የእለት ዜና

የመስቀል በዓልና ድባቡ

የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ከሚከበሩት ዓመታዊ በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ችቦ ለኩሰው ደመራ በመደመር በዓሉን በደማቅ ሁኔታ ሲያከብሩት ይስተዋላል፡፡
በዓሉ በሁሉም አካባቢዎች የሚከበር ሲሆን፣ በደበቡ አካባቢ በተለይም በጉራጌ፣ ሲዳማ፣ ከንባታ፣ ወላይታና ሐድያ አካባቢዎች በአንድ ቤተሰብ ውስጥ “ሻኛው ሞላ ያለ” በሬ በማረድ ከሌሎቹ አካባቢዎች ለየት ባለ ባህል ለአስር ቀናት እንደሚከበር ይታወሳል፡፡
ከባለሃብቶች ጀምሮ በቀን ሥራ እስከሚተዳደሩት ግለሰቦች ድረስ ያሉ የጉራጌ ተወላጆች በዓሉን ለማክበር የሚያስችል የዕርድ በሬ ዓመቱን ሙሉ ብር በመቆጠብ አንድ ፍሬዳ አስከ 98ሺሕ ብር ወጭ አድርገው በመግዛት እንደሚያከብሩት ይነገራል፡፡ በበዓሉ ዕለት ይህን ያላደረገና ያልተሳተፈ “በወላጆች ዘንድ ይረገማል” የሚል ባህል እንዳላቸው ይታመናል፡፡
“ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንጂ ጎጂ ባህል” ባይኖርም፣ በእነዚህ አካባቢዎች በየዓመቱ “ያለፈና የተንዛዛ ድግስ” መደገሱ፣ በተለይም አሁን ከሚስተዋለው የኑሮ ውድነትና ጦርነት ጋር ተያይዞ ለኢኮኖሚ ማሽቆልቆል እንደሚዳርግ ይታመናል፡፡
የአዲስ ማለዳው ኢዮብ ትኩዬ በዓሉን አስመልክቶ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችንና የታሪክ ምሁራንን በማነጋገር የሐተታ ዘማለዳ ርዕስ አድርጎታል፡፡

ሰለሞን ገብረመስቀል ይባላሉ። ተወልው ያደጉት በጉራጌ ዞን በምትገኘው እዣ ወረዳ ሲሆን፣ ዕድሜቸው ለትምህርት ሲደርስ የግራሬ ተብሎ በሚጠራው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመዝግበው ትምህርታቸውን መከታተል ችለዋል። ሰለሞን በዚህ ወቅት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ሙያ እያገለገሉ ይገኛሉ።

ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚሳተፉበት በአደጉበት አካባቢ ዓመቱን ጠብቆ የሚከበረው የመስቀል በዓል ሁሌም እንደሚናፍቃቸው የሚናገሩት ሰለሞን፣ በአባቶች ዘንድ የሚደረገው ምረቃ፣ ችቦ ለኩሶ መቦረቁ፣ እንዲሁም ሰንሠለታቸውን ጠብቀው የሚከናወኑት የባህል ዝግጅቶች፣ በተለይም በዓሉ ሲቃረብ በትዝታ በአእምሯችው ውስጥ እየመጡ አንዳች ደስታን እንደሚለግሷቸው ያወሳሉ።

ዓመቱን ጠብቆ የሚመጣውን በዓል ለማክበር ሁሌም በጉጉት የሚጠብቁት ሰለሞን ገብረመስቀል፣ በዓሉ ከመድረሱ በፊት ለበሬ መግዣ የሚሆን ብር መቆጠብ የእለት ተእለት ተግባራቸው ከሆነ ዘመናት ተሸኝተዋል።
የ2014 የመስቀል በዓልን ለማክበር የሚያስፈልጉ አስቤዛዎችን ለመግዛት ዓመቱን ሙሉ ብር የቆጠቡ ሲሆን፣ የእርድ በሬውን ቀድሞ ቤተሰብ እንዳዘጋጀ ስለተነገራቸው ሌላ ለቤተሰብ የሚያበረክቱት ልብስ፣ ቅቤ፣ ሳሙና፣ በርበሬና ስኳር በቅድሚያ አዘጋጅተው መጨረሳቸውን ተናግረዋል።

በጉራጌ አካባቢዎች የመስቀል በዓል ለተከታታይ አስር ቀን እንደሚከበር የሚናገሩት ሰለሞን፣ “ወሪያት ያህና” ተብሎ በመሰየም ከመስከረም 13 ጀምሮ የሚከበረው በዓል ላይ ለመሳተፍ ቀድመው ወደ ቤተሰቦቻቸው ጎራ በማለት ሲናፍቁትና ሲጓጉለት የነበረውን በዓል አሐዱ ብለው ማክበር እንደሚጀምሩም አብራርተዋል።

እንደ ሰለሞን አገላለጽ ከሆነ፣ ወሪያት ያህና ማለት የተፈጠረውን ናፍቆትና ጉጉት ለመወጣት የእንቅልፍ አልባ ቀን የሚዘከርበት ዕለት ነው። በዚህም ዕለት ሲናፍቁት የነበረውን ቤተሰባቸውንና የባህል ፍሰቱን ተጋርተው እፎይታን ለማግኘት ሳይቸኩሉ የቀሩ አይመስሉም።
በተለይም መስከረም 14 ቀን የሚከናወነውን የእርድ ዋዜማ ከአባቶች ጎን ለጎን ተሰልፈው ለመሳተፍና በዓሉ ከመድረሱ ኹለት ወር ገደማ ቀድሞ በሴቶች ዘንድ ተዘጋጅቶ የሚቀርበውን የእንፋሎት ቆጮ፣ አይብ፣ ጎመንና “በልዩ ጣዕም” የሚሰናዳውን የጉራጌ ክትፎ ከቤተሰባቸው ጋር ተሰባስበው በፍቅር ለመመገብ ቀኗን ደረሰች አልደረሰች እያሉ በተስፋ እየጠበቀዋት እንደሆነ ነው የገለጹት።

በጉራጌ የመስቀል በዓል አከባበር የደመራ ቀን፣ የልጆች ደመራና የአባቶች ደመራ ተብሎ እንደሚከፈል የጠቆሙት ሰለሞን፣ መስከረም 14 ቀን የሚከበረውን የልጆች ደመራ ሲታደሙ የልጅነት ትዝታቸው ትውስ እያላቸው ከልጆች ጋር ተቀላቅለው እንደሚቦሩቁ ይናገራሉ።
አያይዘዉም፣ መስከረም 16 አባቶች ችቧቸውን ይዘው በቅድሚያ እየመሩ ባህሉን ጠብቀው ልጆች ከኋላ እየተከተሉ የሚከበረውን ደመራ ለመታደምም መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።

የመስቀል በዓል በጉራጌ አካባቢዎች ለአስር ቀናት ይከበራል የሚሉት ሰለሞን፣ የዘንድሮውን በዓል ከቤተሰብ ጋር ቆይታ በማድረግ ለአንድ ሳምንት ያህል አክብረው ወደ ሥራ ቦታቸው እንደሚመለሱ ይናገራሉ።
የመስቀል በዓል በአገራችን ከሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ችቦ ለኩሰው ደመራ በመደመር በዓሉን በደማቅ ሁኔታ ያከብሩታል።
ለአብነት ያህልም መዲናችንን መጥቀስ ይቻላል። በመዲናችን ውስጥ የከተሙ ሰዎች ከሊቅ እስከ ደቂቅ በመሰባሰብ በየዓመቱ መስቀል አደባባይ ላይ በደማቅ ሁኔታ ማክበር ከጀመሩ ዘመናት ተሸኝተዋል።

በዓሉን በከተማዋ የከተሙ ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች ተሰባስበው ሲያከብሩ እንደነበርም ይነገራል። ከዘመናት በፊት በአራዳ ጊዮርጊስ ይከበር የነበረው በዓል፣ የደርግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን፣ ቀጥሎም ስሙ አብዮት አደባባይ ተብሎ በተሰየመው ጎዳና ላይ ሲከበር እንደቆየ እና ከ1982 ጀምሮ እስካሁን ድረስ በዛው መስቀል አደባባይ ተብሎ በተሰየመው ቀደመት ቦታው ላይ በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር የታሪክ መምህሩ አልማው ክፍሌ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሰዎች ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በመጉረፍ እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ወደሚገኝበት ቦታ የአንባሰል ተራሮችን ተሹሎኩልከው በተፈጥሮ በመስቀል አምሳል በታነጸውና በተዋበው ግሸን ደብረ ከርቤ ተራራ ላይ በዓሉን ያከብራሉ።
የመስቀል በዓል በእነዚህ አካባቢዎች ብቻም ሳይሆን በአገሪቱ የደቡብ ክፍል በተለይም በጉራጌ፣ በሲዳማ፣ በወላይታ፣ በሐድያና በከምባታ አካባቢዎች ሰፋ ያለ ድግስ ተደግሶ፣ ከሩቅ ያለው ሰው ተሰብስቦ፣ በየሰፈሩ ደመራ በመደመር ለአስር ቀናት በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር የአካባቢው ተወላጆች ይናገራሉ።

ዓመቱን ጠብቆ የሚከበረው የመስቀል በዓል ከ2ሺሕ ዘመናት በፊት እየሱስ ክርስቶስ ተቸንክሮበት የነበረው መስቀል ከተቀበረበት ቦታ ንግስት ኢሌኒ አስቆፍራ መስከረም 16 እንዳስወጣችውና በተፈጥሮ የመስቀል ቅርጽን በተላበሰው በሰሜን ወሎ አካባቢ በሚገኘው ግሸን ደብረ ከርቤ ተራራ ላይ መቀመጡ የሚታወስበት በዓል እንደሆነም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክረስትያን ዘንድ ይነገራል።

ኹሉም በአገሪቱ ያሉ በበዓሉ የሚሳተፉ ሰዎች ደመራ ደምሮ በመለኮስ በዓሉን ማክበራቸው የሚያመሳስላቸው ቢሆንም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ለየት ባለና ልማዳዊ ባህልን በተከተለ መልኩ ሲከበር ይስተዋላል።

በተለይም በጉራጌ አካባቢ ሻኛው ሞላ ያለ ፍሪዳ አርዶ ሰፋ ያለ ድግስ በመደገስ፣ ኹለት ጊዜ ደመራ በመለኮስ፣ እንዲሁም ከመስከረም 13 እሰከ 17 ያሉትን ቀናት በባህል (መስከረም 13 ወሬት ያህናን የበዓል መክፈቻ፣ መስከረም 14 የዕርድ ዋዜማ የእንፋሎት ቆጮ፣ አይቤና ጎመን የሚቀርብበት ቀን፣ መስከረም 15 ወኅሚያ ዕርድ የሚጸምበት ዋነኛው የጉራጌ የመስቀል በዓል፣መስከረም 16 ምግይር ወይም የአባቶች ደመራ) በመከፋፈል በዓሉን በተለየ የባህል ነጸብራቅ ማክበር ከተጀመረ ዘመናትን እንዳስቆጠረ ይነገራል።

በጉራጌ አካባቢ በዓሉ ከኃይማኖታዊ እሳቤ በተጨማሪ በባህላዊ መንገድም ይከበራል የሚሉት የታሪክ መምህሩ አልማው ክፍሌ (ዶ/ር) እሸቱ፣ አገዳው ቀርቦ፣ በሬው ታርዶ፣ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወጣቶችን በምረቃ በመባረክ “አዲስ እህል አየን፤ አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ተተካ” በማለት የዘመን መለወጫ በዓልን የሚከበርበት ዕለት መሆኑንም ገልጸዋል።

አክለውም፣ በአንድም ሆነ በሌላም ምክንያት ከተወለዱበት አካባቢ ርቀዉ የሚኖሩ ልጆች በዚህ ዕለት በቦታው ካልተገኙ በወላጆቻቸው ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለውና “ወልጀ እንደመካን ተቆጠርኩ፤ ልጀ በመቅረቱ አዋረደኝ፤ ከሰው በታች አደረገኝ፤ ረግሜዋለሁ” የሚል ባህል እንዳላቸው ነው የገለጹት።

በዚህም መሰረት የጉራጌ ተወላጆች የመስቀልን በዓል ለማክበር ከመስከረም 12 ጀምረው ያጠራቀሙትን ብር ይዘው፣ እንዲሁም ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ገዝተው ከተለያዩ ቦታዎች ወደየትውልድ ቄያቸው ይተማሉ ነው ያሉት።
ብርሃኑ ደስታ የተባለው የጉራጌ ተወላጅ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ፣ የአካባቢው ተወላጆች የመስቀልን በዓል ለማክበር ዓመቱን ሙሉ ዕቁብ በመጣልና ባንክ ቤት በማስገባት ለበሬ መግዣ የሚሆን ብር የሚቆጥቡ ሲሆን፣ ሴቶችም በበኩላቸው በዓሉ ከመድረሱ ኹለት ወር ቀድመው ቆጮ፣ ማር፣ ቅቤ፣ እርጎ አዘጋጅተው እንደሚጠብቁ ይናገራል።

በቤተ ጉራጌ የመስቀል በዓል የአንድ ቀን ሳይሆን የአስር ቀናት በዓል ነው የሚለው ብርሃኑ፣ ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ እስከ አስረኛው ቀን ድረስ በእናቶች ሰፊ መዳፍ የተዘጋጀውን የተለያየ የምግብ አይነት “ልዩ ጣዕም ካለው” የጉራጌ ክትፎ ጋር የቤተሰብ አባላቱ ተሰባስቦ እየተመገበ እና እየቦረቀ እንደሚቆይ ነው ለአዲስ ማለዳ ያስረዳው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ምንም እንኳን አገራችን ኢትዮጵያ ለምታከበራቸው በርካታ በዓላት የራሷ የሆነ ምስጢርን የተላበሰ ምክንያታዊነት ያላት ቢሆንም፣ ልማዳዊ ድርጊትን መሠረት በማድረግ ለተለያዩ በዓላት የተንዛዛ ድግስን በመደገስ ለኢኮኖሚ መሽቆልቆል ትዳረጋለች የሚሉ ሰዎችም አልጠፉም።

“በዓሎቻችን ሁሉ የብክነት በዓል ናቸው” የሚሉት አልማው ክፍሌ (ዶ/ር) ከሰሜን እስከ ደቡብ የሚገኘው ሕዝብ የተንዛዛ ድግስን በመደገስ አላስፈላጊ ለሆነ ወጭ እንደሚዳረግ ነው የገለጹት።
እንደ መምህሩ አነጋገር ከሆነ፣ በአጠቃላይ የአገሪቱን ዜጎች ስንመለከት ገበሬው ያመረተውን ከመስከረም እስከ ጥር ከልክ በላይ ጠጥቶ በመስከር፣ የተንዛዛ ሰርግ በመደገስና በዓላትን በመንተራስ ሲያባክን ይቆይና ከጥር ጀምሮ እስከ መስከረም ድረስ ለምግብ ፍጆታ ዕጥረት ሲዳረግ ይስተዋላል።

ገበሬው ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ ትምህርትን ተምሮ የባህሪ ለውጥን አምጥቷል ተብሎ የሚታመነው የመንግሥት ሠራተኛ፣ ምሁራንን ጨምሮ በወር ደሞዝ የሚተዳደረው የማኅበረሰብ ክፍል ወር በገባ በ15 ቀን ውስጥ ብሩን በመጨረስ ከ15 እሰከ 30 ያሉትን የወሩን ቀናት “ዘመነ ሰቆቃ ላይ ነን” ሲል ይደመጣል በማለት ነው አልማው የተናገሩት።

በተለይም በጉራጌ አካባቢ የመስቀልን በዓል ለማክበር በአንድ ቤተሰብ ውስጥ በየዓመቱ አንድ በሬ ይታረዳል የሚሉት መምህሩ፣ በየዓመቱ ለሠንጋ ብዙ ብር ወጭ ስለሚደረግ የበሬዎች ዋጋ በዕጥፍ ይጨምራል። 10ሺሕ የሚሸጠው በሬ 60ሺሕ ሲሸጥ አይቻለሁ በማለት ነው የአይን ዕማኝነታቸውን የገለጹት።

አክለውም፣ በዓላት ቀድሞ የተከወኑ የተለያዩ ታሪኮችን የምናስብበት እንጅ ግዴታ ዓመቱን ጠብቀን ለብክነት የምንዳረግበት ጊዜ መሆን የለበትም። ደመራውን ለኩሰን ለአንድ ቀን በሚሆን ቀለል ያለ ዝግጅት የመስቀልን በዓል አክብረን 60ሺሕ ብር የተገዛውን በሬ ብናርስበት በዓሉንም አክብረን በበሬውም እጥፍ ግብዓትን አግኝተን “ከዘመነ ሰቆቃ ችግር” መውጣት እንችላለን በማለት ነው አስተያየታቸውን ያስቀመጡት።

“ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት እንጅ ጎጅ ባህል የለም፤ በመሆኑም የባህል ለውጥ ያስፈልጋል፤ በኹሉም የአገሪቱ ቦታዎች ብክነትን መሰረት ያደረገ ባህል ለኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል” የሚሉት ዶ/ር አልማው፣ በተለይም አሁን ላይ አገራችን በጦርነት የኢኮኖሚ ውድመት የተጋረጠባት ወቅት በመሆኑ የተንዛዛ ድግስን ቀንሶ ለመሠረተ ልማት መትጋት ያስፈልጋል በማለት ነው ምክራቸውን የለገሱት።

የታሪክ መምህሩ አሁን ካለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር አያይዘው የመስቀልን በዓል በሚከበርበት ወቅት ሕዝቡ መሰባሰቡን እንደ ሌላ ዓላማ በመጠቀምና የበዓሉን መታሰቢያነት ለማጠልሸት የሚጥሩ አካላት ስለማይጠፉ፣ በተለይም በዚህ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የመስቀል በዓል በዩኔስኮ የተመዘገበ የዓለም ሁሉ ቅርስ ሆኗል የሚሉት ዶ/ር አልማው፣ ይህን ቅርስ ለማጠልሽት ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ኃይሎች በየአካባቢው መቀመጣቸውን የጠቆሙ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በተረጋጋ መልኩ ዜጎችን ሊያስተዳድር አይችልም ብሎ ለማስመስከር ሕዝብ የሚሰበሰብበትን አካባቢ በመጠቀም ችግር ሊያደርሱ ስለሚችሉ እያንዳንዱ ሰው አብዝቶ ሊጠነቀቅ ይገባል ብለዋል።

ዕድገቷን ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ መዲናዋ አቅንተው በተለያዩ ሥራዎች በተለይም በንግድ የሥራ ዘርፍ የተሠማሩ ግለሰቦች በዓሉን ለማክበር ወደ ጉራጌ አካባቢ ስለሚተሙ፣ ይህን ተከትሎም በበዓሉ ሰሞን የንግድ እንቅስቃሴው ሲቀዘቅዝ ይስተዋላል።
በጉራጌ አካባቢዎች ለበዓሉ የተዘጋጁ ድግሶች እስከሚያልቁ ከመጠበቅ ይልቅ፣ ምንም እንኳን ቤተሰብ ጋር ከተገናኙ ቶሎ መለያየት ቢከብድም፣ ሥራን ግምት ውስጥ በማስገባት በፍጥነት መመለሱ ለግለሰቡ፣ ለማኅበረሰቡና ለአገሪቱ ትንሽ የማይባል ኢኮኖሚያዊ ሚና ይጫወታል ነው የተባለው።

ከዚህም በተጨማሪ አዲስ ማለዳ በበዓላጽ አማካኝነት የሚባክነውን ኢኮኖሚ በማስመልከት ከኢኮኖሚስት አማካሪው ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ ሐሳባቸውንም እንደሚከተለው አብራርተዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች የመስቀልን በዓል ለማክበር ድግስ መደገስ ባህላቸው ስለሚፈቅድ፣ ደመራቸውን ከለኮሱ በኋላ አርደው፣ እሸት አገዳ ቆርጠው እና እንደየአካባቢው ልማድ የተለያዩ ዝግጅቶችን አዘጋጅተው በአካባቢ ደረጃ እንደሚሰባሰቡ የገለጹት ደምስ፣ ድግስ መደገሱና ተሰባስቦ በፍቅር በአንድነት መመገቡ ከልክ ያለፈ እንዳይሆን ታቅዶበት የሚደረግ ከሆነ፣ ሥራ መሥራት የሚያስፈልገው ፍላጎቶችን ለማሟላት እስከሆነ ድረስ በኢኮኖሚ ላይ የከፋ ችግር አያስከትልም ነው ያሉት።

አክለውም፣ ለመስቀል በዓል ብቻ ሳይሆን ጥምቀት፣ ዘመን መለወጫ፣ ሰርግ እና ሌሎች በዓላትን ለማክበር ግዴታ ሰንጋ አርዶ ከዕቅድ ዉጭ በሆነ መልኩ የተንዛዛ ድግስ መደገሱ ግን ለኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ምክንያት መሆኑ አያጠራጥርም ሲሉ ነው የገለጹት።
የትኛውም ባህል እስከዛሬ የቆየበት እርግማኑንም ቡራኬውንም፣ አደርግ አታድርግ የሚለውን አካሄድ ይዞ የሚጓዝ የአንድ ማህበረሰብ መገለጫ በመሆኑ በልኩ ማድረጉ ጠቃሚ ነው።
በዓላትን ተንተርሰን የተንዛዛ ድግስ ከመደገስ ባሻገርም፣ የሰዎች የመግዛት ፍላጎት የሚጨምርበት ወቅት ነው የሚሉት ደምስ፣ በልክና በሥርዓቱ ከተከወነ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ይጠቅማል ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com