በሶማሌ እና ኦሮሚያ 23 ከመቶ ሴቶች የሰብኣዊ መብት ጥሰት ሰለባ ናቸው ተባለ

0
678
  • ከእነዚህ ውስጥ 66 በመቶ የሚሆኑት ስለጥቃቱ ለማንም አይናገሩም

በሶማሌ እና በኦሮምያ ክልሎች ከሚገኙ ሴቶች ውስጥ 23 በመቶ የሚሆኑት የአካላዊ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን በጥናት ማረጋገጡን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ። 34 ከመቶ ሴቶች በትዳር አጋሮቻቸው ጥቃት ሲደርስባቸው፤ ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶች መካከል 29 ከመቶ አካላዊ ጉዳት ይደርስባቸዋል፤ ከእነዚህ መካከል 23 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ እርዳታ እንደሚጠይቁም ለማወቅ ተችሏል።

ሰኔ 14 እና 15/2011 የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ የኀይል ጥቃቶችን ለመከላከል፣ ብሎም ለማስቆም በአዳማ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባዘጋጀው 8ኛ አገር ዐቀፍ ጉባኤ ላይ፣ 23 ከመቶ ሴቶች አካላዊ ጥቃት፣ 10 ከመቶ ፆታዊ ጥቃት፣ 4 ከመቶ በእርግዝና ወቅት አካላዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተገልጿል።

በኮሚሽኑ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ኮሚሽነር መሰረት ማሞ በጉባዔው መክፈቻ እንደተናገሩት በሴቶች እና በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ የኀይል ጥቃቶች የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች ከመሆናቸው በተጨማሪ የጤና፣ የማኅበራዊ እና የሥነ ልቦናዊ ችግሮች በማስከተል የአካል ደኅንነትን፣ በሕይወት የመኖር መብትን እስከ ማሳጣት የሚደርሱ መሆናቸው ይታወቃል ብለዋል።

በአገራችን በሴቶች እና በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ የተለያዩ የኀይል ጥቃቶችን ለመዋጋት፣ ለማስቆም ትልቁና ዋነኛው ዋስትና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት የኀይል ጥቃቶችና ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በተመለከተ በግልጽ ሊወገድ የሚገባ ስለመሆኑ ማረጋገጡ። ያሉት ኮሚሽነሯ፣ ሕገ መንግሥቱ ለሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ ከፍተኛ ትኩረት ከመስጠቱም በላይ በአገራችን የተፈረሙ ዓለም ዐቀፍ እና አሕጉራዊ የሰብኣዊ መብት ስምምነቶች የአገሪቱ ሕጐች አካል እንደሆኑ እና ለዜጐች ሰብኣዊ መብቶች ሰፊ ከለላን የሰጠ መሆኑን ጠቅሰው በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱ ሰብኣዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ኀላፊነት የሕግ አውጪው፣ የሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው እንዲሁም የመላው ዜጐች ኀላፊነት እንደሆነ መደንገጉ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ መገንዘብ አያዳግትም ብለዋል።

የአሜሪካው ተራዶ ድርጅት ዩ.ኤስ.ኣይ.ዲ (USAID) በ2009 በኢትዮጵያ ባስጠናው ጥናት መሰረት ከ50 እስከ 60 ከመቶ የሚሆኑ ሴቶች በቤት ውስጥ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ማስታወቁ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here