የእለት ዜና

በቻይና በተካሄደ የሮቦት ውድድር ላይ ኢትዮጵያዊያኖች አሸናፊ ሆኑ

በቻይና ቤይጂንግ በተካሄደ የሮቦት ውድድር ላይ በቲያንዢን ቴክኖሎጂ እና ኢጁኬሽን ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆኑ አምስት ኢትዮጵያውያን የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆን ችለዋል።

በውድድሩ የተሳተፉት ሰላሙ ይስሃቅ፣ አባኩማ ጌታቸው፣ ፀጋዬ አለሙ፣ ዮሐንስ ኃ/መስቀልና ሄኖክ ሰይፉ የተባሉ ኢትዮጵያውን ሲሆኑ፤ በተወዳደሩበት ዘርፍ፣ ሰላሙ ይስሃቅ የወርቅ፣ አባኩማ ጌታቸው እና ፀጋዬ አለሙ ደገረሞ የብር ሜዳሊያ አግኝተዋል።

በተጨማሪም ዮሐንስ ኃ/መስቀል እና ሄኖክ ሰይፉ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ እንዲሁም የዋንጫ ተሸላሚዎች መሆናቸው ታውቋል።

የወርቅ ተሸላሚው ሰላሙ ይስሃቅ ስለውድድሩ ሲያብራራ ኢትዮጵያውያኑ በትራይ ኮ ሮቦትስ ኤንድ አፕሊኬሽን (“Tri-Co” Robots and Robot Application) ዘርፍ መወዳደራቸውን ያስረዳል።

ውድድሩ ሦስት ሰዓታት የተሰጠው ሲሆን፤ በእነዚህ ሰዓታት ተነጣጥለው የተቀመጡና ግዑዝ የሆኑ አካላትን ገጣጥሞ ‘ህይወት መዝራት’ና የሚሰጠውን ተልዕኮ የሚፈጽም ሮቦት ዝግጁ ማድረግ ደግሞ ከተወዳዳሪዎች የሚጠበቅ ተግባር ነው።

በቻይና ቤይጂንግ በተደረገው በዚህ ውድድር የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው ሰላሙ ይስሃቅ ይህንን ተግባር በአንድ ሰዓት ከ53 ደቂቃ በማጠናቀቅ አሸናፊ ሆኖ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።

ከቀናት በፊት በተካሄደው በዚህ ውድድር ከ20 ዩኒቨርስቲዎች፣ የምርምርና የንግድ ተቋማት የተወጣጡ 2ሺህ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ሰላሙ ያሸነፈው በኢንደስትሪያል ሮቦቲክስና ሰው ሰራሽ ልህቀት ዘርፍ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com