የእለት ዜና

ፕሮጀክቶችን በዘመናዊ መልኩ ማስተዳደር የሚያስችል መተግበሪያ ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ

የፕሮጀክቶችን አሠራር በዘመናዊ መልኩ ማሥተዳደር የሚያስችል መተግበሪያ 83 በሚሆኑ የአገሪቱ ከተሞች በበጀት ዓመቱ ሥራ እንደሚጀመር ተገለጸ።
መተግበሪያው በ83 ከተሞች በመሰራጨት የፌደራል የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና የወጣቶች ሥራ ፈጠራ ፕሮጀክቶች ሥራዎችን ሪፖርት በዘመናዊ መልኩ ለማቅረብ የሚያስችል ሲሆን፣ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር የፌደራል ሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የአይሲቲ ቡድን መሪ ጥላሁን ከበደ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ጥላሁን እንደተናገሩት ከሆነ፣ እስካሁን በዘመናዊ ትግበራ ትስስሩ ያልተቀላቀሉ 72 ከተሞችን ወደ ሥራው ለማስገባት ባለሙያዎችን እያሰለጠኑ እንደሆነና ያልተጠናቀቁት የቴክኒክ አሠራሮች ሙሉ ለሙሉ ሲስተካከሉ management information system (MIS) የተባለው ዘመናዊ የፕሮጀክቶች ሥራ ማስፈጸሚያው በተግባር ላይ እንደሚውል ጠቁመዋል።

አክለውም፣ ከነበሩት 11 ከተሞች ላይ ተጨማሪ 72 ከተሞችን በሲስተሙ በማስገባት በአጠቃላይ 83 የአገሪቱ ከተሞችን በዘመናዊ አሠራሩ ለማሳተፍ ብዙ ሥራ ማቃለላቸውን አብራርተዋል።
በከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ወርሃዊ ሪፖርት አቀራረብ እስካሁን የፍጥነት ችግር ይገጥማቸው እንደነበር የገለጹት ጥላሁን፣ ዘመናዊ የፕሮጀክቶች ሥራ ማስፈጸሚያው ወደ ተግባር ሲገባ በየወሩ ከፕሮጀክት ወደ ክልልና ወደ ዓለም ዐቀፍ ባንክ የሚቀርበውን ሪፖርት በቀላል መንገድ ለማስተላለፍ ለፍጥነት ችግራቸው መፍትሔ እንደሚሆናቸው አብራርተዋል።

አያይዘውም ከበላይ አካላት በፕሮጀክቶች የተከናወነውን ሥራ “በየወሩ አምጡ አታምጡ’’ በማለት ሲያማርር የነበረውን ችግር በማስወገድ፣ የተሠሩትን ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በመመዝገብ ከክልል ወደ ፌደራል፣ ከፌደራል ወደ ዓለም ባንክ ማስተላለፍ የሚያስችል ዘመናዊ የሥራ መተግበሪያ ነው ሲሉ ነው የገለጹት።

የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ሥራዎችን በተመለከተም፣ የሴፍቲኔት ሥራን ለመሥራት በየክልሉ የሚበተኑ እንደ ዶማና መሰል መሳሪያዎችን ብዛት የግዥ ዋጋ፣ በልማት ሥራ ለሚሳተፉት ሰዎች ምን ያክል እንደተከፈለ በመመዝገብ ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ላሉ አካላት መረጃን በማዳረስ የሙስና አሠራሮችን እንደሚያስወግድ ነው የተናገሩት።

የአይ ሲ ቲ ቡድን መሪው እስካሁን የተለያዩ ሪፖርቶችን በአካል ሲያስተላልፉ እንደነበር የገለጹ ሲሆን፣ ዘመናዊ መተግበሪያው ከፍጥነት በተጨማሪ ሪፖርቶችን በቁጥር፣ በምስልና በጽሑፍ መልኩ ለማስተላለፍ እንደሚያስችል አመላክተዋል።
ዘመናዊ የፕሮጀክት ሥራ ማስፈጸሚያው የወጣቶች ሥራ ፈጠራ ፕሮጀክትን እንደሚያግዝም የተገለጸ ሲሆን፣ ወጣቶቹ ከትምህርት ተቋም ተመርቀው ሲወጡ ምንያክል ውጤት አንዳላቸው፣ በምን እንደተመረቁና መቼ እንደተመረቁ መረጃቸውን በቀጥታ ወደ ድርጅቶች በማስተሳሰር ሥራ የሚቀጠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስችላል ብለዋል።

ጥላሁን እንደገለጹት ከሆነ፣ በቴክኖሎጅው የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራው በኹለት አይነት መንገድ ማለትም አንደኛ ራሳቸውን ቀጣሪ አድርገው የሚሠሩ ሲሆን፣ በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ በውጭም በአገር ውስጥም አሠሪዎችን በማገናኘት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ይረዳል ብለዋል።

መንግሥትም ሥርዓቱን በመጠቀም ሠሪና አሠሪዎችን የማገናኘት ተግባሩን እንደሚያከናውን፣ በዚህ ሥራ የሚሳተፉ ወጣቶችን ለተከታታይ ኹለት ሳምንት በማሰልጠን ወደ ሥራው እንደሚያስገባቸው አመላክተዋል።
እስካሁን በአገሪቱ ያሉ ኤጀንሲዎች ተመርቀው ሥራ ያጡትን ብቻ ከሥራ ፈላጊዎች ጋር በማገናኘት ከሚተገብሩት አሠራር በተለየ መልኩ፣ መንግሥት በሥራ የተሠማሩ የተለያዩ ባለሙያዎችን ከውጭ አገራት ጋር በዘመናዊ መተግበሪያው በማገናኘት እንደሚሠራም ነው ጥላሁን የገለጹት።

አክለውም ሥርዓቱ እየተሰራ ያለው በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ‹አፍሪ ኮም› በተባለው ድርጀት ሲሆን፣ የሚያሠራውም ዓለም ባንክ መሆኑን ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!