የእለት ዜና

ለ10 ዓመት የተጓተተው የሞጆ የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ በ2014 ወደ ፕሮጀክት ትግበራ እንደሚገባ ተገለጸ

ለ10 ዓመት የተጓተተው የሞጆ የተቀናጀ ቆዳ ኢንዱስትሪ ክላስትር ቅድመ ሥራዎች ተጠናቀው በ2014 ሙሉ በሙሉ ወደ ፕሮጀክት ትግበራ እንደሚገባ ተገለጸ።
የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ለአዲስ ማለዳ በላከው መረጃ፣ የሞጆ የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ ክላስተር (ፓርክ) ፕሮጀክት ሥራው ለአስር ዓመት ያህል ሲጓተት የቆየ መሆኑን አመላክቷል።

በመሆኑም ኢንስትቲዩቱ በዚህ ዓመት የቅድመ ፕሮጀክት ሥራዎች በቶሎ እንዲጠናቀቁና ወደ ዋናው የፕሮጀክት ትግበራ ሥራ እንዲገባ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ማቀዱን ገልጿል። ዕቅዱ እንዲሳካ አስፈላጊ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች እና አስፈላጊውን የክትትልና የድጋፍ ሥራ እንደሚያከናውንም ጨምሮ አመላክቷል።

አሁን ላይ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው የእያንዳንዱ ገበሬ የመሬት ይዞታ ተለክቶ የተጠናቀቀ መሆኑም በመረጃው ተመላክቷል። 193 ሔክታር መሬት ተለይቶ አርሶ አደሮችን የማሳመን ሥራውም መጠናቀቁን ኢንስትቲዩቱ ጠቁሟል። የመሬት ካሳው ተገምቶ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትን የካቢኔ ውሳኔ እየጠበቀ ሲሆን፣ የካሳ ክፍያ በጀት አስቸኳይ ውሳኔን ከሚሹ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው መሆኑ ተመላክቷል።

በተጨማሪም የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ የቆዳ ፍተሻ ላብራቶሪ፣ የሞዴልና የፋሽን ማሳያ ማዕከል፣ በሞጆ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ውስጥ ለመገንባት ከሞጆ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጋር መፈራረሙ የሚታወስ ነው። ዓላማውም የቆዳ ውጤቶችን የጥራት ደረጃ ለማረጋገጥ፣ ሞጆ አካባቢ ያለውን የአየር ብክለት ለመቀነስ እና የቆዳና የቆዳ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በአንድ ክላስትር ወደ ሞጆ እንዲሰባሰቡ ለማድረግ ነው።

በዚህ ዓመትም ኢንስትቲዩቱ ከሞጆ የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ ፕሮጀክት በተጨማሪ በሞጆ ከተማ የሚገኙ የቆዳ ፋብሪካዎች የገጠማቸው የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ችግር በቶሎ እንዲፈታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሠራ በዕቅዱ አመላክቷል።
ኢንስቲትዩቱ ሞጆ ላይ የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ ክላስተር (ፓርክ) መገንባቱ በተበታተነ መንገድ የሚሠሩ የቆዳ ፋብሪካዎችን በቅርበት ሆኖ በአንድ ክላስተር አሰባስቦ በመከታተልና በማሠራት በከተማዋ ብሎም በቆዳ ምርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ የሆነ ዕድገት እንደሚያስገኝ ተነግሮለታል።

የቆዳ ልማት ኢንስትቲዩት ከሞጆ የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ ክላስትር በተጨማሪ በቀጣይ ብዙ ልዩ ትኩረትንና ድጋፍን የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸን ገልጿል። እነዚህም የዘርፉ ዋና ማነቆዎች ሲሆኑ፣ የጥሬ ቆዳና ሌጦ አያያዝና ቁጥጥር ሥርዓትን ማሻሻል፤ የጨው ግብይትና አቅርቦትን ማሻሻል፤ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ሁኔታን ማሻሻል፤ እንዲሁም የኖራ አቅርቦት ችግርን በአስተማማኝ ሁኔታ ማሻሻል ናቸው።

ኢንስትቲዩቱ ሞጆን እንደ አገር የቆዳ ከተማ (ሌዘር ሲቲ) ለማድረግ በሐሳብ ደረጃ በዕቅድ ከአስር ዓመት በላይ ሲሠራበት እንደነበር መግለጹም ይታወቃል። በዚህም የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ተጠናቆ በሙሉ ዓቅሙ ሥራ ሲጀምር በቆዳ ዘርፍ ብቻ ከ15 ሺሕ እስከ 25 ሺሕ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር መገለጹ የሚታወስ ነው።

በኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የሞጆ የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ ክላስተር ፕሮጀክት አንዱ ትልቅ የትኩረት መስክና ግብ መሆኑ ተነግሯል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!