የእለት ዜና

በተፈናቃይ ሥራ ፈላጊ ሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ትንኮሳ

ዳሳሽ ሞላ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ 04 ቀበሌ ልዩ ስሟ ወፍጭና ተብላ በምትጠራው ቦታ ነው። ዳሳሽ ትምህርቷን እስከ ስምንተኛ ክፍል ብትከታተልም፣ በአቅም ማነስ ምክንያት ትምህርቱን ጫፍ ማድረስ ባለመቻሏ ባለሃብቶች ቤት ዘንድ ተቀጥራ በመሥራት ነው ሕይወቷን የምትመራው።

ከኹለት ወር በፊት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ባካሄደው ጥቃት ወደ አዲስ አበባ የመጣቸው ዳሳሽ ሞላ፣ ሕይወቷን የምትመራው በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ አንድ ባለሃብት ቤት ተቀጥራ መሆኑን ትገልጻለች።
በጦርነቱ ውስጥ ያሉት የቤተሰቦቿ ነገር ሁሌም ቢያሳስባትም፣ ተፈናቅላ እንደመምጣቷ ሥራ ማግኘቷ ደግሞ በትንሹም ቢሆን እፎይታን ሰጥቷታል። ከዕለታት በአንደኛው ቀን ትሠራበት ከነበረው ቤት እንድትወጣ ቀጣሪዋ ድንገት አርድታት ነበር። ቀጣሪዋ ከቤት ያስወጣቻት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ገደማ ስለነበር አልጋ ይዛ ብታድርም፣ በማግስቱ ቀጥታ ሥራ ወደ ማፈላለግ ነበር ያመራችው። በዚህ አጭር ጊዜ ቢያንስ ሦስት ቤቶችን በተለያየ ምክንያት ረግጣለች።

በዚህ መንገድ ሕይወትን የምትመራው ወጣቷ፣ አንዳንዶቹ ቀጣሪዎቿ ከልጆቻቸው ባልተናነሰ የሚለግሷት ክብር እና የእናት አባት ዓይነት እንክብካቤ “ለካስ መወለድ ቋንቋ ነው” እንድትል ይጋብዛታል።
ሌላኛዎቹ ቀጣሪዎች ደግሞ ሥራ ከማብዛት ባሻገር፣ ሰብዓዊነትን ረስተው የድካሟን ደሞዝ ይነፍጓትና ሕይወትን እንድታማርር እንደሚያደርጓት ታወሳለች።

ከምትሠራበት ቦታ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትወጣ ምንም ብር ስላልነበራት በፍጥነት ሥራ ማፈላለግ እንዳለባት ተገንዝባ ነበር። ቀድሞ ሥራ ወዳገኘላት ደላላ በመደወል ሥራ እንዲፈልግላት ስታሳስበው ሥራ እንዳለና በሰዓቱ መምጠት እንደምትችል ይነግራታል።
ደላላው ጋር ከተገናኙ በኋላ ግን ነገሮች በተቃራኒው እንደጠበቋት ትናገራለች። አዲሱ ገበያ በሚባለው አካባቢ ቀጥሯት ያገኘችው ደላላ፣ ካገኘችው በኋላ የሚሄደበትን መንገድ አራዘመባት። “ወዴት ነው አንደርስም እንዴ?’’ ብትለውም፣ “ደርሰናል ትንሽ እያለ’’ ብዙ መተጣጠፊያ መንገዶችን በመሹለክልክ ለረጂም ሰዓት እንደተጓዙ ትናገራለች።

በሥራ ሲባዝን የዋለው ሰው ሁሉ ወደ ቤቱ በመግባት ጭር ያለው አካባቢ እና በከዋክብትና ጨረቃ ታጅቦ ፀጥ እረጭ ያለው ምሽት ለዳሳሽ ፍርሃትን አሳድሮባት ነበር።
ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በዳስሽ አስተሳሰብ ሥራ ወደምትገባበት ቤት ደረሱ። ደላላው ግን ቀድሞ ወደ አመቻቸው አልጋ ነበር የወሰዳት። ለመግባት ፍቃደኛ ባትሆንም፣ እጇን ጥብቅ አድርጎ ይዞ እቤት ካስገባት በኋላ ወደ አልጋው እያመራ፣ “በእኔና አንቺ ብቻ አልተጀመረም፤ ምን ችግር አለው?’’ በማለት ወሲብ እንዲፈጽሙ ለማድረግ እንደገፋፋት ትናገራለች።

በሁኔታው ከመገረምም አልፎ ሐፍረት ተሰማኝ የምትለው ዳሳሽ ሞላ፣ “እና ሌሎች ገደል የገቡ እንደሆን እኔም ገደል መግባት አለብኝ! የት ታውቀኛለህ? የትስ አውቅሃለሁ?’’ በሚል ጩኸትና መኮሳተር ለብዙ ሰዓት ትሞግት ነበር። ቢሆንም ግን “ታዲያ ምን ችግር አለ ከዚህ በኋላ መተዋወቅ እንችል የለ እንደ’’ በማለት ሊያታልላት ቢሞክርም፣ ከክፍሉ እንዲወጣ በመማጸን እንዲወጣ ካደረገች በኋላ በሯን ዘጋች።

ይህ በእንዲህ እያለ ተስፋ ያልቆረጠው ደላላ፣ ይባስ ብሎ በድጋሚ በሯን ከመቆርቆር አልቦዘነም። እሷም እስኪነጋ ድረስ በሯን ሳትከፍት ነበር የቆየችው። ከተለመደው በተለየ መልኩ የረዘመ የመስላት ሌሊት ነግቶ ከክፍሉ ስትወጣም፣ ሥራ አገናኙ ደላላ አሁንም በቀላሉ ሊለቃት አልፈቀደም።

አብራት የነበረች ሌላኛዋን ጓደኛዋን ቀደም ብሎ ወደ ሥራ ቢያስገትም፣ እሷን ግን ሊጫወትባት እንደፈለገ ትናገራለች። ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ አብራቸው እንድትጠጣ ጥያቄ ሲያቀርቡላት ወደ ማደሪያዋ መሄድ እንደምትፈልግ ብትነግራቸውም ሊሰሟት አልቻሉም። የምትቀጥራት ሰው እየመጣች እንደሆነና መጠበቅ እንዳለባት ተነግሯት ብትጠብቅም የመጣ ሰው ስላልነበረ ዓላማቸው ሌላ መሆኑን የተረዳችው ዳሳሽ፣ ከእነርሱ የምታመልጥበትን መንገድ ዘየደች።

ከትንሽ ቆይታ በኋላ ሽንት ቤት ልጠቀም በሚል ሰበብ ካለችበት ችግር ሊያወጧት የሚችሉ ሌሎች ሰዎችን ማግኘት እንዳለባት ወሰነች። ውሳኔዋንም ወደ ተግባር ቀየረችው። በሆቴሉ ውስጥ ከሚተራመሱት ግለሰቦች አንድኛቸውን በመጠጋት “በእናታችሁ እርዱኝና ልዉጣ?’’ በማለት ያለችበትን ሁኔታ ስትነግራቸው፣ ችግሯን የተረዱ ሰዎች ባደረጉላት ትብብር ከነበረችበት ሁኔታ በብዙ መከራ አምልጣ እንደወጣች ትናገራለች ።

በአገናኝ ኤጀንሲዎች አማካይነት “ሥራ መፈለግ በጣም ከባድ ነው’’ የምትለው ዳሳሽ፣ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ ደላላዎቹ ሥራ የሚያስገቧቸው በሐሰተኛ ደሞዝ የሚሆንበት አጋጣሚ ስላለ ይከፈላችኋል የተባለውን ብር እንደማያገኙ ታብራራለች።
ዳሳሽ ሞላ በሕይወቷ ውስጥ በገጠማት ችግር አምርራ እንደምታለቅስ የገለጸች ሲሆን፣ የሠራተኞች መብት እንደማንኛውም ሰው ሊከበር እንደሚገባ አሳስባለች። አያይዛም በስራ አፈላላጊዎች አማካኝነት በሚፈጸመው ጾታዊ ትንኮሳ ከሚከሰተው የሥነ-ልቦና ድቀት በተጨማሪ፣ ብዙ ሴቶች ያለ ዕቅድ ወልደው ጎዳና ላይ እንደወደቁ ጠቁማለች። ሥራ ፈላጊ ሴቶችም ሥራ ሲያፈላልጉ ጥብቅ ጥንቃቄ ማድረግ እንደለባቸው ነው ምክሯን የለገሰችው።
በአገራችን የተለያዩ ቦታዎች በተለይም በገጠሩ አካባቢ የተወለዱ ሴቶች በየጊዜው ወደ ተለያዩ ትላልቅ ከተሞች ሥራ ፍለጋ ሲሰደዱ ይስተዋላል።

በአገራችን ሥራ አጥነት እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ ሥራ የማግኘት ዕድል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ እንደመጣ በብዙዎች ዘንድ መነገር ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። በዚህም ምክንያት እንኳን ተምረው ለመመረቅ ያልበቁት ይቅርና የዩኒቨርስቲ ዲግሪ ያላቸው ወደ ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሚመላለሱና የሥራ ማስታወቂያ ወደ ተለጠፉባቸው ሰሌዳዎች በየዕለቱ የሚመላለሱ ዜጎች ምስክር ናቸው።

በመሆኑም፣ ከገጠሩ አካባቢ ወደ ከተማ ለሥራ የሚመጡ ሴቶች ወደ ከተማዋ ከማቅናታቸው በፊት ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ስለሚመስላቸው፣ ከመጡ በኋላ ነገሮች ባልጠበቁት መልኩ ይመሰቃቀሉባቸዋል። ከከተማ ውስብስብነት በተጨማሪ በፍጥነት ሥራ የማግኘት ችግርና ለጊዜው ማሪፊያ የሚሆን የቦታና የገንዘብ ዕጥረት እንደሚገጥማቸው ሴቶቹ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ።

ይህን ተከትሎም ወደ ከተማ የመጡበትን ዓላማ ከጫፍ ለማድረስ ወደ ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች በማምራት ሥራ ማፈላለጉን እንደ ዋነኛ አማራጭ ይጠቀሙበታል።
ለከተማዋ አዲስ የሆኑት ሴቶች ይቅርና ትምህርታቸውን ጨርሰው ሥራ በማፈላለግ መዲናዋን ከጫፍ እስከ ጫፍ እናውቃታለን ለሚሉት ሰዎች እንኳን፣ በአገናኝ ኤጀንሲዎቹ የገንዘብ፣ የጉልበትና የጊዜ ኪሳራ እንደሚገጥማቸው ይናገራሉ።

በተለይም ከገጠሩ አካባቢ ወደ ከተማ የሚያቀኑ ሴቶች በተደጋጋሚ ጾታዊ ትንኮሳ እየገጠማቸው መሆኑንም ይናገራሉ። በተለይም በተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በሰሜን ወሎ አካባቢዎች በሰነዝረው ጥቃት ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ወደ መዲናዋ የመጡና ሥራ የሚፈልጉ ሴቶች፣ በጦርነቱ ምክንያት ባዶ እጃቸውን ከቀያቸው መውጣታቸውን ተከትሎ፣ ሥራ ለማግኘት ከኤጀነሲዎች ጋር በሚያደርጉት ቅርርብ ጾታዊ ትንኮሳ እየደረሰባቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

ለጾታዊ ትንኮሳው መከሰትም እንደምክንያት ከሚመዟቸው ችግሮች መካከል፣ ለጊዜው ማረፊያ ቤተሰብ ማጣት፣ የአልጋ ውድነትን ተከትሎ በሚያጋጥማቸው የብር ዕጥረት ከሥራ አገናኝ ግለሰቦች ጋር የሚኖራቸው አላስፈላጊ ቅርርብ፣ ሥራ እስከሚያገኙላቸው ከእነርሱ ጋር መሆን እንደሚችሉ የሚያቀርቡላቸው መልካም የሚመስል አጋጣሚ እና፣ ’’ሥራ አለ’’ ብለው በደካማ ጎናቸው በመግባት ለፆታዊ ትንኮሳው የሚዳርጓቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ይጠቁማሉ።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ካነጋገረቻቸው ስዎች መካከል ትዕግስት አለሙ የተባለችው ወጣት በሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች የደረሰባትን ፆታዊ ትንኮሳ እንደሚከተለው ገልጻለች፤ በጦርነቱ ምክንያት በሰሜን ወሎ ዞን ከምትገኘው መርሳ ከተማ ተፈናቅየ ነው የመጣሁት የምትለው ትዕግስት፣ ወደ አዲስ አበባ መጥታ በግሏ ሥራ ብታፈላልግም በቀላሉ ማግኘት ስላልቻለች ወደ ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች ስልክ ደዉላ ነበር። ከቀናት ቆይታ በኋላ ሥራ እንደተገኘላት ተደውሎላት ወደ ኤጀንሲው ስትሄድ፣ ወደ ቀጣሪዎቹ ከመላኳ በፊት ሰውየው፣ “ሰዎቹ እስከሚመጡ ምሳ ልጋብዝሽ’’ ብሎ ወደ ቤቱ ይዟት እንደገባና ከምሳ በኋላ ቤቱን በመዝጋት በሚያሳቅቅ መልኩ ሊተሸሻት እንደሞከረ ነው የገለጸቸው።

ባልጠበቀችው ክስተት የተደናገጠችው ትዕግስት፣ በመሸነፍ ስሜት ውስጥ ሆና ጩኽት በማሰማት እንዲለቃት ብትሞክርም፣ ሊያፍናት እንደሞከረና “አፍነህ ብትገድለኝ ይሻለኛል’’ ብላ በመጽናቷ ከችግሩ ለማምለጥ መቻሏን ነው የገለጸችው። በጊዜው ግለሰቡ ጾታን አስመልክቶ የሰነዘረው “የማንቋሽሽ ቃል” አእምሮዋን እንደጎዳውና በሴትነቷ እንድታዝን እንዳደረጋት ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጸችው።

ትዕግስት እንደተናገረችው ከሆነ፣ “ሴት በመሆናችን ብቻ ያለ ፍላጎታችን ልንገደድ አይገባም። ሥራ ማገናኘቱ መልካም ቢሆንም፤ በመጠጥና በሱስ ሕይወታቸውን አበላሽተው የሌሎችን ሕይወት የሚያበላሹ ደላላዎችን የሚመለከተው አካል ሊከታተላቸው ይገባል።”
ሌላኛዋ ስሟ እናዳይጠቀስ የፈለገችው ግለሰብም፣ “በኤጀንሲዎች የሚደርስብን ችግር ይህ ብቻ አይደለም። ብር ከተቀበሉ በኋላ ሥራውን በማጓተት ብሩን በልተውት የሚቀሩ ደላሎችም አሉ። እኛም እኮ ቤተሰብ ነበረን፤ ከክፉው ዘመን ስለደረስን ለምን በሰላም ትኖራላችሁ ተብለን ከቄያችን ተፈናቅልን ነው እንጂ’’ በማለት ነው የተናገረችው።

አዲስ ማለዳ ጾታዊ ትንኮሳ የሚደርስባቸው ሴቶች ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት ለመውጣት ምን ማድረግ አለባቸው በማለት ከሥነ-ልቦና ባለሙያው ሙዘየን ጀማል ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፤ ባለሙያው ጾታዊ ትንኮሳ በሴቶች ላይ አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊና ማኅበራዊ ጉዳት እንደሚያደርስባቸው በመግለጽ መፍትሄዎቹንም አስቀምጠዋል።

ለአንድ ቦታ አዲስ የሆኑ ሰዎች በአካባቢው የሚያጋጥማቸውን ችግር ማወቅ ስለሚከብዳቸው ሴቶች በሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች ብዙ ጊዜ ጾታዊ ትንኮሳ ሲገጥማቸው ይስተዋላል የሚሉት ሙዘየን፤ ቀጣሪዎቹ “በብሬ ነው የማሠራው’’ በሚል አስተሳሰብ የሚያደርሱት የጉልበት ብዝበዛ፣ በደላላዎቹ ችግር አማካይነት ደሞዝ አለማግኘት እና መፈናቀል በራሱ ከጾታዊ ትንኮሳው ላይ ሲጨመር ለጭንቀት በመዳረግ እራስን እስከማሳት ድረስ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልም ነው ያብራሩት።

የሥነ-ልቦና ባለሙያው እንደተናገሩት ከሆነ፣ የጾታዊ ትንኮሳ ሲደርስባቸው ለጊዜው ካሉበት ቁጭት መውጫ መፍትሄ መስሏቸው፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ሽሻ መሳብና የአልኮል መጠጥ ወደመጠቀም ሲሄዱና በቀላሉ ወደማይወጡበት አጉል ሱስ ሲገቡም ይስተዋላሉ። ይህ አካሄድ እንኳን መፍትሄ ሊሆን ለዕለቱ መልካም ቢመስልም ከጊዜ በኋላ በአእምሮ ላይ ተደራራቢ ተጽዕኖ በማሳደር መጀመሪያ የተከሰተውን ትንሹን ችግር አግዝፎ ሕይወትን ያበላሻል ብለዋል።

ሙዘየን ችግሩ እንዳይደርስ መጠንቀቁ አማራጭ የሌለው ምርጫ መሆንን የጠቆሙ ሲሆን፣ ችግሩ ከደረሰ በኋላ ሥር ከመስደዱና ከሰደደ በኋላ ከጉዳቱ ለመውጣት ምን መደረግ እንዳለበት አመላክተዋል።
ጾታዊ ትንኮሳ የደረሰባቸው ሴቶች አቅም እንደሌላቸው በማሰብ፣ “እኔ ማንም የሚረዳኝ የለም፤ ማንም አይደለሁም፤ የተዋረደኩ ነኝ’’ በሚል አስተሳሰብ አእምሯቸውን ስለሚያጨናንቁት፣ ጉዳዩ በተደጋጋሚ ከመታሰቡ በፊት፣ አንደኛ ከሐሳቡ ወጥተው ዘና የሚሉበትን ቦታ ማመቻቸት፡ ኹለተኛ ጉዳት ያደረሰውን አካል በሕግ መጠየቅ፤ ሦስተኛ ያጡትን ነገር እንዲያገኙ ማገዝ (ለምሳሌ የወር ደሞዝን) እና የሥነ-ልቦና ምክር እንዲያገኙ ማድረግ ቀላል የማይባል መፍትሄ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ጾታዊ ትንኮሳውን ያደረሰው አካል በህግ መቀጣቱ በገፈት ቀማሾቹ አእምሮ “ማንም የለኝ፤ አቅምም የለኝ’’ በማለት የሚመላለሰውን ጭንቀት ያቃልላል ሲሉ ነው የገለጹት።

አክለውም፣ በወቅቱ ክትትል ሳይደረግ ቀርቶ ሕመሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ “አእምሮ ሕመምተኛ የሆነ ሰው እኮ አይድንም’’ ከሚል ከተለመደ አባባል በመራቅ፣ ከላይ ከዘረዘርናቸው መፍትሄዎች ወደ መድኃኒት መጠቀም በመሸጋገር እንደማንኛውም ሰው ጤነኛ ሆኖ መኖር እንደሚቻል ነው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ምክራቸውን የለገሱን።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com