የእለት ዜና

የ2014ን የመስቀል በዓል በሠላም ለማክበር ኹሉም የሕብረተሰብ ክፍል ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተገለጸ

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በሚከበረው የመስቀል በዓል ላይ ከአምናው የተሻለ በዛ ያለ ቁጥር ያለው ሰው ተካፋይ እንደሚሆን ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ በላይ ትላንት የበዓሉን አከባበር በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ ለበዓሉ ከውጭ አገር የተለያዩ የኃይማኖት አባቶችና የውጭ ዜጎች ይገባሉ በማለት ነው የገለጹት።
ምክትል ሥራ አስኪያጁ እንደተናገሩት ከሆነ፣ በዓሉ ሠላማዊ እንዲሆን ኹሉም ሰው የሠላም አምባሳደር መሆን አለበት በማለት ነው መልዕክታቸውን ያስቀመጡት።
አያይዘውም አምና በሆሳዕና ከተማና በተለያዩ የደቡብና የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ከይዞታ ጋር በተገናኘ የመስቀል በዓል ያልተከበረባቸው ቦታዎች እንደነበሩም ነው የጠቆሙት።
ዘንድሮም ምዕመናኑ በዓሉን በሠላማዊ መንገድ እንዲያከበሩ ለማስቻል ቤተክህነት ምን ሠርታለች ተብለው የተጠየቁት ቀሲስ በላይ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች በኹሉም የአገሪቱ ክፍል የዕምነት ተከታዮች የደመራ በዓልን በሠላም እንዲያከብሩ ጥሪ አስተላልፈናል በማለት ነው የተናገሩት።
መስቀል አደባባይ በአዲስ መልኩ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው የመስቀል የደመራ በዓል ከእስካሁኑ በተለየ መልኩ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ የአከባበር ሥነ-ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅ መሆኑም ተመላክቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com