የእለት ዜና

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የኹለት እጁ እነሴ ወረዳ ተፈናቃይ ተማሪዎችን ሊቀበል ነው

የምሥራቅ ጎጃም የኹለት እጁ እነሴ ወረዳ አሥተዳደር በፌደራል መንግሥት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በቀሰቀሰው ጦርነት ከሰሜን ወሎ የተፈናቀሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምር ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
በጦርነቱ ኹሉም የትምህርት ተቋማት በመውደማቸው የነገ ተስፋ ሕፃናት ቤትና ምግብ አልባ ከመሆናቸውም ባሻገር፣ በቀላሉ ወደ ትምህርት ተቋማት የማይመለሱ መሆናቸው አሳስቦኛል የሚለው የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር፣ ተማሪዎቹን ተቀብሎ ሙሉ ወጫቸውን በመሽፈን በዞኑ በሚገኙ 57 ትምህርት ቤቶች ለአንድ ዓመት እንደሚያስተምራቸው ነው የገለጸው።

በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት ጦርነት ሳቢያ “ወላጆቻቸውን ያጡ፣ ቤት ንብረት የሌላቸውና ወላጆቻቸው የሕልውና ዘመቻው ላይ ያሉ” ተማሪዎችን ከሰሜን ወሎ ዞን ተቀብለው ለማስተማር ከማኅበረሰቡ ጋር በመወያየት “አንድ ወላጅ ለአንድ ተማሪ” ብለው መስማማታቸውን ነው በምስራቅ ጎጃም ዞን የኹለት እጁ እነሴ ወረዳ አሥተዳዳሪ ተመስገን ዘውዴ የተናገሩት።

አሥተዳዳሪው እንደተናገሩት ከሆነ፣ አቀባበሉን በተመለከተ በተማሪዎቹ ፍላጎት መሠረት ኹለት ዓይነት አማራጭ ያቀረቡ ሲሆን፣ ይኸውም በመጠለያ (በካምፕ) ሆነው መማር ለሚፈልጉ መጠለያ እንዳዘጋጁና ከወላጆች ጋር ተጠግተው መማር ለሚፈልጉ ለአንድ ተማሪ አንድ ወላጅ በመስጠት የዓመቱን ትምህርት እንዲከታተሉ ማድረግ እንደሚችሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ተመስገን አክለውም፣ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንና በምስራቅ ጎጃም ዞን በሚገኙት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቹን መድበው የማስተማር ዓቅሙ እንዳላቸው አብራርተዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን አካባቢ ሠላም በመሆኑ ትምህርት ለመጀመር ምዝገባ ላይ ቢሆኑም፣ የሰሜን ወሎን ችግር በማስመልከት ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይት አድርገው የአካባቢው ማኅበረሰብ በበኩሉ ተማሪዎቹን ተቀብሎ ለልጆቹ የሚያደርገውን ተመሳሳይ እንክብካቤ በመለገስ ለማስተማር በደስታ መስማማቱን ነው አስተዳዳሪው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

አስተዳዳሪው አክለውም፣ በ57ቱ ትምህርት ቤቶች ያሉ መምህራን በአካባቢው ያሉ ተማሪዎችን እንደሚያስተምሩት ተፈናቃይ ተማሪዎቹንም ለማስተማር ፈቃደኛ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ከ 30ሺሕ በላይ የአካባቢው ተወላጅ ተማሪዎችን የሚያስተናግድ ቢሆንም፣ የሚቀበሏቸው ተማሪዎችን እስካሁን በሚሠሩበት ’’የተማሪ-መምህር ጥምርታ’’ መሠረት በእያንዳንዱ ክፍል ስለሚጨምሯቸው እስካሁን ባለው ሁኔታ ተጨማሪ መምህርና ክፍል እንደማያስፈልጋቸው አስተዳደሪው ተናግረዋል።

አያይዘውም የሚቀበሏቸውን ተማሪዎች ብዛት አረጋግጠው ተጨማሪ መምህር ካስፈለገ ከሰሜን ወሎ ዞን ጋር በመመካከር ተፈናቃይ መምህራን ከተማሪዎቹ ጋር ለማምጣት ማቀዳቸውን ጠቁመዋል።
ተጨማሪ መምህራን ካስፈለገ እንጨምራለን ያሉት አስተዳዳሪው፣ የሚመጡት መምህራን ደሞዛቸው በአማራ ክልል መንግሥት ከተከፈላቸው፣ ቀለባቸውንና መኖሪያ ቤት ተዘጋጅቶላቸው፣ ልጆቹን ዓመቱን ሙሉ አስተምረው ካርዳቸውን ይዘው ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ተግባር እንጂ በተለየ መልኩ መምህራን ለመቅጠር እንዳላሰቡም አመላክተዋል።

ከማኅበረሰቡ ጋር በነበራቸው ውይይት ለታዳጊዎቹን አሁን ካልደረስንላቸው መቼም ልናግዛቸው አንችልም በማለት አቋማቸውን የገለጹት በጎ አድራጊዎቹ፣ ካሏቸው 57 ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ “ጎረቤት ወረዳዎችም ለተመሳሳይ ተግባር ዝግጁ ስለሆኑ” ከሰሜን ወሎ የሚያመጧቸውን ተማሪዎች ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታቸው ሳይለዩ ማስተናገድ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

አስተዳደሪው አክለውም ትምህርት የሚጀመረው መስከረም 24 በመሆኑ ተማሪዎችን በመመዝገብ ላይ እንደሆኑና ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ከሰሜን ወሎ ዞን የተፈናቀሉ ተማሪዎችን መቀበል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

“በትህነግ ሴራ እየተመሰቃቀለ ያለው ሕዝባችን እስካሁን ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል” የሚሉት ተመስገን፣ ከአሁን በፊት 4.1 ሚሊዮን ብር፣ 560 ኩንታል እህል፣ 16 በሬዎችና 22 ፍየሎች ጎንደር ለሚገኝው መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ድጋፍ እያበረከቱ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

አዲስ ማለዳ በፌደራል መንግሥት በኩል በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በሚሰነዝረው ጥቃት ሰዎች ከተለያዩ የሰሜን ወሎ አካባቢ በመፈናቀል በደሴ፣ በኮምቦልቻና በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚገኙ ስትዘግብ መቆየቷ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com