የእለት ዜና

የሸገር ባስ ትራንስፖርት ድርጅት የክሬን አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የሸገር ባስ ትራንስፖርት ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ እና በክልል ከተሞች ተደራሽ የሚሆን የክሬን አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገለጸ።
ድርጅቱ ከሚሰጠው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በተጨማሪ፣ በመዲናዋ አዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ለሚያጋጥሙ የመኪና ብልሽቶች አገልግሎት መስጠት የሚችል የመኪና ማንሻ ወይም የክሬን አገልግሎት በይፋ መጀመሩን የሸገር ባስ ትራንስፖርት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ ሳሙኤል ፍስሐ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት ይሰጥ ከነበረው ያልተቀናጀ አገልግሎት የአሠራር ለውጥ በማድረግ እና በአዲስ መልክ በተደራጀ መልኩ በመሥራት አገልግሎቱ መጀመሩን ገልጸዋል። ቢሮ ኃላፊው አአክለውም፣ ይህ አሁን ይፋ የሆነው ፈጣን የመኪና ማንሻ ወይም የክሬን አገልግሎት ካለፈው ኹለት ሳምንት ጀምሮ በራሱ በድርጅቱ ብራንድ (መለያ) በመደበኛነት እየሠራ እንደሆነ ነው የገለጹት።

ድርጅቱ ከሚሰጠው መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት በተጨማሪ፣ ባለሙያዎችን በማሠልጠን እና ኹለት ዘመናዊ ክሬኖችን ሥራ ላይ በማዋል በአዲስ አባባ እና በክልል ከተሞች አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል። ከሦስት ዓመት በፊት አገልግሎቱ በመደበኛነት ባልተጠናከረ፣ ባልተቀናጀና ወጥነት በሌለው ሁኔታ ጀምሮ ነበር። በአሁኑ ሰዓት ከደንበኞች ጋር በመተባበር ሥራውን በአዲስ መልክ በማደራጀት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ ከሚሰጠው የሕዝብ ትራንስፖርት በተጨማሪ፣ በተጠናከረ መልኩ የክሬን አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ገልጸዋል።

ቢሮ ኃላፊው እንደገለጹት፣ ኹለት ዘመናዊ ክሬኖችን ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ ክሬኖቹ ትናንሽ እና በጣም ትላልቅ መኪኖችን የሚያነሱ ናቸው። በመሆኑም ክብደታቸው እስከ 20 ቶን ድረስ የሚሆን መካከለኛ ክብደት ያላቸውን መኪኖች ማንሳት የሚችል ነው ብለዋል። ኃላፊው አያይዘውም እነዚህ ክሬኖች አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሰዓት 1029 ብር፣ እንዲሁም በክልል ከተሞች ለሚሰጡት አገልግሎት ደግሞ በኪሎ ሜትር 47 ብር የአገልግሎት ክፍያ እንደሚጠይቁም ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

ከመስከረም 2014 ጀምሮ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የሸገር ባስ የክሬን አገልግሎት ባለሙያዎች ለ24 ሰዓት ዝግጁ ሆነው የሚሠሩ ናቸው ሲሉ ሳሙኤል ተናግረዋል። በተጨማሪም ሸገር ባስ የራሱ የሆኑ የኦፕሬተር ባለሙያዎችን በመቅጠር እየሠራ ነው ብለዋል።
የክሬን አገልግሎት በዋናነት የአውቶቢሶች ብልሽት እና አደጋ በሚደርስበት ወቅት ባለሙያዎች ሔደው ወደ ጋራዥ በማስገባት በድጋሚ አገልግሎት ላይ የሚያውል ነው። በዋናነት ለድርጅቱ አውቶቢሶች አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን የጠቆሙት ሳሙኤል፣ በትርፍ ጊዜ ሌሎች መኪኖች ሲበላሹ ሥራ ይሠራል ብለዋል።

ሸገር ባስ እየሰጠ ያለውን የክሬን አገልግሎት ለማሳለጥ ለክሬን ኦፕሬተሮቹ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ሰጥቷል። የሸገር ባስ የክሬን ኦፕሬተሮች ከፍተኛ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ለ15 ቀናት የወሰዱት ሥልጠና በሥራቸው ላይ የሚያጋጥመውን የጊዜ ብክነት እንዲቀንሱ ያስችላል ተብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!