የእለት ዜና

ብልጽግና ፓርቲ ብቻውን የሚወዳደርበት የሱማሌ ክልል ምርጫ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫን ሰኔ 14/2013 ያስፈጸመ ሲሆን፣ ከጸጥታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የተነሳ ሰኔ ላይ ምርጫ ባልተካሄደባቸው ቦታዎች ኹለተኛወ ዙር ምርጫ ለመስከረም 20/2014 ቀጠሮ ተይዞለታል።
በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሙሉ በሙሉ ካልተካታቱ ክልሎች መካከል የሱማሌ ክልል አንዱ ሲሆን፣ በክልሉ የመራጮች ምዝገባ ተደርጎ በአሁኑ ሰዓት የሚወዳደረው የፖለቲካ ፓርቲ ብልጽግና ብቻ መሆኑን የክልሉ የኮሚኒኬሽን ምክትል ቢሮ ሀላፊ መሐመድ ሮብሌ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ባለሳለፍነው ሰኔ በተካሄደው ስደስተኛውን አገራዊ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ያልተካተቱ እና በከፊል ምርጫ የተካሄደባቸው ክልሎች አሉ። ሙሉ በሙሉ ምርጫ ያልተደረገባቸው የሱማሌ፣ ትግራይ እና ሐረሪ ክልሎች ሲሆኑ፣ በከፊል ምርጫ ከተካሄደባቸው ክልሎች መካከል አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና ደቡብ ክልል ይገኙበታል። በከፊል ምርጫ ከተደረገባቸው ክልሎች መካከል ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አንዱ ሲሆን፣ በክልሉ ካሉት ሦስት ዞኖች ምርጫ የተካሄደው በአንዱ መሆኑ የሚታወስ ነው።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምርጫ ያልተደረገባቸው ኹለት ዞኖች መተከልና ካማሺ ዞኖች ሲሆኑ፣ በዞኖች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማካሄድ አልችልም በማለቱ እንደሆነ የሚታወስ ነው። በክልሎች የተወሰኑ አካባቢዎች ምርጫ ሳይከናወን የቀረው በነበረው የጸጥታ ችግር እና ድምጽ መስጫ ወረቀት ኅትመት ላይ ባጋጠመ ችግር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጹ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦረድ መስከረም 20/2014 በሐረሪ፣ በሱማሌ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ለሚያካሂደው ምርጫና ሕዝበ ውሳኔ የተመዘገቡ መራጮች አጠቃላይ ቁጥር 7.6 ሚሊዮን ሲሆን፣ በድሬደዋ 1841፣ ሐረሪ 135 ሺሕ፣ ሱማሌ 5.1 ሚሊዮን፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች 2.3 ሚሊዮን፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ምርጫ እና ሕዝበ ውሳኔ 527 ሺሕ መራጮች ይሳተፋሉ ሲል ቦርዱ አስታውቋል።

እነዚህ ምርጫ የሚካሄድባቸው የምርጫ ክልሎች በ47 የተወካዮች ምክርቤት እና በክልል ምክርቤት ደግሞ 105 ናቸው። በአጠቃላይ 7054 የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ምርጫው ይካሄዳል ተብሏል።
ቦርዱ ምርጫውን በአንድ ጊዜ ማካሄድ እንደማይችል መወሰኑን ተከትሎ፣ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በኹለት ዙር ያካሄዳል። የቦርዱ የኹለተኛውን ዙር የቅድመ ምርጫ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሰኔ 14/2013 ያካሄደው ምርጫ ቦርድ፣ ቀደም ሲል ኹለተኛው ዙር ምርጫ ደግሞ ለጳጉሜን 1/2013 ያሳለፈ ቢሆንም፣ የቅድመ ምርጫ ዝግጅቱ በታቀደው ልክ ባለመጠናቀቁ ኹለተኛው ዙር ምርጫ መስከረም 20/2014 እንዲካሄድ ቦርዱ መግለጹ ይታወሳል።

በዚህ ኹለተኛው ዙር ምርጫ በሱማሌ ክልል ውስጥ ከሚወዳደሩ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ብልጽግና ብቻ የቀረ ሲሆን፣ በክልሉ በሚካሔደው ምርጫ ላለመሳተፍ የወሰኑት ፓርቲዎች ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ናቸው። ፓርቲዎቹ ከምርጫው ራሳቸውን ያገለሉት ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ ላቀረቧቸው አቤቱታዎች ምርጫ ቦርድ “ተገቢውን ምላሽ አልሰጠም” በሚል ነው።
አዲስ ማለዳ በምርጫው የማይሳተፉት ፓርቲዎችን ለማነጋገር የሞከረች ሲሆን፣ የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ የሚከተለውን ነግረውናል።

በኢትዮጵያ ስድስተኛው አገራዊ የምርጫ የክንውን ሒደት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያለምንም ማስፈራሪያ በነጻነት የመሳተፍ መብት እንዳላቸው እና ማንኛውም የምርጫ እንቅስቃሴ በምርጫ መርሆች እና በሕግ መመራት እንዳለበት ቢታወቅም፣ በክልሉ የሚታየው ግን ፍጹም ተቃራኒ ለአንድ ፓርቲ ብቻ ያደላ ነው ብለዋል።

ኢዜማ እና ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በጋራ በሰጡት አስተያየት ደግሞ፣ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ኹሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፈረሙት የጋራ ሥምምነት ላይ እና በምርጫው ሥነ-ምግባር ዐዋጅ መሠረት ተገቢውን የምርጫ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለባቸው በምርጫው ሥነ-ምግባር ዐዋጅ መረገጋገጡን አስታውሰዋል።

ነገር ግን፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ አመለካከታቸውን በሕጋዊ መንገድ ቅስቀሳ በማድረግ እና መራጮችም ሐሳባቸውን በነጻነት በመግለጽ መሳተፍ እንዲያስችላቸው የተሠራ ምንም አይነት ሥራ የለም ብለዋል።
በሱማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ ሒደት ችግር ያዘለ ከመሆኑም በላይ፣ የምርጫ ሥርዓት የጣሰ፣ የምርጫን ትርጉም በሚያሳጣ መንገድ ለአንድ ወገን ያዳላ ነው ሲሉ ኢዜማ እና ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አስታውቀዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ በፊት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረቧቸው ቅሬታዎች ሊፈቱ አለመቻላቸው በምርጫው ላይ ዕምነት እንዳይኖረን አድርጎናል ሲሉ ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል።

ኢዜማ እና ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ይፋ ባደረጉት መረጃ መሰረት፣ ከዚህ በፊት ተሰርቆ የነበረው የምርጫ ቁሳቁስ በአዲስ እንዲተካ መጠየቃቸውን አስታውሰው፣ አሁን ግን ቀድሞ ተዘርፎ በነበረው ካርድ ወደ ምርጫ በመገባቱ ምርጫው ታአማኒነት ይጎለዋል ብለዋል።
ፓርቲዎቹ የምርጫ ጣቢያ ያልተቋቋመባቸው አካባቢዎች ላይ ምርጫ ጣቢያ እንዲቋቋም የጠየቁ ሲሆን፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠው ምላሽ በቂ አይደለም ሲሉ አስታውቀዋል።

የምርጫ ቦርድ የተዋቀረበት መንገድ በየደረጃው ሳይሆን ከመንግሥት መዋቅር ጋር ነው ያሉት ራሳቸውን ያገለሉት ፓርቲዎቹ፣ የምርጫ ቁሳቁስ የዘረፉ የምርጫ አስፈጻሚዎች በሕግ አለመጠየቃቸው ምርጫው ፍትሃዊ እንዳይሆን ያደርገዋል ሲሉ ገልጸዋል።
በቦርዱ የቀረቡ የምርጫ ቁሳቁስ ድልድል ሒደት፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላና ሥልጠና ሒደት፣ እንዲሁም ስለመራጮች ምዝገባ ሒደትና የጊዜ ሰሌዳ ግልጽ መረጃ አለመቀመጡን አንስተዋል።

በቦርዱ በኩል የሠለጠኑ ሠልጣኞች ሳያውቁ የምርጫ ቁሳቁስና ሠነድ በወረዳና በቀበሌ የመንግሥት መዋቅር ሠራተኞች በኩል መከናወኑ ታማኝነት የጎደለው በመሆኑ መስከረም 20/2014 ከሚካሄደው ምርጫ ራሳቸውን አግልለዋል።
ቦርዱ በበኩሉ፣ የሚሠራጩ ቁሳቁሶች የጫኑ መኪኖች አዲስ አበባ ከሚገኘው የቦርዱ ጊዜያዊ መጋዘን መስከረም 11/2014 ወደየጫኑበት ምርጫ ክልል መጓዛቸውን የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ገልጸዋል።

ቦርዱ በራሱ ወጪ አምስት ሚሊዮን ብር በማውጣት የመራጮች ምዝገባ የተበላሸባቸውን ቦታዎች ያሰለጠናቸውን ባለሙያዊች በመላክ የማሻሻል ሥራ ተሰርቶ በድጋሚ እንዲመዘገቡ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፣ ይህንንም ሪፖርት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ልኬያለሁ ሲል አስታውቋል።
የመራጮች ምዝገባ በድጋሚ የተደረገው ከፖለቲካ ፓርቲዎች በቀረበ አቤቱታ ነው ተብሏል። ለአስፈጻሚዎች ሥልጠና በመስጠት በአስፈጻሚዎች በኩል ያለውን የግንዛቤ ዕጥረት በማስተካከል እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የመራጮች ምዝገባ ድጋሚ እንዲካሄድ ተደርጓል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች በቀረበው ጥያቄ መሠረት አንድ ሙሉ ክልል ድጋሚ የምዝገባ ሒደት እንዲከናወን ተጠይቆ ነበር፣ ነገር ግን ከሀብት (ሪሶርስ) ዕጥረት አንጻር ማድረግ አልተቻለም።

ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉ ፓርቲዎች ልክ ምርጫው ኹለት ሳምንት ሲቀረው መውጣታቸው ለመራጮች ያሳዩት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሲል ምርጫ ቦርድ ጠቅሷል። በጋራ ምክርቤቱ የምትስማሙበትን የምርጫ አስፈጻሚ እንዲሰጡን ብንጠይቃቸውም፣ የጋራ የሆነ የሚያስማማን የምርጫ አስፈጻሚ የለንም ሲሉ መልሰውልናል ብሏል ቦርዱ።

ከቀናት በኋላ በሦስት ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚከናወነው ምርጫ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩ ሲሆን፣ በሱማሌ ክልል ከሚካሄደው ምርጫ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን አግልለዋል።
ከእነዚህም አንዱ የሆነው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ራሱን ከምርጫው ያስወጣው በተለያዩ ምክንያቶች መሆኑን አስታውቋል። የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሠራር ጉድለት በመኖሩ እና እነዚህን ጉድለቶች እንዲያስተካክል ጠይቆ ለውጥ ባለመምጣቱ ነው ሲል ገልጿል።

በመጪው መስከረም 20 ምርጫ ከሚከናወንባቸው የፓርላማ መቀመጫዎች ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት በሱማሌ እና በደቡብ ክልል የሚገኙ ሲሆኑ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች ውስጥ ባለፈው ሰኔ 14 ምርጫ የተካሄደባቸው 436ቱ ላይ ብቻ ነው። በወቅቱ ሙሉ ለሙሉ ምርጫ ያልተካሄደበት የሱማሌ ክልል በፓርላማ 23 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ በመስከረም ሃያው ምርጫ በኹሉም ላይ ምርጫ ይደረጋል ሲሉ ሶልያና ገልጸዋል። ከእነዚህ የፓርላማ መቀመጫዎች በተጨማሪ ለ273ቱም የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች ምርጫ ይካሄዳል።

በመስከረም 20 በሚደረገው ምርጫ፤ እንደ ሱማሌ ክልል ሁሉ በበርካታ ቦታዎች ለፓርላማ መቀመጫዎች ምርጫ የሚደረገው በደቡብ ክልል ነው። የደቡብ ክልል ካለው 104 የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ውስጥ በአሁኑ ምርጫ ለውድድር የቀረቡት ሃያ ኹለቱ ናቸው። በፍርድ ቤት በነበረ ክርክር ምክንያት ሰኔ 14 ምርጫ ባልተከናወነበት በሐረሪ ክልልም ለኹለት የፓርላማ መቀመጫዎች በዚሁ ዕለት ምርጫ ይደረጋል።

የመጀመሪያ ዙር አገራዊ ምርጫ ውጤት ከግማሽ ወር በኋላ ባሳለፍነው ሐምሌ 3/2013 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ሆኗል። ቦርዱ ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት 547 መቀመጫዎች ካሉት ኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 465 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ተካተዋል። ይህም ማለት ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ ተቆርጠው የቀሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ብዛት 82 መቀመጫዎች ናቸው። የመጀመሪያ ዙር ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከ436 የሕዝብ ተወካዮች መቀመጫ ገዥው ብልጽግና 410 ወንበሮችን ማሸነፉን ቦርዱ መግለጹ የሚታወስ ነው። ቦርዱ በገለጸው ውጤት መሰረት በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 26 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና በግል ተወዳዳሪዎች ተይዘዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com