የእለት ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ2 ዓመታት በኋላ ወደ ናይጄሪያ ኢኑጉ ከተማ የድጋሚ በረራ አገልግሎት ሊጀምር ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ ናይጄሪያ ኢኑጉ ከተማ የድጋሚ በረራ አገልግሎት ሊጀምር መሆኑን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ናይጄሪያ ቢሮ ሀላፊ ሽመልስ አራጌ በትላንትናው ዕለት አስታውቋል፡፡

አየር መንገዱ የድጋሚ በረራውን ከመስከረም 21 ቀን ጀምሮ ሲጀምር ቦይንግ 787 አውሮላንን እንደሚጠቀም ተገልጿል፡፡
ወደ ከተማዋ የሚደረገው በረራ በሳምንት ሶስት ቀናት ማለትም ዘወትር ረቡዕ፣ አርብ እና ቅዳሜ መሆኑን ሀላፊው ጨምረው ተናግረዋል፡፡

መስከረም 21 ቀን ናይጄሪያ ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጣችበት ቀን መሆኑን አስታውሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ናይጄሪያ መብረር ከጀመረበት እ.ኤ.አ ከ1960 ጀምሮ በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከሩን ተናግረዋል፡፡

በዚህ የነጻነት ቀን ወደ ኢኑጉ ከተማ በረራ መጀመር ደግሞ አሁንም በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ መካከል የነበረውን የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ያጠናክረዋል ብለዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወደ ናይጄሪያዋ ኡኑጉ ከተማ ይደረግ የነበረው በረራ እኤአ በ2019 የተቋረጠው የናይጄሪያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በኢኑጉ ከተማ የሚገኘውን የአካኑ ኢቢያም አለማቀፍ አየር ማረፊያ ለጥገና እንዲዘጋ በመወሰኑ ነበር፡፡

የኢኑጉ ከተማ አየር መንገድ ለጥገና ከመዘጋቱ በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ከተማዋ ዓለም አቀፍ በረራ የሚያደርግ ብቸኛው አየር መንገድ እንደነበር ያስታወሱት ሀላፊው አሁን ላይ አስፈላጊው ጥገና ተደርጎለት ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!