የእለት ዜና

እየጨመረ የመጣው የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ ወላጆችን አስመርሯል

ደምሴ አብዲሳ (ስማቸው የተቀየረ) በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው። ደምሴ የኹለት ልጆች አባት ናቸው። ባለቤታቸውን በሞት ከተነጠቁ በኋላ ልጆቻቸውን የማሳደግ ኃላፊነት የእርሳቸው ሆኗል። ልጆቹ በሥነ-ምግባር እና በዕውቀት ልቀው እንዲገኙ የሚፈልጉት ደምሴ፣ ከፍተኛ የትምህርት ክፍያ በመክፈል ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት እያስተማሯቸው ይገኛሉ።

ደምሴ የግል የዐይን ሕክምና ክሊኒክ ያላቸው ሲሆን፣ የሚያገኙትን ገቢ ቤተሰብ ያስተዳድሩበታል። ደምሴ የመጀመሪያ ልጃቸው የ 8ተኛ ፣ኹለተኛው የ7ተኛ ክፍል ተማሪ ነው። የደምሴ ልጆች ቅዱስ ዮሴፍ (ሴንት ጆሴፍ) ትምህርት ቤት ለኹለት ዓመት የተማሩ ሲሆን፣ በሚመጣው ዓመት ትምህርታቸውን ለመቀጠል ቀድሞ ለትምህርት ይከፍሉት ከነበረው ክፍያ ዕጥፍ ጨምሮባቸዋል።

‹‹ልጆቼ በሥነ-ምግባር እና በተሟላ ዕውቀት እንዲዳብሩ እፈልጋለሁ። ስለዚህ ትምህርት ቤቱ ጭማሪ ቢያደርግም ልጆቼን አስተምራለሁ›› ብለዋል። እንደ ደምሴ ገለጻ ከሆነ፣ በፊት ይከፍሉት የነበረው ሦስት ሺሕ ብር በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ጭማሪ ተደርጎበት 6ሺሕ200 ደርሷል። ይህ ክፍያ በተርም ማለትም በሦስት ወር የሚከፈል ሲሆን፣ በዓመት ሦስት ጊዜ ይከፍላሉ። ለኹለቱም ልጆቻቸው ተመሳሳይ ክፍያ የሚከፍሉ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለኹለቱ ልጆቻቸው በዓመት የሚያወጡት የትምህርት ቤት ክፍያ ብቻ 37ሺሕ 200 ብር ይደርሳል።
ከትምህርት ቤት ክፍያ ውጭ የዩኒፎርም፣ የሚጠቀሙበት መጻሕፍት እና የተለያዩ መዋጮዎች እንደሚከፍሉ ደምሴ ይገልጻሉ።

የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ ወላጆችን ማስመረር ከጀመረ ረጅም ዓመታት ተቆጥረዋል። ትምህርት ቤቶች አንዱ ከሌላው ለየት ያለ ነገር ይዞ በመምጣት እና የተማሪዎችን የዕውቀት ደረጃ በማሳደግ ውድድር ውስጥ ናቸው። የተማሪዎቹ የዕውቀት ደረጃ አድጓል ወይስ አላደገም የሚለውን ልጆቹን ወደትምህርት ቤቶቹ የላከ ወላጅ ብቻ ነው ምስክር መሆን የሚችለው። ነገር ግን፣ በኢትዮጵያ እንዲሰጥ በሚፈለገው የትምህርት ጥራት ደረጃ እየሰጡ የሚገኙት ከ50ሺሕ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንድ ሺሕ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የሚሠሩ እና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ተናጋረዋል።

እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገለጻ ከሆነ አንድ የግል ትምህርት ቤት ለመክፈት ማሟላት የሚገባቸው በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተቀመጡ መስፈርቶች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟሉት ጥቂቶች መሆናቸውን ነው። ለዚህም ከፍተኛ ቁጥጥር መደረግ እንደሚገባው ነው የተገለጸው።

ትምህርት ቤቶች የሚያስከፍሉት ክፍያ ለተማሪዎቹ ለሚሰጡት አገልግሎት መሆኑ ይታወቃል የሚሉትም ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወጣቶች ሥነልቦና አማካሪና ኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው።
እንደ ባለሙያው ገለጻ ከሆነ ወላጆች ልጆቻቸውን የግል ትምህርት ቤት እየከፈሉ የሚያስተምሩት ጥራት ያለው ትምህርት ለማግኘት ቢሆንም፣ ምን ያህሎቹ በጥራት ያስተምራሉ የሚለው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው ብለዋል።

የመንግሥት ትምህርት ቤት የሚማሩ ጎበዝ እና ዓላማ ያላቸው በርካቶች መሆናቸውንም መገንዘብ ያስፈልጋል። በርግጥ ተማሪዎች ክፍል ውስጥ ከሚሰጣቸው ትምህርት በተጨማሪ በግል የሚደረግላቸው የመምህራን ዕገዛ እውቀታቸውን እንዲያዳብሩ የሚያግዛቸው መሆኑን ሊታወቅ ይገባል ብለዋል ባለሙያው። በተለይ ዓለም ዐቀፍ ካሪኩለም የሚከተሉ ትምህርት ቤቶች ከቃል ትምህርት ባለፈ ልምምድ የሚያደርጉበት አቅርቦት መኖር ተማሪዎችን በማነቃቃት የትምህርት አቀባበላቸውን እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል።

ትምህርት ቤቶች ላይ የሚደረገው ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ወላጆችን የሚያስመርረው ካለው የኢኮኖሚ ጫና አንጻር ነው ያሉ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ የተፈጠረው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ወላጆች ገቢያቸው ሳያድግ ወጪያቸውን የሚጨመር በመሆኑ ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ጫና ይፈጥርባቸዋል ብለዋል።

መታሰቢያ ደሳለኝ ልጇን በዲቦራ ትምህርት ቤት የምታስተምር ሲሆን፣ ለቀጣይ ዓመት 35 በመቶ ጭማሪ በማድረግ እንዳስከፈሏት ትናገራለች።
ምንም እንኳን በግል ሥራ የምትተዳደር ብትሆንም፣ የትምህርት ቤቱ አግባብ የሌለው ጭማሪ ከኑሮ ውድነቱ ጋር እጅግ እያስመረራት እንደሆነ ገልጻለች።
የመዋዕለ ሕፃናት (ኬጂ) ተማሪ ልጅ ያላት መታሰቢያ፣ በፊት በሴሚስተር ትከፍለው ከነበረው 4ሺሕ 937 ብር አሁን ወደ 6ሺሕ 665 ብር መጨመሩን ነግራናለች።

ትምህርት ቤቱ የዋጋ ጭማሪ ከማድረጉ በፊት ወላጆችን ያወያየ ቢሆንም፣ በውይይቱ ላይ መሳተፍ ያልቻለችው መታሰቢያ በተጨመረው ክፍያ መጠን ተስማምታ መቀጠሏን ለአዲስ ማለዳ ተናግራለች።
የኢትዮጵያ ትምህርት ዘርፍ ማሻሻያ መሠረት የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1994 የጸደቀ ሲሆን፣ ይህም በትምህርት ዘርፍ ልማት ፕሮግራሞች ውስጥ የተካተተ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም የትምህርት ፖሊሲ ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት ትምህርት ሥርዓቱን ያሻሽላል ተብሎለት ነበር።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት 640ሺሕ ተማሪዎች ግማሾቹ ማለትም 320ሺሕዎቹ በግል ትምህርት ቤት እንደሚማሩ (Education statistic Annual Abstract 2007) መረጃ ያሳያል።
መንግሥት በኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት የትምህርት ደረጃዎችን ለማስፋፋት በማሰብ በርካታ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ዕድል እየሰጠ ነው።

ትምህርት ቤቶች የቀጣይ ዓመትን የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ለመጨመር ወላጆች እና የሚመለከታቸውን አካላት በማወያየት መሆን እንደሚገባው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ያስቀመጠው መስፈርት ይጠቅሳል። ይህንንም መሠረት በማድረግ ቢሮው የ2014 የትምህርት አገልግሎት ክፍያ በተመለከተ መረጃዎችን አሰራጭቷል። በዚህ መረጃውም ላይ በዘፈቀደ ትምህርት ቤቶች ይሠሩበት የነበረውን የመመዝገቢያ ክፍያ በተመለከተ ማንኛውም ትምህርት ቤት የመመዝገቢያ ክፍያ ሲያስከፍል፣ ከሚከፈለው ወርሐዊ የአገልግሎት ክፍያ 25 በመቶ ብቻ እንዲሆን ተደርጓል።

ይህንን መሠረት በማድረግ ለ2014 የትምህርት ዘመን ክፍያ ለመጨመር ካስገቡት አንድ ሺሕ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 162ቱ የመመዝገቢያ ክፍያ ከ25 በመቶ መብለጥ የለበትም የተባለውን ባለማሟላታቸው ድጋሚ እንዲያስተካክሉ መደረጉን ቢሮው ማስታወቁ ይታወሳል። ይህንን የማይተገብሩ ካሉ ከባድ የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጣቸው እና ፍቃዳቸው ሊሠረዝ እንደሚችልም ተገልጾ ነበር።

ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ክፍያ የሚጨምሩት ካለባቸው የቤት ኪራይ ክፍያ፣ የመምህራን ደሞዝ እና ሎሎች ኢኮኖሚያዊ ወጪዎች በመነሳት መሆኑን ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ በአገራችን የሚገኙ ዓለም ዐቀፍ ትምህርት ቤቶች የሚመሠረቱበት መሥፈርት ከፍተኛ ወጪ ስለሚያስወጣ ክፍያቸውም ከፍተኛ እንደሚሆን አዲስ ማለዳ ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘችው መረጃ ያሳያል። በሚመሠረቱበት አደረጃጀትም የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት፣ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት እና የአገር ውስጥ ካሪኩለም የሚመሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው ታውቋል።

የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚያስከፍሉት ክፍያ በተመለከተ አዲስ ማለዳ ምርመራ ያደረገችባቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ውድ የተባለ ክፍያ የሚያስከፍለው ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ስኩል (ICS) ሲሆን፣ አመታዊ ክፍያው ከ334 ሺሕ እስከ 1.1ሚሊዮን ብር ነው።

ቀጥሎም ሳንፎርድ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ሲሆን በድረ-ገጹ ላይ ባገኘነው መረጃ ዓመታዊ ክፍያው ከ 321 ሺሕ እስከ 447ሺሕ ብር ነው። ለአዲስ ተማሪ መመዝገቢያ 146ሺሕ 200 ብር ሲሆን፣ ለመደበኛ ምዝገባ 225ሺሕ ብር ነው። ለውጭ ዜጋ ተማሪዎች ከ 675 እስከ 890ሺሕ የሚጠይቀው ሳንፎርድ ትምህርት ቤት ለምዝገባ 157ሺሕ ብር ያስከፍላል። ሳንፎርድ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ለሚያስከፍሉት ክፍያ የሚሰጡትን አገልግሎቶች አዲስ ማለዳ ብትጠይቅም መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በተጨማሪም ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ስኩል (ICS) ጥያቄዎቻችንን በኢሜል ማሳወቅ እንደሚገባ ገልጸውልን ብንጠይቃቸውም ይህ ጋዜጣ እስከታተመበት ቀን ድረስ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።

ፋስት መረጃ አገኘሁት ባለው መረጃ እንደጠቀሰው በኢትዮጵያ ይህን ያህል ገንዘብ የሚያስከፍሉ ትምህርት ቤቶች ነጻ የዋይፋይ አገልግሎት፣ ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎች፣ ትላልቅ የተሟሉ ቤተ መጻሕፍት፣ የሙዚቃ ማዕከል፣ ላብራቶሪዎች፣ የኮምፒውተር ማዕከል፣ የስፖርት አዳራሽ፣ የባስኬት ቦል ሜዳ፣ የቴኒስ ሜዳ፣ ዘመናዊ የእግር ኳስ ሜዳ፣ የመሮጫ ትራክ፣ ጂምናዚየም፣ ክሊኒክ ያላቸው መሆኑን ጠቅሷል። በተጨማሪም በአንድ ክፍል ከ15 እስከ 25 ተማሪ የሚማሩ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ የሚማሩት ተማሪዎች ከአንድ ሺሕ የማይበልጡ ናቸው።

በአሜሪካን የትምህርት ካሪኩለም የሚመራው ICS እጅግ ዘመናዊ ት/ቤት ሲሆን፣ በዚህ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በግለሰብ ደረጃ ክትትል ተደርጎባቸው ተሰጧቸውን እንዲያወጡ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። እስከ ዛሬ 12ኛ ክፍል የተፈተኑት ሁሉም ያለፉ ሲሆን፣ 15 በመቶዎቹ አገር ውስጥ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ሲሆን፣ ሌሎቹ በአሜሪካ እና በካናዳ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸውን ቀጥለዋል። ICS ትምህርት ቤት 12ኛ ክፍል ለጨረሱ ኹሉም ተማሪዎች የአሜሪካ ዲፕሎማ ይሰጣል።

ሰሚት የሚገኘው ዋን ፕላኔት ዓለም ዐቀፍ ትምህርት ቤት ከመዋለ ሕፃናት እስከ ኹለተኛ ደረጃ (ሀይስኩል) ያለው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር እንደ የግል ትምህርት ቤት ዕውቅና የተሰጠው ነው። ዋን ፕላኔት ዓለም ዐቀፍ ደረጃን የጠበቀ፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥርዓተ ትምህርት እና የማስተማሪያ ዘዴዎችን ይጠቀማል።

ለአዲስ ማለዳ መረጃውን ከሰጡንና ልጆቻቸው ዋን ፕላኔት ለማስተማር ካሰቡ ወላጆች መካከል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ኹለት ልጅ ያለው ወላጅ ስለሁኔታው አጫውቶናል። በዚህም መሠረት ትምህርት ቤቱ የትምህርት ክፍያ 75ሺሕ 825 ብር በተርም፣ የምዝገባ፣ የመግቢያ እንዲሁም የተጨማሪ ካፒታል ክፍያ ዓመታዊ እና አንድ ጊዜ የሚከፈል ካፒታል ሌቪ ባጠቃላይ 39ሺሕ 375 ብር ያስከፍላል። የተርም ክፍያው በዓመት ሦስት ጊዜ ሲሆን፣ ከትምህርት ቤት ክፍያው በተጨማሪ 18ሺሕ 900 ብር የዕቃ አቅርቦት ክፍያ እንደሚያስፈልግ ለአዲስ ማለዳ የደረሳት መረጃ ያሳያል።

ወላጆች በዋን ፕላኔት ከአንድ በላይ ተማሪ የሚያስተምሩ ከሆነ 10 በመቶ የትምህርት ቤት ክፍያ የሚቀንስ ሲሆን፣ ኹሉም ክፍያ በባንክ በኩል የሚፈጸም ነው። ትምህርት ቤቱ ክፍያውን ያስቀመጠው በዶላር ሲሆን፣ ለአገር ውስጥ ተማሪዎች ክፍያው በባንኮች የዶላር ምንዛሬ ተመንዝሮ የሚከፈል ነው።

ያነጋገርናቸው ወላጅ የተገለጸላቸው በብር እንደሚከፍሉ እንደሆነ የነገሩን ቢሆንም፣ ባንክ ላይ ባለው ዕለታዊ የዶላር ምንዛሬ የሚመሠረት በመሆኑ በቀጣይ ተርም ላይ በሚከፍሉበት ወቅት ጭማሪ እንደሚኖረው ይጠቅሳሉ።
በ1998 የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን የአገር ውስጥ ካሪኩለም መሠረት በማድረግ፤ ከስድስት ሺሕ ብር እስከ ሰባት ሺሕ ብር በተርም የሚያስከፍለው ሳፋሪ አካዳሚ፣ ባለፉት ኹለት ዓመታት ኮቪድ-19 ያደረሰውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም ወላጆች ላይ ጭማሪ ማድረጋቸውን የሳፋሪ አካዳሚ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መስከረም በለጠ ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰአት ቅርንጫፎቹን ስድስት ያደረሰው ሳፋሪ አካዳሚ፣ ባደረገው የዋጋ ጭማሪ ላይ ወላጆች እና የወላጅ ተወካይ ኮሚቴዎችን ያካተተ ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ አብዛኛው ወላጅ በጭማሪው ተስማምቶ ቀጥሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com