የእለት ዜና

በኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ የተሰየመው አደባባይ የፊታችን እሁድ ይመረቃል

በኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ አዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተሰየመው አደባባይ የፊታችን እሁድ እንደሚመረቅ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና የለሚ ኩራ ክፍል ከተማ በሰጡት የጋራ መግለጫ አስታውቋል።

በመግለጫቸውም በአፍሪካ የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ሴት የኦሊምፒክ ባለድል በመሆን የበርካታ አትሌቶች የጀግንነት ምሳሌ አደባባይ መሰየሙ እንደሚያስደስታቸው ገልጸዋል።

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አሊያስ ሙሀመድ፤ በጀግናዋ አትሌት ስም በክፍለ ከተማችን አደባባይ በመሰየሙ እንኮራለን በማለት፤ እንደ ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ አይነት ዓለም አቀፍ ጀግኖችን ማክበር ሌሎች ጀግኖችንም ለማፍራት ያግዛል ብለዋል።

በመሆኑም በጀግናዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ስም የተሰየመው አያት የሚገኘው አደባባይ የፊታችን እሁድ በይፋ ይመረቃል ብለዋል።

ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ተሉ እ.ኤ.አ በ1992 የባርሴሌና ኦሊምፒከም በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት ለሴት ጥቁር አፍሪካዊያን ፈር ቀዳጅ አትሌት ናት።

በሲዲኒ ኦሊምፒክም ለኢትዮጵያ ወርቅ አምጥታለች፤ ከዚህም ባለፈ በርካታ ድሎችን በማስመዝገብ ስሟ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ ይጠራል።

ፍልቅልቋ አትሌት ኮሎኔል ደራርቱ ተሉ አሁን ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳነትነት እየመራች ትገኛለች።

በእለቱ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማድረግ ዓላማ ያደረገ የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ይካሄዳል መባሉንም ኢዜአ ዘግቧል።

አደባባዩን በኦሊምፒክ አርማ የማስዋብና አረንጓዴ የማድረግ ስራዎች ተከናውኗል ያሉት ደግሞ የክፍለ ከተማው ስፖርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አበበ አንሙት ሲሆኑ፤ በእለቱ ለሚካሄደው የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር የተለያዩ ዝግጅት ተደርጓል፤ የመወዳደሪያ ማሊያውም በክፍለ ከተማው ሁሉም ወረዳዎች ይገኛል ብለዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com