የእለት ዜና

የሔር ኢሴ ባህላዊ ሕግ በዓለም ቅርስነት ለማስመዘገብ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ

የሔር ኢሴ የኢሣ ማኅበረሰብ ባህላዊ ያልተጻፈ ሕግን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ።
የሔር ኢሴ ባህላዊ መተዳደሪያ ሕግ በሱማሌ ክልል፣ ሲቲ ዞን በ16ተኛው ክፍለ ዘመን 44 የኢሣ ማኅበረሰብ አባላት ተቀምጠው ያጸደቁት መሆኑነን ‹የሲቲ ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን› ኃላፊ አያን አሊ ገለጹ።
ከዛን ወቅት ጀምሮም የሱማሌ ሕዝብ አንድ አካል የሆነው ኢሣ ማኅበረሰብ ሕጉን ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል እየተቀባበለ እየተመራበት እንደቆየ ነው የተነገረው።
ሕጉ በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና ሱማሌ ላንድ የሚገኙትን የማኅበረሰቡን አባላት ያስተሳረ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ ባህላዊ ሕጉ ኢትዮጵያ ለምትገነባው የዘመናዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግብዓትነት ያግዛልም ተብሏል።
በዓለም ቅርስት እንዲመዘገብ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት አያን አሊ፣ ቅርሱ ሲመዘገብና ሲተዋወቅ የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ይበልጥ ያስተሳስራል ሲሉ ነው የገለጹት።
አያይዘውም፣ የማኅበረሰቡን ባህላዊና ታሪካዊ የጋራ ዕሴቶች ከማስተዋወቅ ባለፈ፣ ለቱሪስት መስህብነት በመዋል በጋራ የማደግ ራዕይን እንደሚያጠናክርም ነው የጠቆሙት።
በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሚዳሰሱ ቅርሶችን በዓለም ዐቀፍ ቅርስነት ማስመዝገብ የሚያስችል ሰነድ ዋና አዘጋጅ ገዛኻኝ ግርማ በወቅቱ የገለጹት፣ ባህላዊው ሕግና ሥርዓቱ በትውልድ ቅብብሎሽ እየዳበረ የመጣ መሆኑን ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com