የእለት ዜና

የአሜሪካ ስሞታ

ሠሞኑን መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው በሙሓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ አሜሪካና ጀሌዎቿ የሰነዘሩት ስሞታ ነው። በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ ያለውና በጽንፈኞች እንደሚጠላ የሚነገረው አንደበተ ርትዑ ዲያቆን፣ ከሰሞኑ መነጋገሪያ የሆነው በአንድ አዳራሽ ተናገረ በተባለው ንግግር ሳቢያ ነው።

ለተለያዩ ሥልጣኖች ሲታጭ እሪይ የሚልበት የማያጣው የቀጣዩ የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆነው ዳንኤል፣ የመንግሥት አማካሪ መሆኑ ይፋ ከተደረገ ወዲህ የማይወደው መጨመሩ ቢነገርም፣ ዝናው ውቅያኖስ ተሻግሮ ይሄዳል ብሎ የጠበቀ አልነበረም።
አሜሪካ ዜጎቿ የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጥላቻ ንግግር ከመናገር አልፈው “ፍለጠው፤ ግደለው” እያሉ ሲቀሰቅሱ ሰምታ ዝም እንዳላለች፣ ጥቆማ ሲደርሳትም ሰበብ አስባብ እየሰጠች እንዳላማኸኘች አሁን ደርሳ ገምጋሚ መሆኗና ይቅርታ ይጠይቁ ማስባሏ ብዙ ትችት አሰንዝሮባታል።

አንድ ዘር ከምድረ ገጽ ይጥፋ አለ ብለው ነገሩ ሳይገንና አሜሪካም እንደእርጎ ዝንብ ጥልቅ ሳትልበት በፊት አንዳንዶች ጉዳዩን ለማጦዝ ሞክረው የነበረ ቢሆንም፣ የድጋፍ አጸፋውን ግን የቻሉት አይመስልም ነበር። በተለይ የንግግሩን ቪዲዮ በመልቀቅ ዘርን እንዳልጠቀሰ ለማሳመን የተሄደበት መንገድ ወሬውን ብዙ ሰው እንዲቀባበለው አድርጓል።

የአሜሪካ መንግስት አሸባሪ ተብሎ በመንግስት ለተፈረጀ አካል ተቆርቁሮ ሳይሆን፣ በመድረኩ ላይ ቀጥሎ የተናገረውን የውጭ ኢንቬስተርን የተመለከተውና እርስ በርሳችን እንረዳዳ የሚለው አስተያየት አበሳጭቷቸው ነው ያሉ አልጠፉም። አሜሪካ ያን ያህል ከነአስተሳሰባቸው ይጥፉ ከተባሉት ቡድኖች በላይ ተቆርቋሪ ሆና፣ ታሪካቸው ከመዝገብ ይደምሰስ ለልጆቻችንም የክፉ ነገር ምሳሌ እናድርጋቸው መባሉ በይበልጥ፣ እሷ ለግማሽ ክፍለዘመን የለፋችበትን ስለሚያከስምባት ተናዳ ነው ያሉም አሉ።

ያም ተባለ ይህ፣ ጉዳዩ ለቀናት በማኅበራዊ ትስስር ገጾች እየተንሸራሸረ ብዙዎች አስተያየታቸውን እንዲሁም ድጋፋቸውን ከጎንህ ነን በሚል ዘመቻ አሰምተዋል። ‹አለ› የተባለው እንዳልተባለ ማስተባበያ ቢነገርም፣ እኛ የመሰለን እንደዛ ነው በሚል ትችት ከመሰንዘር ያልተቆጠቡም ነበሩ።

በሌላ በኩል፣ ምንም ቢባል የማይበርዳቸው እሱን ከመደገፍ ወደ ኋላ የማይሉ በርካቶች የመኖራውን ያህል፣ ምንም ቢናገርና ቢሠራ የማይጥማቸው እንዳሉ ይታወቃል። ኃይማኖት አንዱ መለያያ ምክንያት እንደሆነ የሚናገሩ ቢኖሩም፣ ፖለቲካው እንጂ ሌላ ያጣመራቸው ባለመሆኑ በስራው ይደገፋል በማንነቱ ይጠላል የሚሉ አሉ።

የሙሓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጉዳይ ይህን ያህል ከአገር ውጭ ጭምር መነጋገሪያ መሆኑ የገረማቸው በርካቶች ናቸው። እንዲህ አይነት ያልተጨበጠ ወሬ እያነፈነፉ ለውጮቹ የሚያቀብሉትን የኮነኑ አስተያየት ሰጪዎችም አልታጡም። በተጮኸ ቁጥር ምላሽ በመስጠት ጊዜ መባከን እንደሌለበት፣ እንዲሁም ወርቅን ምንም በአቧራ ለመሸፈን ቢሞከር ወርቅነቱን አያስቀሩትም በማለት የተቺዎቹ ሙከራ እንደማይሳካ ብዙዎች ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com