የእለት ዜና

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንቦችን አጸደቀ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ሐሙስ ባካሄደው 100ኛ መደበኛ ስብሰባው በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎች አስተላልፏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው ውይይቱ የተካሄደው በፌዴራል የገቢ ግብር ደንብ፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና የግሉ ዘርፍ ሠራተኞች ጡረታን ለመደንገግ በቀረቡት ረቂቅ ዐዋጆች፣ እንዲሁም በማዕድን ሥምምነቶች እና የተሐድሶ ሕክምና አገልግሎትን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው።

ከነሐሴ 3/ 2009 ጀምሮ በሥራ ላይ ያለው የፌዴራል የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 ጥቂት አንቀጾች ግልጽነት የሚጎድላቸውና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ ጫናን ያሳደሩ ሆነው በመገኘታቸው ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ በቀረበለት ረቂቅ የማሻሻያ ደንብ ላይ ምክር ቤቱ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

በተጨማሪም መንግሥት የዜጎችን ከአገሪቱ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ዕድገት ተጠቃሚነት ለማሳደግ በአገር አቀፍ ደረጃ ሪፎርም እያካሄደ ከመሆኑም በላይ፣ በዘርፉ በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ የሚታዩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ ይገኛል ተብሏል።
በጡረታ አገልግሎት ዕቅድ ለሚሸፈኑ ባለመብቶች ፈጣን፣ ውጤታማና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ ዕርካታ ለማሳደግ እንዲሁም ግልጽ የፈንድ አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት በሥራ ላይ የነበሩትን ዐዋጆች ማሻሻል በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጆቹ ተዘጋጅተው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርበዋል። ምክር ቤቱም በቀረቡት ረቂቅ ዐዋጆች ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ግብዓቶች በማከል ይጸድቁ ዘንድ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል።
በጡረታ አገልግሎት ዕቅድ የነበሩትን ዐዋጆች ማሻሻል በማስፈለጉ ረቂቅ ዐዋጆቹ ላይ እንዲሁ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቁ አስተላልፏል።

የማዕድን፣ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በቀረቡት ሰባት ከፍተኛ የማዕድን ልማት ስምምነቶች ላይ ምክር ቤቱ ባካሄደው ውይይት፣ የኢንቨስትመንቶቹ መተግበር ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያስገኙ፣ ከ1ሺህ 300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተመልክቷል።

ሚኒስቴሩ ባዋቀረው የሕግ፣ የቴክኒክና የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ኮሚቴ የኢንቨስትመንቶቹ አዋጭነት፣ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው ጠቀሜታ እና የኩባንያዎቹ መነሻ ካፒታል እንዲሁም ተአማኒነት በዝርዝር ተገምግሞ ስምምነቶቹ ለምክር ቤቱ ቀርበዋል። ኢንቨስትመንቶቹ በሚቋቋሙባቸው አካባቢዎች በከፍተኛ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት መርህ የሚያገለግሉ እና የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አስገዳጅ ድንጋጌዎች በስምምነቶቹ መካተታቸውን በማረጋገጥ ግብዓቶችን በማከል ስምምነቶቹ እንዲፈረሙና ወደ ሥራ እንዲገቡ ምክር ቤቱ መወሰኑ ታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!