የእለት ዜና

የሴቶች አመራር ሰጭነት እና የፖለቲካ ተሳትፎ

Action For Social Development And Environmental Protection Organization (ASDEPO) 2006 ዓ፣ም የተቋቋመ እና አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት ሲሆን የተለያዩ የልማት(development) እና የሰብዓዊ (humanitarian) ሥራዎችን በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋር፣
በቢኒሻንጉል፣ በጋምቤላ እና ትግራይ ክልሎች ውስጥ በእናቶች እና ሕፃናት ጤና፣ የምግብ ሥርዓት ማሻሻል፣ የሴቶችን እና ወጣቶች የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል፣ በሠላም እና ግጭት አፈታት እንዲሁም የሴቶችን ተሳትፎ ለማሻሻል እየሠራ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴቶች ተሳትፎ በጣም ውስን እንደሆነ ይታወቃል። ሴቶች በኹሉም ማኅበረሰብ ሊባል በሚችል ደረጃ ለዘመናት አድሏዊ ልዩነት እየተደረገባቸው እና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሳይከበሩላቸው መቆየታቸውን ከታሪክ መመልከት እንችላለን። እነዚህን የመብት አለመከበር እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ልዩነቶችን ለማስወገድ በርካታ ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች እና አገር አቀፍ ሕጎች በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ውለው ይገኛሉ።

ለኹሉም የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች እውቅናን ከሰጡት እንደ ኹሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት መገለጫ(UDHR)፣ ዓለም ዐቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት(ICCPR)፣ ዓለም ዐቀፍ የኢኮኖሚ፣ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች ስምምነት(ICESCR)፣ እንዲሁም በልዩ ሁኔታ ለሴቶች መብት ልዩ ትኩረት ያደረጉት የሴቶች የፖለቲካ መብቶች ስምምነት(CPRW)፣ በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም ልዩነት ለማስወገድ የተደረገ መግለጫ(Declaration on Elimination of All Forms of Discrimination Against Women)የመሳሳሉ ሠነዶች ለሴቶች መብት ዕውቅና የሰጡ ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች ይገኙበታል።

በኢትዮጵያም የሴቶች መብት ከኢ.ፌ.ድ.ሪ. ሕገ-መንግሥት ጀምሮ በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ ዕውቅና ተሰጥቶት ይገኛል። እንዲሁም፣ በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 9/4 መሰረት ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ የሕግ አካል ይሆናሉ በማለት የደነገገ በመሆኑ፣ በስምምነቶቹ የተዘረዘሩትን የሴቶች መብት የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነት በመንግሥት ላይ ወድቋል ማለት ነው።

ምንም እንኳ የሴቶችን እኩልነት እና ኹለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ አገራዊ እና ዓለም ዐቀፋዊ ሕጎች ኢትዮጵያ ቢኖራትም፣ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ሲታይ በጣም ውስን ነው። የተወሰኑ ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ቢኖሩም እንኳ፣ ሴቶች በተወከሉበት ፓርቲ ውስጥ ያላቸው የውሳኔ ሰጭነት ድርሻ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት እጅግ አናሳ ነው።

አጠቃላይ ሴቶች በፖለቲካው ያላቸው ተሳትፎ እጅግ አናሳ ቢሆንም እንኳ፣ የሴቶችን ድርሻ በሚኒስትርነት/ በካቢኔነትም ላለፉት አመታት በምናይበት ጊዜ 13.9% ሴቶች በሚኒስትርነት ደረጃ የነበሩ ሲሆኑ፣ በ2011/12 ደግሞ 50% ደርሶ ነበር። ይህ ጽሑፍ በተጠናቀረበት ሰዓት 2013/2014 የሴቶች የካቢኔ ቄጥር 48.2% በመሆን እንደገና በ1.8 በመቶ ዝቅ ብሏል። ይህ የሴቶች ተሳትፎ በካቢኔነት ማዕረግ የጨመረ ቢሆንም፣ ይህ የሚበረታታ ቁጥር ቀጣይነት እንዲኖረው በሕግ የተደገፈ ተቋማዊ አሠራር ያስፈልጋል። ምንም እንኳ የሴቶች የቁጥር ውክልና ለሴቶች የነቃ የፖለቲካ ተሳትፎ መሠረታዊ ቢሆንም፣ በአመራርነት ደረጃ ያሉ ሴቶችም ከቁጥር ባለፈ የውሳኔ ሰጭነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሊፈተሸ ይገባል።

ሴቶች ከወንዶች እኩል በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካ ተሳታፊ እንዳይሆኑ እንቅፋት የሆኑት ባህላዊ እና አመለካከታዊ ማኀበረሰብ ሠራሽ ተግዳሮቶች ከዚህ በፊት የተገለጹ ቢሆንም፣ በዚህ ዕትም ደግሞ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የወንዶች ሚናንና የሴቶችን ተሳትፎ ለማበረታታት አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን እንመለከታለን።

ስለ ሥርዓተ-ጾታ ስናወራ በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያለውን ማኅበረሰብ ሰራሽ አስተሳሰብ፣ አመለካከት እና የሥራ ድርሻ ላይ ያተኮረ ስለሆነ፣ ሴቶች በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚው እና በፖለቲካው ላይ ያላቸው ውሱን ተሳትፎ እንዲስተካከል እና ሴቶች ለአገራቸው እና ለማኅበረሰባቸው ያላቸውን ዕምቅ አቅም ተጠቅመው ኹለንተናዊ ዕድገት እንዲያመጡ፣ እንዲሁም የስርዓተ ጾታ እኩልነትን በማረጋገጥ በሰሴች ላይ የሚስተዋለው ፍትሀዊነት የጎደለው አሰራር እንዲስተካከል፣ በተጨማሪም ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቀንሱ የወንዶች ያልተቆጠበ ጥረት ያስፈልጋል።

ወንዶች በተለይ ባሎች፣ ሴቶችን ለማብቃት፣ ሴቶች ወደ ፖለቲካው እንዲመጡ እና እንዲሳተፉ ለማበረታታት ስለ ሥርዓተ-ጾታ፣ እንዲሁም የሴቶች ዕድገት ለአገር፣ ለማኅበረሰብ የሚኖረውን ፋይዳ ጠንቅቀው ሊያውቁ እና ሊገነዘቡ ይገባቸዋል።
አብዛኛው የችግሮቻችን ምንጮች አለማወቅ እና ከነበረው ማኅበረሰብ ሰራሽ አስተሳሰብ መላቀቅ አለመቻል፣ እንዲሁም የሚጠቅመንን አዲስ አሠራርን መቀበል አለመቻል ስለሆነ በወንዶች ላይ የአመለካከት ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ ሊሠሩ ይገባቸዋል።
ይህንን ጹሑፍ በምናጠናቅርበት ጊዜ በስድስተኛው ዙር ምርጫ ዕጩ የነበሩ ሴት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን ያነጋገርን ሲሆን፣ ዕጩዎቹ እንደተናገሩት “ባሎቻችን ስለፈቀዱልን፣ ስለደገፉን እና ስለአበረታቱን ነው ለምርጫ መወዳደር የቻልነው፤ ባሎቻችን ባይፈቅዱ እና ቢቃወሙን ኖሮ ከትዳራችን ፖለቲካው ስለማይበልጥ አንወዳደርም ነበር” ብለዋል።

በተቃራኒው ደግሞ ባሎቻቸው የስድስተኛው ምርጫ ዕጩ የነበሩ ሚስቶችን በምንጠይቅበት ጊዜ፣ አብዛኛው ባሎች ሚስቶቻቸውን ሳያስፈቅዱ ለምርጫ ዕጩነት እንደተመዘገቡ እና ከተመዘገቡም በኋላ ለሚስቶቻቸው እንደነገሯቸው ገልጸውልናል። ከዚህ የምንረዳው የወንዶች ሚና የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለመጨመር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ነው።

አጠቃላይ የማኅበረሰቡን አመለካከት ለመቀየር መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍ ያለ ድርሻ አላቸው። ASDEPO ከ ዓለም ዐቀፍ የሪፐብሊካን ተቋም( International Republican Institute-IRI) ጋር በመተባበር በአገራችን ላይ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለመጨመር የሚስተዋሉ ምቹ ሁኔታዎች በማጠናከር እና በመደገፍ ሴቶች ከከፍተኛ የሥልጣን እርከን እንዲደርሱና ውሳኔ መስጠት ላይ እንዲሳተፉና እንዲሠሩም ጥሪ አቅርቧል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com