 ዓ፣ም የተቋቋመ እና አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት ሲሆን የተለያዩ የልማት(development) እና የሰብዓዊ (humanitarian) ሥራዎችን በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋር፣
በቢኒሻንጉል፣ በጋምቤላ እና ትግራይ ክልሎች ውስጥ በእናቶች እና ሕፃናት ጤና፣ የምግብ ሥርዓት ማሻሻል፣ የሴቶችን እና ወጣቶች የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል፣ በሠላም እና ግጭት አፈታት እንዲሁም የሴቶችን ተሳትፎ ለማሻሻል እየሠራ ይገኛል፡፡

1.1.በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሴቶች ጉልህ የፖለቲካ እና የአመራር ተሳትፎ

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የወንድ የበላይነት የሕግና የባህል መሠረት ኑሮት ለዘመናት የነበረ ሲሆን፣ የሴቶች ተሳትፎ በሁሉም ዘርፍ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎት ኖሯል። በተለይ የፖለቲካ እና የአመራር ተሳትፎን ስንመለከት የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶች አኳያ ዝቅተኛ ነበር። በዚህ ጽሑፍ ለማሳየት የተፈለገው የሴቶችን ተሳትፎ እና ጉልህ ሚና ሲሆን፣ አርዓያ የሚሆኑ ሴቶችን እንደምሳሌ ለማሳየት ይሞክራል።

ወደ አስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን መለስ ብለን ለማየት ብንሞክር በአፄ ዘርዐያቆብ ዘመን የሴቶች በፖለቲካው የነበራችው ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር። ንጉሱ ዘጠኝ ሴቶችን በከፍተኛ የመንግሥታቸው አመራር ውስጥ ሾመው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። በአፄ ልብነድንግል የንግስና ዘመንም ንግስት እሌኒ የንጉሱ አማካሪ ነበረች። በዘመነ መሳፍንት ወቅትም ተሳትፏቸው የጎላ ሴቶች እንደነበሩ ታሪክ ያስረዳል።

በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ብዙዎች እንደሚስማሙት በእቴጌነት ዘመናቸው የነበራቸው የፖለቲካ እና የአመራር ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር። እቴጌ ጣይቱ የጦር መሪ፣ የጦርነት ዘዴ ቀያሽ፤ የአዲስ አበባ ከተማ እንድትመሰረት ሐሳብ አመንጭ፤ ብልህ እና ጥበበኛ ሴትም ነበሩ። የፖለቲካ ተሳትፏቸው እንደማሳያ ብንጠቅስ፣ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር በነበራት ግንኙነት የውጫሌ ውል ሊያስከትል የሚችለው አገራዊ ጉዳት በመረዳት ንጉሰ ነገስቱ አፄ ምኒልክ ውሉን ቀደው በጣልያን ላይ ጦርነት እንዲታወጅ ጠንካራ አቋም የወሰዱ ጠንካራ ሴት ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በአድዋ በተዋጊነትና በጦርነቱ የተጎዱትን ወታደሮች በማከም እንዲሳተፉ አድርገዋል።

የአባታቸውን ዘውድ ጭነው ንግሥተ-ነገሥታት ለመሆን የበቁት እቴጌ ዘውዲቱም ተጠቃሽ ንግሥት ናቸው። አፄ ምኒልክ የልጅ ልጃቸውን ልጅ እያሱን አልጋ ወራሻቸው ማድረጋቸው ለሴቶች በዘመኑ የነበረውን አስተሳሰብ ቢያሳይም፣ ከልጅ እያሱ ውድቀት በኋላ ዘውዲቱ እንድነግሱ በመኳንንቶች ይሁንታ መገኘቱ አስገራሚ ነው።

በኢጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት ማለትም ከ1928 – 1933 ዓ.ም. የኢትዮጵያውያን የአርበኝነት ታሪክ ውስጥ የሴች ተሳትፎ ክፍተኛ ነበር። ከበደች ስዩም፣ ሸዋረገድ ገድሌ፣ ቢተውሽ በላይ፣ እንዲሁም ንግስት ሮማን ወርቅ ኃ/ሥላሴ የፖለቲካ እና አርበኝነት ሥራ በመሥራት ተጠቃሽ ሴቶች ናቸው።

በንጉሠ ነገሥት ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ስንዱ ገብሩ የፓርላማ አባል እና ምክትል ሰብሣቢ፣ እንዲሁም የማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊም ሆነው አገልግለዋል። የጣሊያን ወረራ በመቃወምና በመታገልም ቀዳሚዋ ሴት ነበሩ።
የመንግሥት ሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ አና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን በተደረጉ እንቀስቃሴዎች ለምሳሌ፣ የአፄ ኃይለሥላሴን ዘውዳዊ ሥርዓት እና የደርግን ሥርዓት ለመጣል በተደረጉት ትግሎች ውስጥ በርካታ ሴቶች ተሳትፈዋል። ለምሳሌ ማርታ መብራህቱ ዘውዳዊ ሥርዓቱን በመቃወም አይሮፕላን እስከመጥለፍ ከደረሱት ሴቶች አንዷ ነበረች። በወቅቱ በነበሩት ፓርቲዎችም ከተራ አባልነት እስከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነትም የደረሱ ሴቶች ነበሩ።

በደርግ ዘመነ መንግሥት እና እስካሁን ባለው ጊዜ የሴቶች ተሳትፎ ከበፊቱ የተሻለ ቢሆንም አሁንም ክፍተቱ የጎላ ነው። ምንም እንኳ በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አንጸባራቂ ሴቶች ቢታዩም፣ በቁጥር በጣም ውስን በመሆናቸውና መዋቅራዊ ድጋፍ ባለማግኘታቸው፣ እንዲሁም በነበረው ማኅበራዊ እና ኢኪኖሚያዊው ተጽዕኖ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የተወሰነበት፣ እንዲሁም ሴቶች በአገራቸው ፖሊሲ ፣ ስትራቴጅ፣ አፈጻጸም ላይ እኩል መወሰን ባለመቻላቸው የሴቶችን ችሎታ ካለመጠቀም ባለፈ እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እና ፍትሐዊነት እንዳይሰፍን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲስተዋሉ ምክንያት የሆነ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶች የሚበረታቱ እና ተስፋ የሚሰጡ ሁነዋል።

1.2.ስድስተኛው የምርጫ እና የሴቶች ተሳትፎ
በስድስተኛው የምርጫ ሒደት ውስጥ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። ከነዚህም ውስጥ፡-
የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የፓለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች የተለያዩ የውይይት መድረኮች በመዘጋጀታቸው እና የግንዛቤ ሥራ በመሥራታቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ሴቶችን ወደአመራር እና ወደፖለቲካ ተሳታፊነት ያመጡበት ሁኔታ መኖሩ፣ እንዲሁም በተለያዩ የውይይት መድረኮች የሴቶች በውሳኔ ሰጭነትና ፓለቲካ ተሳትፎ ዙሪያ ያለው አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታን አስመልክቶ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ውይይት መረደጉ ማኅበረሰብ ጋር የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር አድርጓል።
በተለያዩ ሚዲያዎች የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎና ውክልና ማሳደግ እጅግ ወሳኝ መሆኑን በውይይት፣ በጥናታዊ ጹሑፎች በማቅረባቸው እና የሚዲያ ትኩረት በማግኘቱ ማኅበረሰቡ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ጥቅም መረዳት ችሎአል።

በአሁኑ ጊዜ መንግሥታዊ ያልሆኑ እና የሲቪክ ማኅበራት ድርሻ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ እና የአመራር ሰጨነት ሚና ለማሳደግ ከፍ እያለ መምጣቱ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ከመሳደግ አንጻር ፣ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ፍላጎትን ከመቀስቀስ እና አቅም ከማጎልበት አንጻር እንዲሁም የሴቶች ተሳትፎ በፖለቲካው እና በአመራር ሰጭነት እንዲጨምር ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አንጻር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

በተለያዩ ሙያ እና የሥራ ዘርፍ( ከዩንቨርስቲዎች ፣ ከምርምር ተቋማት እና ከተለያዩ ድርጅቶች) ላይ ያሉ እና ከዚህ በፊት የፖለቲካ ተሳትፎ ያልነበራቸው ሴቶች የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መሳተፍ ችለዋል። በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ያቀረቡአቸው ዕጩ ሴት ተመራጮችን ቁጥር መጨመር ተችሏል።

በገዥው ፓርቲ በኩል የሴቶችን ተሳትፎን ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎች የሚያበረታታ በመሆኑ፣ ይህንንም ተከትሎ በርከት ያሉ ቁጥር ያላቸው የብልጽግና ፓርቲ ተወካዮች መመረጣቸው እና ወደ አመራር መምጣታቸው አንደትልቅ ውጤት የሚቆጠር ነው።
በስድስተኛው የምርጫ ሒደት ውስጥ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩ ጥረቶች ቢደረጉም፣ ሴቶች በተሻለ መልኩ ወደ አመራርነት እንዲመጡ እና ውሳኔ ሰጭ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጭነት እንዳይመጡ ያደረጓቸው መዋቅራዊ፣ ፓለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኪኖሚያዊ ችግሮች በደንብ መፈተሸ እና ችግሮችን ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት መደረግ ይኖርበታል::

1.3. የሴቶች አመራር ሰጭነት እና የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች

በፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶች በአባልነትና በመሪነት እንዲሳተፉ የፖለቲካውን ምህዳር ማስፋት፣ እንዲሁም የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲሻሻል ዘላቂ የሆኑ ተቋማዊ ለውጦችን ማድረግ
ሴቶች በፖለቲካ መድረኮች እንዲሳታፉ ማመቻቸት፣ የስርዓተ-ፆታ መዋቅሮችንና አጀንዳዎችን ማውጣትና በትክክል መተግበር፣
በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያለውን የተሳሳተ አመለካት ማስተካከል፣ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎች በተለይም የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር ዐዋጅ ተግባራዊ በማድረግ ሴቶችን በፖለቲካ ውስጥ እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታን መፍጠር
የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት እና አመራርነት ሚና ማሳደግ የሁሉም ድርሻ በመሆኑ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይ ወንዶች ፣ ባሎች ፣ ወንድሞች የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እንደ አገር፣ እንደ ማኅበረሰብ እና ለሴቶች እኩልነት ለማረጋገጥ ያለውን ጉልህ ሚና ተገንዝበው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ዋና ተዋናኝ መሆን ይኖርባቸዋል፤

የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት እና አመራርነት ተሳትፎ በሚጠበቀው ልክ ለማሳደግ ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ የሚደርስን ተጽዕኖ በማስቀረት በኩል የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። በዚህም ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማኅበረሰብ ደረጃ ፣ በኃይማኖት ተቋማት ደረጃ፣ በመንግሥት ተቋማት ደረጃ፣ እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራት በኩል የተጠና ቅንጅታዊ ሥራ ሊሠራ ይገባዋል።

ምንም እንኳን በምክር ቤቶች ያለው የሴቶች ውክልና ቁጥር መሻሻል ቢያሳይም፣ ሴቶች በወሳኝ ቦታዎች ማስቀመጥ ከቁጥር ማሟያ ባለፈ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና በአገራቸው ኹለንተናዊ ዕድገት ላይ እኩል ወሳኝ እንዲሆኑ የተለያዩ ሥልጠናዎች በመስጠት እና የተለያዩ አገራትን ተሞክሮ በመዳሰስ የሴቶችን አቅም ማጎልበት ያስፈልጋል።

ASDEPO ከ ዓለም ዐቀፍ የሪፐብሊካን ተቋም( international republican Institute(IRI)) ጋር በመተባበር በአገራችን ላይ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለመጨመር የሚስተዋሉ ምቹ ሁኔታዎች በማጠናከር እና በመደገፍ ሴቶች ከከፍተኛ የሥልጣን እርከን እንዲደርሱና ውሳኔ መስጠት ላይ እንዲሳተፉና፣ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርቧል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com