የእለት ዜና

በካማሺ ዞን ጅጋንፎይ ወረዳ በንጹኃን ዜጎች ላይ በታጣቂዎች ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ

ከ10 በላይ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ታግተዋል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መስከረም 3/2014 ካማሺ ዞን፣ በለው ጅጋንፎይ ወረዳ በታጠቁ ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን እና ንጹኃን ዜጎች መሞታቸውን የወረዳው ነዋሪዎች ገለጹ።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የበለው ጅጋንፎይ ወረዳ ነዋሪዎች ጥቃቱ በተደጋጋሚ እንደሚፈጸም ጠቅሰው፣ በወረዳው ያሉ የክልሉ የልዩ ኃይል አባላት እስካሁን ምንም መፍትሔ ባለማምጣታቸው ችግሩ እየተባባሰ መሆኑን ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ አያይዘውም መስከረም 3/2014 ከአስር የሚበልጡ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት እና ሰባት ንጹሐን ዜጎችን በታጣቂ ኃይሉ መታገታቸውን ጠቁመዋል። በታጣቂ ኃይሉ ታግተዋል የተባሉት የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት እና ንጹሐን ዜጎች እስካሁን ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በተመሳሳይ መስከረም 3/2014 ታጠቂ ኃይሎቹ ኹለት የመንግሥት መኪናዎችን በመዝረፍ አንዱን አቃጥለው ሌላኛውን ደግሞ ይዘው መሄዳቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
በአካባቢው የሚኖሩ ግለሰቦች በተደጋጋሚ በሚከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ላለፉት ኹለት እና ሦስት ወራት በአካባቢው ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም ብለዋል። የጸጥታው ኹኔታ እየተባባሰ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ በዚህም ምክንያት የንግድም ሆነ ሌሎች መሠረታዊ እንቅስቃሴዎች፣ ባንኮች እና ሱቆችን ጨምሮ በመዘጋታቸው እየተቸገርን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በአካባቢው እየተንቀሳቀሰ ያለው ታጣቂ ቡድን ንጹኃንን በመግደል እና ሕፃናትንም ጭምር በማገት በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የአይን እማኞች ተናግረዋል። “በተለይ በአሁኑ ሰዓት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አለመኖሩን በመጠቆም ወደ የትም ሔደን መሸሽ የማንችልበት ሁኔታ ላይ ነን” ሲሉ የወረዳው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የክልሉ የልዩ ኃይል አባላት ጥቃቱን መመከት እንዳልቻሉም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። የወረዳው የመንግሥት ባለሥልጣናት እየተፈጸመ ባለው ጥቃት ዙሪያ ምንም አይነት ምላሽ እየሠጡ አለመሆናቸው ችግሩን አባብሶታል ሲሉ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

“በአሁኑ ወቅት በወረዳው ከፍተኛ የሆነ ችግር መኖሩ የማይካድ ሐቅ ነው፤ ስለሆነም መንግሥት እና የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍተሔ ሊሰጠን ይገባል” ሲሉ የተናገሩ የወረዳው ነዋሪ ላለፉት ወራት ከደረሰው እና አሁንም እየደረሰ ካለው ጥቃት ራሳችንን የምንከላከልበት ዓቅም የለንም ነው ያሉት።

አስተያየት ሰጭዎቹ በአካባቢው በየጊዜው በሚፈጠረው ጥቃት ምክንያት ነዋሪዎች ወጥቶ ለመግባት እንደ ተቸገሩ አንስተው፣ የዕለት ጉርስ ለማግኘት ሥራ መግባት እና ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ግብዓቶችን ለመግዛት ወደ ሱቆች መሄድ እንዳልቻሉ ጠቁመዋል። አያይዘውም “እኛ በአሁኑ ሰዓት የቁም እስረኞች ሆነናል፤ መንግሥትም አፋጣኝ ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል” ብለዋል።

አዲስ ማለዳ በካማሺ ዞን በንጹኃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት እና የመንግሥት የጥበቃ ችግር ተስተውሏል መባሉን በተመለከተ ከክልሉ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

በክልሉ በካማሺ እና በመተከል ዞኖች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እልባት ሳያገኝ እስካሁን መዝለቁን ተከትከሎ የዞኖቹ ነዋሪዎች ለግድያ፣ ለመፈናቀልና ለንብረት ውድመት እየተዳረጉ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በመተከል ዞን የክልል ልዩ ኃይሎችና መከላከያ ሠራዊት ተሠማርተው በክልሉ ከሚንቀሳቀሠው ታጣቂ ኃይል ዜጎችን ከጥቃት ለመታደግ እየሠሩ እንደሚገኝ መንግሥት መግለጹ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!