የእለት ዜና

“ዓለም ዐቀፍ ተቋማት አንኳር ሥራቸው ሰብኣዊነት እንጂ ፖለቲካ አይደለም” በአዲስ አበባ የሚገኙ የአማራ ክልል ተወላጆች

ዓለም ዐቀፍ ተቋማት አንኳር ሥራቸው ሰብኣዊነት እንጂ ፖለቲካ አይደለም! ስለሆነም በሰሜን ወሎ፣ ዋግምራ እና በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች በአፋጣኝ ሊደርሱላቸው ይገባል ሲሉ በአዲስ አበባ የሚገኙ የአማራ ክልል ተወላጆች ጠየቁ።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የአማራ ክልል ተወላጆች አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ዋና ፅህፈት ቤት በር ላይ በዛሬው ዕለት መስከረም 11/2014 ማለዳ በመገኘት የተቃውሞ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

በተቃውሞ ሰልፉ ላይም “የዓለም ዐቀፍ ተቋማት በትግራይ ክልል ውስጥ ገብተው ድጋፍ እንዳደረጉት ሁሉ፤ በአማራ ክልልና በአፋር ክልልም በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች ሊደርሱላቸው ይገባል።” ሲሉ ጠይቀዋል።

በሰሜን ወሎ፣ በሰሜን ጎንደር፣ በዋግምራ፣ በመርሳ፣ በቆቦና መሰል በአማራ ክልል በሚገኙ አካባቢዎች ላሉ ዜጎች የመድኃኒት እና የምግብ ድጋፍ ሊያደርስላቸው ይገባልም ብለዋል።

“የአሜሪካው የረድኤት ድርጅት (USID)፣ የአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP)፣ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅትን (UNICEF) ጨምሮ የዓለም ዐቀፍ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት፤ በእነዚህ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ምንም ዓይነት ድጋፍ ሲያደርጉ አላስተዋልንም።” ያሉት ሰልፈኞቹ ተቋማቱ በአስቸኳይ በረሃብ እና በመድኃኒት እጦት እየተቸገሩ ወዳሉት አካባቢዎች በመሄድ ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!